የሴኔጋል ጠቅላይ ሚኒስትር ኦስማኔ ሳንኮ በተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ የሚፈረደውን ከፍተኛውን የእስር ቅጣት በእጥፍ ሊጨምር የሚችል ረቂቅ ሕግ አቀረቡ። በአዲሱ ረቂቅ ሕግ መሠረት የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን እስከ 10 ዓመት በሚደርስ እስር ሊቀጡ ይችላሉ።
የሴኔጋል ካቢኔ ባለፈው ሳምንት ያጸደቀው ይህ ረቂቅ ሕግ ማክሰኞ ዕለት ለአገሪቱ ፓርላማ ቀርቧል። ቀድሞውኑ በሕግ ክልከላ በጣለችው ሴኔጋል ይህ ረቂቅ የተዘጋጀው፤ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ውስጥ ተገኝተዋል የተባሉ ሰዎች ላይ ተከታታይ እስሮች ከተፈጸሙ በኋላ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሳንኮ በፓርላማ ለሕግ አውጪዎች ባደረጉት ንግግር፤ አዲሱ ሕግ “ከተፈጥሮ የተቃረነ ድርጊት” ሲሉ የጠሩትን ተግባር ከአምስት እስከ 10 ዓመት በሚደርስ እስር የሚቀጣ እንደሆነ ገልጸዋል። በነባሩ ሕግ ግን የሚያስቀጣው ከአንድ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እስር ነበር።
“ድርጊቱ በዕድሜ ካልደረሱ ልጆች ጋር የተፈጸመ ከሆነ ከፍተኛውን ቅጣት ያስወስናል” ሲሉ ተናግረዋል። የመብቶች ተሟጋቾች በበኩላቸው ረቂቅ ሕጉን ተችተዋል።
የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ተሟጋች መሆን እንደ የውጭ ጣልቃ ገብነት በሚቆጠርባት ወግ አጥባቂዋ ሴኔጋል ውስጥ፤ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት መብትን በተመለከተ የሚደረግ ክርክር ውጥረት የሚፈጥር ጉዳይ ነው።
በቅርብ ዓመታት የሃይማኖት ተቋማት ከፍተኛ ቅጣት እንዲጣል የሚጠይቁ ሰልፎችን አካሂደዋል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ደግሞ የአገሪቱ ፖሊስ በፀረ ተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ሕግ አማካኝነት ሁለት ታዋቂ ግለሰቦች እና አንድ ስመ ጥር ጋዜጠኛን በቁጥጥር ሥር አውሏል። በአጠቃላይ በዚህ ወር 30 ገደማ ሰዎች ከዚሁ ጋር በተያያዘ እንደታሰሩ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
