የአሜሪካ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤት ኃላፊ ማርክ ሩቢዮ በናይሮቢ እና በአዲስ አበባ ሊያደርጉት የነበረውን ጉብኝት መሰረዛቸው ተሰምቷል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ሊያደርጉት የነበረውን ጉብኝት የሰረዙት፤ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ለአምስት ቀናት በቻይና ጉብኝት ለማድረግ ወደ ቤጂንግ ካቀኑ ከሰዓታት በኋላ መሆኑ ነው የተገለጸው።
እንደ አፍሪካ ኢንተለጀንስ ዘገባ ከሆነ የሩቢዮ የመጀመሪያው የአፍሪካ ጉብኝት ‘በደህንነት እና የንግድ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደርጋል’ ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም፤ ጉብኝቱ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሟል።
ይሁን እንጂ ፕሬዚዳንት ሩቶ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ዋሽንግተንን ሊጎበኙ ይችላሉ ተብሏል፡፡
በቻይና ጉብኝታቸው ዛሬ የጀመረው የኬንያው ፕሬዚደንት ዊልያም ሩቶ፤ የአሜሪካ ታሪፍ የዓለም ንግድን ካቋረጠ ወዲህ ቤጂንግን የጎበኙ የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሪ ሆነዋል።
የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በጣለው የንግድ ታሪፍ ከተጎዱ 185 ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ እና ኬንያ ይገኙበታል።
ከመጋቢት ወር መጨረሻ ጀምሮ የ10 በመቶ የመነሻ ታሪፍ ከእነዚህ አገሮች ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሁሉም ምርቶች ላይ ተግባራዊ መደረጉ ይታወሳል።
የትራምፕ የ10 በመቶ ቀረጥ “የመጀመሪያ ታሪፍ” ተብሎ የተገለጸም ሲሆን፣ ይህ ማለት አሜሪካ ባለፉት ዓመታት ‘ኢኮኖሚዋን ተጠቅመዋል’ ብላ ለምታምንባቸው አገሮች ተጨማሪ ታሪፍ ይኖራል የሚል ግምትን አስሰጥቷል።
ይህንንም ተከትሎ አሜሪካ የጣለችውን አዲስ ታሪፍ ከቻይና በስተቀር ባሉ አገሮች ላይ የተፈጻሚነት ጊዜውን ለ90 ቀናት ማራዘሟን አስታውቃለች፡፡
አዲሱ ዝቅተኛ ታሪፍ ከኬንያ ወደ አሜሪካ የሚላኩ ምርቶች በሙሉ የኮታና የቀረጥ ነፃ ዕድል (አጎዋ)ሥር ያሉ ምርቶችን ጨምሮ፤ ኬንያ ከ50 በመቶ በላይ እቃዎቿን ከቀረጥ ነጻ ወደ አሜሪካ እንድትልክ አስችሏታል።
ይህም 25 ዓመታትን ያስቆጠረው የአፍሪካ አገራትን ከቀረጥ ነፃ የሚያደርጋቸው አጎዋ፤ በአዲሱ የታሪፍ ተመን መሰረት የአፍሪካ አገራት ከዕድሉ ውጭ እንደሚያደርጋቸው ተዘግቧል፡፡
በዚህ የንግድ ጉዳይ እና በደህንነት ጉዳዮች ላይ ለመወያየት በመጀመሪያ ወደ ናይሮቢ በማምራት ከዛም ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡ የተገለጸው ማርክ ሩቢዮ፤ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በቻይና ጉብኝት ለማድረግ ወደ ቤጂንግ ማቅናታቸውን ተከትሎ ጉብኝታቸውን ላልተወሰነ ጊዜ ማራዘማቸው ተነግሯል።
#አሐዱ_የኢትዮጵያውያን_ድምጽ
