ቀጸላ ክፍሌ
ከሕልፈተ ኢሕአዴግ በኋላ የመጣው የለውጥ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ ከለውጥ ይልቅ ነውጥን አንብሮባት ድፍን አምስት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ሳምንታት ቀርተውታል፡፡ ይህ መንግሥት በዚህ አምስት ዓመት ውስጥ ሀገሪቱ በዘመኗ አይታው ወደማታውቀው ማጥ ውስጥ ዘፍቋታል፤ ኢትዮጵያን ካለፉት የደርግና የኢሕአዴግ ሥርዓቶችም በላይ እጅግ ዘግናኝ ውርጅብኝን አከናንቧታል፡፡ ኢትዮጵያውያን ሁለገብ በኾነ መልኩ ሁሉም ብሔረሰብ በሚያስብል ደረጃ መከራ ስቃያቸውን አይተዋል፤ አሁንም የግፍ ሰንሰለቱን ቀጥለውበታል፡፡ በዚህ ስመ ለውጥ የብልጽግና መንግሥት ዘመን የትግራይ ሕዝብ በህወሓት እብሪት ሳቢያ ተነግሮ የማያልቅ የመከራ ዶፍ ወርዶበታል፡፡ የአማራ ሕዝብ የሰሜኑ ጦርነት ካሳረፈበት ጠባሳም በላይ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል እንደታዳኝ እንስሳ እየተለቀመ ታርዷል፤ ተፈናቅሏል፣ ተጨፍጭፏል፤ ሁሉም ነገር አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ የአፋር ሕዝብም በሰሜን ትግራይ በምሥራቅ ሶማሌ የጦርነት እሳት ላይ ጥደው ቀቅለውታል፡፡ በተመሳሳይ የኦሮሞ ሕዝብም አንድ በብልጽግና አንድም በሸኔ በሁለት ጥይት እየተለበለበ ይገኛል፤ ሌላው ቀርቶ ከሞላ ጎደል ሰላም የኾነው ደቡብ ክልል እንኳን እንደቀላድ መሬት መሸንሸኑ ሳያንስ እንደፍም እሳት በታቀፈው የክልል አጀንዳ መለብለብ ከጀመረ አምስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
በአጠቃላይ እንደሕዝብ ኢትዮጵያውያን ያለፉትን አምስት ዓመታት የደረሰባቸው ፍዳ ከየትኛውም ዘመን ጋር አቻ መኾን የሚቻለው አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ በመዲናዋ አዲስ አበባ እንኳን ቤት ሠርቶ ሀብት አፍርቶ የመኖር ዋስትናቸው ተገፏል፡፡ ከተማዋ በአንድ ፋናኝ ቡድን መላ አስተዳደራዊ መወቅሯ የተያዘና በተለይም ከከተማ አዋሳኝ የኦሮሚያ አመራሮች ጋር በማበር ከአንድ ቡድን ውጪ ያለ ማንነትን ላለማስተናገድ እለት እለት የሚውተረተሩባት የሞኞች አምባ ከኾነች ሰነባብታለች፡፡ በዚህም በየጊዜው ዋና መንገዶችን መዝጋት፤ ንጹሐን በላባቸው የሰሩትን ቤት በማፍረስ ተስፋ አልባ ማድረግ የተለመደ ተግባር ኾኗል፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ በተመሠረተው እና ተጠሪነቱ ለኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ነው በተባለው ሸገር ከተማ ስር በተካተቱ ስድስት ክፍላተ ከተሞች ሕገ ወጥ ናቸው በሚል ማንነትን በለየ መልኩ በአብዛኛው የአማራ ተወላጆች መኖሪያ ቤት እየፈረሰ ይገኛል። በሰበታ፣ ቡራዩ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ፣ ሱሉልታ እና ገላን የሚገኙ የአማራ፣ የትግራይ፣ የጉራጌ፣ የጋሞና መሰል ብሔር ተወላጆች መኖሪያ ቤት ያለ ምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ ፈርሶባቸው ጎዳና ላይ ወድቀዋል። አልፎም ተበድረው እና ያላቸውን ጥሪት አሟጠው የሠሩት መኖሪያ ቤት ሲፈርስ ተስፋ በመቁረጥ በገመድ በመታነቅ እና መርዝ በመጠጣት በሱሉልታ አከባቢ እስከ አሁን የታወቁ ሁለት ሰዎች እራሳቸውን አጥፍተዋል፡፡ ሕጻናትም ሜዳ ላይ በመጣላቸው ሳቢያ የጅብ ራት ኾነዋል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት፣ እናቶች እና አዛውንቶች የሚጠለሉበት አጥተው ጎዳና ላይ የወደቁ ሲኾን አንድ አከባቢ ተሰባስበው እንዳይገኙ በፀጥታ ኃይሎች እንዲበተኑ መደረጉም የተሰወረ ሀቅ አይደለም።
በጥቅሉ ሀገሪቱ አሁን ላይ በእብሪተኛና ዘረኛ ኃይሎች ትዕቢት ሳቢያ ውሃ ላይ እንደተንሳፈፈ ኩበት ወዲያ ወዲህ በመናጥ ላይ ትገኛለች፡፡ የብልጽግና መንግሥት ቃል የገባው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይሁን ለጠላቶቿ በማይገባ መልኩ የገዛ ሕዝቡን በሰቆቃ ሰንሰለት አስሮት ይገኛል፡፡ ሕዝቡን የጦርነትና ረሃብ ምርኮኛ አድርጎታል፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ የወጣ የዓለም ሕጻናት እርዳታ ድርጅት ጥናት እንዳመላከተው ከ22 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ርሃብ ተጋርጦባቸዋል፡፡ ይህ የኾነው ዝም ብሎ ሳይኾን የብልጽግናው መንግሥት በሚከተለው ፍኖተ አገዛዝ ሳቢያ መኾኑ ግልጽ ነው፡፡ ባለታደሰ አስተሳሰብ እና ባልታደሰ ሕገ መንግሥት ሀገር እየመራ ኢትዮጵያ እዚህ ደረጃ ላይ እንድትገኝ አድርጓታል፡፡ አምስት ዓመታት ሙሉ የመግለጫ ጋጋታ የሚደመጥበት ዛቻና መናናቅ የነገሰበት ኾኖ ቆይቷል፡፡ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትም የመግለጫ መዓት ያዥጎደጎዱበት ዓመታት ነበር አምስቱ ዓመት፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ጉባኤ ባለፉት ስደስት ወራት ብቻ ከ24 በላይ በሰላምና ጸጥታ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ መግለጫዎችን አውጥቷል፡፡ እንግዲህ የመብት ተሟጋች ድርጀት በስድስት ወር ይህን ያህል መግለጫ ካወጣ በአምስት ዓመታት ውስጥ ምን ያህል ሊያወጣ እንደሚችል አመላካች ነው፡፡ እንደምሳሌ ኢሰመጉ ብቻ ተጠቀሰ እንጂ እንደኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና ሌሎች መሰል የሀገር ውስጥና የውጭ ተቋማትም የሀገሪቱን የጸጥታ ሁኔታ አስመልክተው በርካታ መግለጫዎችን አውጥተዋል፡፡ ይህ የሚያመለክተው ደግሞ ሀገሪቱ በምን ዓይነት የሰላም ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ ነው፡፡ የብልጽግና መንግሥት ሀገሪቱን በምን ዓይነት መንገድ እየመራት እንደኾነ ማሳያ ነው፡፡
የኾኖ ኾኖ ሰሞኑን ይህን የመንግሥት የአገዛዝ ሥርዓት የታዘበ አንድ የዓለም አቀፍ የጥናት ተቋምም ኢትዮጵያን ፈላጭ ቆራጭ የመንግሥት አገዛዝ ካላቸው አገራት መካከል አንዷ እንደኾነች አመላክቷል፡፡ ከሰሞኑ ይፋ በኾነውና የዓለም አገራትን የዴሞክራሲን ሁኔታ በሚለካው የፈረንጆቹ 2022 ዓመት የዲሞክራሲ ኢንዴክስ፤ ኢትዮጵያን ፈላጭ ቆራጭ የመንግሥት አገዛዝ ካላቸው አገራት መካከል አንዷ አድርጓታል፡፡ “ኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ” የተሰኘው ተቋም ይፋ ያደረገው የአገራት ዓመታዊ የዲሞክራሲ ኢንዴክስ ጥናት፤ ኢትዮጵያ ባለፈው የፈረንጆቹ 2022 በፈላጭ ቆራጭ የመንግሥት አስተዳደር ውስጥ ማለፏን አመላክቷል፡፡ በእርግጥ በዚህ ጥናት መሠረት ከመላው የዓለም ሕዝብ መካከል 8 በመቶ ያክሉ ብቻ በ“ሙሉ ዲሞክራሲ” ሥርዓት ውስጥ ይኖራሉ ተብሏል፡፡ ቀሪው የዓለም ሕዝብ ከለዘብተኛ ዲሞክራሲ እስከ ፈላጭ ቆራጭ አገዛዝ ባሉት የአገዛዝ ስርዓቶች ውስጥ የሚኖር ነው፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን ግን ችግራችን ዲሞክራሲ ሳይኾን የሰላም እና የእኩልነት እጦት ነው፡፡ የእኩልነት እጦት ሲባል አሁን ላይ በሀገራችን የተንሰራፋው የዘረኝነት መንፈስ ከወለደው የአገዛዝ ቀንበር መላቀቅ ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር አሁን ላይ ኢትዮጵያውያን በአንባገነን መንግሥታት መቅናታቸው እንደማይቀር እሙን ነው፡፡ ምክንያቱም አንባገነን መንግሥታት ከአድርግ አታድርግ ሕጋቸው ውጭ በነጻነት መኖርን ይፈቅዳሉና ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን በአንባገነን መንግሥት መዳፍ ሥር ኾኖም ይህ አይፈቀድም፡፡ መንግሥት ይህን ችግር ከማስተካከል ይልቅ የነካውን ነገር ሁሉ ማበላሸት ዐብይ ሥራው ይመስላል፡፡ ለመሞትና ለመፈናቀል አልያም ጭቆናን ለማስተናገድ የፖለቲካ ጥያቄ ማንሳት ሳያስፈልግ ብሔረሰባዊ ማንነት ብቻውን በቂ ነው፡፡ አሁን ላይ በኢትዮጵያ ምድር ብሔረሰባዊ ማንነት ሲፈልግ ይገድላል፤ ያፈናቅላል፤ ሲለው ደግሞ ከሞትም ከምንም በላይ አድርጎ በአንድ ጀምበር የሀብት ማማ ላይ ይሰቅላል፡፡ በአዲስ አበባችንም ኾነ በኢትዮጵያችን አሁን ላይ ግዘፍ ነስቶ እየታየ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሰሞኑን ከወለጋ ተነስተው ደብረብርሐን የገቡት 35ሺህ የአማራ ተወላጅ ተፈናቃዮች ምስክር ናቸው፡፡ ለዘመናት አንዲት ኾና የኖረች ቤተክርስቲያንን በብሔረሰባዊ ማንነት ለመክፈል የተሔደበት ርቀት ሌላኛው ዋቢ ነው፡፡
