የቀድሞው ሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ የክስ መዝገብ በዛሬው ዕለት በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቢቀርብም፤ በተመሳሳይ ምክንያት ለ4ኛ ጊዜ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶበታል፡፡
በዚህም መሠረት የተከሳሹ መዝገብ ለግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም. ቀጠሮ እንደተሰጠው የአቶ ታዬ ደንደአ ጠበቃ አበራ ንጉሤ ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
አቶ ታዬ ከዚህ በፊት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሕገ-መንግሥትና ሕገ-መንግሥት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ችሎት ከተከሰሱበት ከሦስቱ ክሶች መካከል በሁለቱ ማለትም፤ ሁከት እና ብጥብት በማነሳሳት እና የፀረ ሰላም ኃይሎችን በመደገፍ ክሶች በነጻ መሰናበታቸው የሚታወቅ ነው።
ጠበቃው እንደገለጹት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነጻ የተባለውን ክስ ዐቃቤ ሕግ ይግባኝ በመጠየቁ ክርክሩ ቀጥሏል፡፡
“በክርክር ሂደቱ ግን መዝገቡን የሚያው ዳኛ በመታመሙና ችሎት ላይ በአካል መቅረብ ባለመቻሉ፤ ለ4ተኛ ጊዜ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል” ብለዋል፡፡
“ጉዳዩን መዝገቡን የተቀበሉ ዳኞች ማየት ይችሉ ነበር፡፡ የተሰጠው ምክንያት አሳማኝ አይደለም” ያሉት የሕግ ባለሙያ እና ጠበቃው አቶ አበራ፤ በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች መዋቅርና ሕግ መሠረት ዳኝነት በችሎቱ ባለ1፣ ባለ3፣ ባለ5 እና ባለ 7 ሆኖ የሚዳኝበት ሥነ-ስርዓት ሲሆን 4ተኛ ዳኛ መኖሩ ይህንን ስርዓት የሚጥስ በመሆኑ አፋጣኝ ፍትህ ሊሰጥ እንደሚገባ ለችሎቱ ማስረዳታቸውን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
ግራ ቀኙን ያደመጠው ፍርድ ቤትም መዝገቡን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለመጨረሻ ጊዜ በሚል ለግንቦት 25 ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
