አየር መንገዱ ለሐጅ ተጓዦች ያዘጋጀውን ልዩ የሐጅ ጉዞ አገልግሎት የኢትዮጵያ አየር መንገድ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ አቶ ለማ ያደቻ፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ዛሬ በይፋ አስጀምሯል።
የአየር መንገዱ የንግድ ዘርፍ ዋና ኃላፊ አቶ ለማ ያደቻ በፕሮግራሙ ማስጀመሪያ መድረክ ባደረጉት ንግግር ለመላው ሙስሊም ማህበረሰብ ለ1446ኛው ሐጅ እንኳን አደረሳችሁ ብለዋል።
ኃላፊው አየር መንገዱ ለሐጃጆች ልዩ የመስገጃና የማረፊያ ቦታ ያለው የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጫ አዘጋጅቶ ከዛሬ ጀምሮ ክፍት ማድረጉን አስታውቀዋል።
አየር መንገዱ ለሐጅ ተጓዧች የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠትን ጨምሮ በየዓመቱ ከሙስሊሙ ማህበረሰቡ ጋር በጋራ በርካታ ተግባራት ሲሰራ መቆየቱን ጠቁመው፤ ወደፊትም በቅርበትና በትጋት ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሸህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ በበኩላቸው፤ አየር መንገዱ ሙስሊሙን ማህበረሰብ በዚህ ደረጃ ለማስተናገድ መዘጋጀቱ የመንግስትን ቁርጠኝነት ማሳያ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢትዮጵያን በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም እያስተዋወቀ የሚገኝ የሀገር ምልክት ኩራት የሆነ የጋራ ተቋማችን ነው ሲሉ ገልጸዋል።
