ኢትዮጵያን እና ኬንያን በሚያዋስነው በሞያሌ ድንበር ላይ ኢትዮጵያውያን 50 ኪሎ ሜትር ወደ ኬንያ እንዲሁም ኬንያውያን 100 ኪሎ ሜትር ወደ ኢትዮጵያ ገብተው እንዲገበያዩ የሚፈቅደው ስምምነት፤ በአካባቢው ያለውን ሕገ-ወጥ ንግድ ለማስቀረት እንደሚያግዝ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል።
የተቋሙ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ወንድሙ ፍላቴ፤ ባሳለፍነው የፈረንጆች ዓመት ኬንያ 115 ሚልየን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ወደ ኢትዮጵያ ስትልክ በአንጻሩ ኢትዮጵያ 58 ሚልየን ዶላር ዋጋ ያላቸው ምርቶችን ወደ ኬንያ መላኳን አስታውሰው፤ የሁለቱ hገራት ዓመታዊ የንግድ ልውውጥ ከ200 ሚልየን ዶላር በታች መሆኑን ገልጸዋል።
አዲሱ ስምምነት በሦስት መሰረታዊ ነጥቦች ላይ ያተኮረ ሲሆን፤ ዋና ዓላማው ኢትዮጵያ እና ኬንያ የሚዋሰኑት ቦታዎች የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች የመሀል አገር ምርትን በቀላሉ ማግኝት እንዲችሉ ማድረግ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
“በተጨማሪም ድንበር አካባቢ የሚስተዋለውን ሕገ-ወጥ ንግድ ማስቀረት እንዲሁም፤ የአካባቢውን ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ማረጋገጥ ዓላማው አድርጓል” ብለዋል።
በድንበር ላይ ንግድ ልውውጡ የተለያዩ መሠረታዊ ምርቶች፣ የምግብ ዘይት፣ ቆዳና ሌጦ፣ አልባሳት፣ የውበት መጠበቂያ ምርቶች፣ የእንስሳት ተዋፅኦ፣ የኤሌክትሮኒክስ ምርቶች፣ የቤት ውስጥ መገልገያ ቁሳቁሶች፣ እንዲሁም አትክልት እና ፍራፍሬ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በዚህም ስምምነት መሠረት ነጋዴዎች በጋራ በተስማሙበት የምርት ዝርዝር መሠረት እስከ 1 ሺሕ የአሜሪካ ዶላር የሚደርስ የንግድ ልውውጥ በወር እስከ አራት ጊዜ ድረስ ማካሄድ ይችላሉ ተብሏል።
በተያያዘ ሁለቱ ሀገራት በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) አስተባባሪነት በአፍሪካ ቀንድ የሁለትዮሽ ትብብር ልማት ፕሮጀክቶች ዙሪያ ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ ባደረጉት ውይይት፤ የሁለትዮሽ ንግድን ለማጎልበት ድንበር ተሻጋሪ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች ለመገንባት ተስማምተዋል።
በዚህም አዲስ አበባ እና ናይሮቢ በዳዋ ወንዝ ላይ ሁለት ድልድዮችን ለመገንባት መስማማታቸው ተነግሯል።
የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) ድልድዮቹን “የተስፋ መተላለፊያዎች” ሲል የገለጸም ሲሆን፤ “ተሽከርካሪዎችን ብቻ ሳይሆን በቂ የመሠረታዊ አገልግሎቶች የማያገኙ ማሕበረሰቦችን ምኞት የሚስተላልፍ ነው” ሲል ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
በተጨማሪም የራሙ አንድ አለቅ የድንበር ጣቢያ እና የሱፍቱ የንግድ ማሳለጫ ማዕከል ወደ ሥራ እንደሚገቡ ተመላክቷል።
በዚህም ሀገራቱ የድንበር ተሻጋሪ የፋይበር ኦፕቲክ ግንኙነትን ለማጠናቀቅ፣ የድንበር ተሻጋሪ ዲጂታል አገልግሎቶችን ለማሻሻል እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ተደራሽ ለማድረግ መስማማታቸውም ነው የተነገረው።
(አሐዱ ሬድዮ)
