ሩሲያ በዩክሬይን ላይ በ407 ድሮኖችና በ45 ሚሳኤሎች ጥቃት ሰነዘረች፡፡ በዛሬው እለት ሩሲያ በፈፀመችው በዚህ ጥቃት ቢያንስ አምስት ሰዎች መገደላቸውንና ከ70 በላይ መቁሰላቸውን የዩክሬይን ባለስልጣናት ገልፀዋል፡፡
የዩክሬይን አየር ሀይል ባወጣው መግለጫ ሩሲያ ከላከቻቸው 407 ድሮኖች መካከል 368ቱን ማክሸፉን ገልፆ ከ45ቱ ሚኤሎች ውስጥ 36ቱን መመከቱን አስረድቷል፡፡ ከእነዚህ መካከል ስድስቱ ኢስካንዳር የሚባሉት ሚሳኤሎች መሆናቸውንም ገልጿል፡፡
ሩሲያ ዛሬ አርብ ይህንን ጥቃት የፈፀመችው በመላው ዩክሬይን ሲሆን በተለይ ዋና ከተማዋ ኬይቭ ላይ ከፍተኛ የሚባለው ምት መድረሱ ተዘግቧል፡፡ በተለይም በበርካታ መሰረተ ልማቶች ላይ ጥቃቱ ያነጣጠረ መሆኑን የጠቀሱት ዘገባዎች በዩክሬይን የሚገኙ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የባቡር መስመሮች መቋረጣቸውንም አስረድተዋል፡፡ በተያያዘ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ባወጣው መግለጫ ዛሬ መጠነ ሰፊ ጥቃት ማከናወኑን አስታውቋል፡፡
በመግለጫው ‹‹የኬይቭ መንግስት ለፈፀመው የሽብር ጥቃት መልስ የሚሆን በምድር፣ በአየርና በባህር የሚወነጨፉ ሚሳኤሎችንና ድሮኖችን ተጠቅመን እርምጃ ወስደናል፡፡ ሁሉም ኢላማዎቻችን ወታደራዊ ናቸው›› ብሏል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ትራምፕ ትላንት ባደረጉት ንግግር ዩክሬይንና ሩሲያን ወደሰላም ከማምጣት ይልቅ ትንሽ ጊዜ እንዲዋጉ መፍቀድ የተሻለ ሊሆን ይችላል ማለታቸው ይታወሳል፡፡
