ያለፉት ሳምንታት ለኢትዮጵያ መልካም ኾነው አልሰነበቱም፡፡ መጪዎቹ ጊዜያትም ቀላል አይመስሉም፡፡ በርግጥ ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ችግር እና መከራ ዕጣ ፈንታቸው ከኾነ ሰንብቷል፡፡ ዕንባቸውን የሚያብስ ሳይኾን ቀውስን የሚጠምቅላቸው እንደ አሸን የበረከተበት ዘመን በመኾኑም ይኽ መኾኑ ላይገርም ይችል ይኾናል፡፡ እንዲስቁ ሳይኾን በየአጋጣሚው ማቅ እንዲለብሱ መከራን ጊዜ እየጠበቀ የሚያዋልድ ኃይል በሀገሩ ላይ መሰልጠኑ ትናንትም፣ ዛሬም ነገም ነገራችን ኹሉ የስቅየት እንዲኾን አስገድዷል፡፡
የአሁኑ ግን ይለያል፡፡ ኢትዮጵያ ቆዳዋ ተገፍፎ በቀረቻት ስስ ጅማት መቆሟ ያስቆጫቸው ኃይሎች የማይነካውን ነክተው ተዝካሯን ለማውጣት ቋምጠዋል፡፡ እነኚህ ሰይጣናዊ ፍላጎቶች ያደሩ እንጂ የአንድ ጀምበር ቅዠቶች አይደሉም፡፡ ገና ከዓመታት በፊት ሲታሰቡ፣ ሲወጠኑ፣ ሲረቀቁ እና የትግበራ ሰነድ ሲዘጋጅላቸው የኖሩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ አስደንጋጩ ጉዳይ፣ በዚህ ልክ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን አፍርሶ ‹‹ኢትዮጵያን ለመመራት›› የሚመኝ ‹‹ባለአእምሮ›› አጀንዳውን በመሪነት የሚዘውር መኾኑ ነው፡፡
ግዮን መጽሔት በዚህ ዕትም ርዕሰ አንቀጽዋ ‹‹መንግሥት ኢትዮጵያ እንድትኖር ይፈልጋልን?›› ስትል አበክራ ትጠይቃለች፡፡ ይኽ ጥያቄ ተራ እና ቀሊል እንቶ ፈንቶ አይደለም፡፡ ዛሬን ከትናንት ለማወዳደርም ኾነ ኢትዮጵያን ከሌላው ዓለም ለማነጻጸር ለሚነሳ ማንኛውም ባለአእምሮ ከሚደርስበት ፍጹም ግራ ገብ እውነታ ተነስቶ የሚጠይቀው ጥያቄ በመኾኑ ነው፡፡ ዘወትር ስለ ጠንካራ ተቋማት ለሀገር አስፈላጊነት ሲደሰኩር የሚውል መንግሥት በዚህ ልክ ለሺህ ዓመታት ጠንካራ የሕግ፣ የሞራል እና የዕሴት ምንጭ ኾና በኖረች ተቋም ፍርሰት ላይ አንዳንዴ ተባባሪ ሌላጊዜ ደግሞ ገለልተኛ መስሎ ከመታየቱ የሚወለድ ጥያቄ በመኾኑ ነው፡፡
እንዲህ ያለው የመንግሥት ሚና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ከፋፍሎ በማዳከም ‹‹ኢትዮጵያን መምራት ይቻላል›› ከሚል ዐቋም የመነጨ ከኾነ ዛሬም ደጋግሞ እንዲያስብበት ይመከራል፡፡ ባለፉት ሳምንታት ድፍረት በተሞላበት መንገድ የፈጸማቸውን ይፋዊ ነውሮችም ገና ያልተወራረዱ ሒሳቦች መኾናቸውን በዚሁ አጋጣሚ ማስታወስም ይገባል፡፡ በተለይም በኦሮሚያ ክልል በቅዱስ ሲኖዶስ የተወገዘውን ሕገወጥ ቡድን በልዩ ኃይል ፓትሮሎች በማጀብ አብያተ ክርስቲያናትን እና መንበረ ጵጵስናዎችን በመሰባበር እና በሻሸመኔ ከተማ ደግሞ በርካታ ቁጥር ያላቸውን አማኒያን ተኩሶ በመግደል የፈጸመው ሸፍጥ እንዲህ በቀላል መረሳት የሚችል አይደለም፡፡ ይኽ የመንግሥት ሕገ ወጦችን ‹‹አለሁኝ›› የማለት አቋም አሁንም ከቤተክርስቲያኒቱ ሕጋዊ አካል ከኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር ‹‹መግባብት›› ላይ ደረሰ ከተባለ በኋላም በአንዳንድ አካባቢዎች መቀጠሉ ከምንም በላይ ክፍፍሉን ይፈልገው እንደነበር አመላካች ነው፡፡
‹‹መንግሥት ኢትዮጵያ እንድትኖር ይፈልጋልን?!›› የሚለውን ጥያቄ መጽሔታችን ደግማ የምታነሳውም፣ ክቡር ጠ/ሚኒስትሩም ኾኑ በዙሪያቸው ያሉ አማካሪዎቻቸው በዚህ ጉዳይ ላይ እያራመዱ ያሉት አቋም ትወና የተሞላበት፣ በማደናገሪያዎች የታጀበ እና የፖለቲካውን መጠነ ፣ሙቀት ተከትሎ በሚቀያየር የኃይል አሰላለፍ ላ እንጂ በሕግ እና በመርኅ ላይ የተመሠረተ ባለመኾኑ ነው፡፡
ለዚህ ደግሞ ባለፉት ሳምንታት ጠ/ሚኒስትሩ ከሚኒስተሮቻቸው ጋር አደረጉት በተባለውና እርሳቸው ብቻ ተናግረው እርሳቸው ብቻ በቋጩት ስብሰባ ጉዳዩን አስመልክቶ ያራመዱትን ፍጹም ስሁት ዐቋም፣ ጉዳዩ የምልዓተ ሕዝቡ ኾኖ መንበራቸውን ማንቀጥቀጥ የጀመረ በመሰለበት ጊዜ ወጥተው ካራመዱት ፍጹም የራቀ የሚመስል ሌላ አቋም ጋር አሰናስሎ መመልከት ጠቃሚ ነው፡፡ በአንድ በኩል ቤተክርስቲያኒቱ ለሕጓ እና ለቀኖናዋ ታምና የሔደችበት ሰላማዊ ትግል፣ በሌላ በኩል የሀገር ሕልውና እንዳይናጋ የወሰደችው ኃላፊነት ነገሮች መጥፎ አቅጣጫ እንዳይዙ በብዙ ረድቷል፡፡
በአንጻሩ መንግሥት ከያዘው ስሁት ዐቋም በተወሰነ ደረጃ መለስ ያለ ቢመስልም፣ አሁንም (በተለይም በኦሮሚያ ክልል) የሰተሳሳተው ስሌቱን ተፈጻሚ ለማድረግ ሕገወጥ ከኾኑ አካሔዶች የተመለሰ አይመስልም፡፡ ለዚህ ባለፈው አንድ ሳምንት ብቻ አፈንጋጭ የተባሉት ጳጳሳት በ‹‹እርቅ›› ወደ ቅዱስ ሲኖዶስ ተመለሱ ከተባለ በኋላ የተወሰኑቱ ከድርጊታቸው አለመታቀባቸውን አይቶ እንዳላየ መኾንን መርጧል፡፡ ይኽ ያልጠራና በሴራ የታጀበ አካሔዱ ግን አሁንም እውን መንግሥት ኢትዮጵያ እንድትኖር ይፈልጋልን? የሚለውን ጥያቄ በግዝፈት እንድንጠይቅ ያስገድደናልና ልብ ይግዛ ስንል መልዕክታችንን እናስተላልፋለን፡፡ ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን ይጠብቅ!
