የአቶ ጋሻው መርሻና የቢቢሲ ቃለ ምልልስ ለምን ተቋረጠ ?

Date:

“የአማራ ክልል 95 በመቶ አካባቢ ሰላም ነው”

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ይካሄዱ የነበሩ ሕዝባዊ እንቅስቃሴዎችንተከትሎ በተሰባሰቡ ወጣቶች ነበር ወደ ፓርቲነት ያደገው።

ከለውጡ በኋላም በአማራ ክልል በርካታ ደጋፊዎችን ማፍራት የቻለ አገራዊ የፖለቲካ ፓርቲ ለመሆን በቅቷል። በ2013 ምርጫ የተወዳደሩ የተወሰኑ አመራሮቹ የምክር ቤት መቀመጫ ሲያገኙ ሌሎች ደግሞ መንግሥታዊ ሹመት ይዘው በተለያዩ ተቋማት ውስጥ እያገለገሉ ይገኛሉ።

የሕዝብ ተወካዮቹ በምክር ቤቱ ጠንካራ ሃሳቦችን እና ትችቶችን ከማንሳት ባለፈ ፓርቲው በሚወክለው ሕዝብ ላይ እየደረሱ ነው ያላቸውን በደሎችን እና የመብት ጥሰቶች በጠንካራ መግለጫ ሲያስታውቅ ቆይቷል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የፓርቲው እንቅስቃሴ እና ድምጽ እምብዛም አይሰማም። በአባላቱ መካከልም ክፍፍል ተፈጥሯል። ክፍፍሉ ለምን ተፈጠረ? በክልሉ ስለሚካሄደው የትጥቅ እንቅስቃሴ ምን ይላል? እና ሌሎችንም ጥያቄዎች እንዲመልሱልን የፓርቲውን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጋሻው መርሻን ጋብዘናል።

በአማራ ክልል ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ እና ስለፓርቲው ማብራሪያ እንዲሰጡ ቢቢሲ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ከሆኑት ከአቶ ጋሻው መርሻ ጋር ቃለ ምልልስ አድርጓል። አቶ ጋሻው በአገራዊ፣ በክልላዊ እና በአብን ጉዳዮች ላይ የቀረቡላቸውን ጥያቄ ከሞላ ጎደል ከመለሱ በኋላ ቢቢሲን በወገንተኝነት በመክሰስ ቃለ ምልልሱን አቋርጠዋል። ቃለ ምልልሱን እንዲያቋርጡ ያደረጋቸው ጥያቄ ምን ነበር?

ቢቢሲ፡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ከዚህ ቀደም እንደነበረው ጠንካራ ድምጹ አይሰማም። አብን አሁን ምን ላይ ነው ያለው?

አቶ ጋሻው፡ አብን አለ። በጥሩ ቁመና ላይ ነው ያለው። በቅርቡ ጉባዔ አካሂደናል። አዳዲስ አመራሮችን መርጠናል፤ የነበሩትም ቀጥለዋል። ስለዚህ በጥሩ የድርጅታዊ ቁመና ላይ ነው ያለው።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከፍተኛ መሳከር ስላለ እና ግጭት የሚካሄድበት ስለሆነ፤ እኛ የምንንቀሳቀስበት አካባቢ ደግሞ ለሦስት ዓመት ገደማ በግጭት ውስጥ ነው ያለው። ከዚህ የተነሳ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ስናካሂድ ላንታይ እንችላለን፤ ነገር ግን ድርጅታዊ ሥራ እየሠራን በጥሩ ቁመና ላይ እንገኛለን።

ቢቢሲ፡ በምትወክሉት ክልል ውስጥ በሚካሄደው ግጭት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸሙ እና ቀውሶች እያጋጠሙ እንደሆነ ሪፖርቶች ይወጣሉ። ሆኖም አብን በዚህ ላይ መግለጫ ሲያወጣ አይታይም። ለምንድን ነው?

አቶ ጋሻው፡ ጠንካራ መግለጫ ሲያወጡ አይታይም የሚለው የአረዳድ ጉዳይ ነው። ፓርቲው አሁንም ጠንካራ ነው። ሁልጊዜ ለሕዝብ የወገነ ፓርቲ ነው። ሕዝብ ተበድሏል፤ ሥርዓት ተጓድሏል ብለን ባሰብን ጊዜ ሁሉ መግለጫዎችን እናወጣለን፤ ጋዜጣዊ መግለጫዎችን እንሰጣለን። አስፈላጊ የሆኑ ትግሎችንም እናካሂዳለን።

ምናልባት በጣም ስሜታዊ በሆነ መልክ፣ ስሜት ኮርኳሪ በሆኑ ቃላት አልተናገራችሁም ወይም ደግሞ ነገሩን የሚያባብስ ነገር አልተናገራችሁም የሚል ግምገማ ከዚህም ከዚያም እንሰማለን። ያ ግን ፖለቲካ አይደለም። ፖለቲካ በስሌት እንጂ በስሜት የሚሠራ አይደለም። እኛ በነበርንበት ቁመና ላይ ነው ያለነው። ከነበርንበት ቁመና ላይ አንድ ስንዝር እንኳን አልራቅንም።

ቢቢሲ፡ በተለይ ግጭቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ በክልሉ እየደረሱ ያሉ በርካታ ሰብዓዊ እና ማኅበራዊ ቀውሶች ነቅሳችሁ ያወጣችሁበትን መግለጫ አልታየም። በክልሉ ምን እየተካሄደ እንዳለ እየደረሰ ያለው ቀውስ ምን ያህል እንደሆነ ታውቃለችሁ?

ምላሽ ምንድን ነው?

አቶ ጋሻው፡ እንግዲህ እኛ ነባር ፖለቲከኞች ነን። የዚህን አገር ፖለቲካ ከየት ወዴት የምናውቅ ሰዎች ነን። ገና ለገና ሃሳባችን ከመንግሥት ስለገጠመ ከመንግሥት ጋር አብረው ናቸው እንዳንባል ብለን ልንቃወም አንችልም።

ከመንግሥት ጋር በምንስማማበት ጉዳይ አብረን እየሠራን እንቀጥላለን። ከመንግሥት ጋር ልዩነት ባለን ጉዳይ ላይ ደግሞ መንግሥት ላይ ተፅዕኖ እየፈጠርን የምንችለውን እያደረግን እንቀጥላለን። ይህ የሠለጠነ የፖለቲካ አካሄድ ነው። መጯጯህ እና ስሜታዊ በሆኑ ቃላት ሕዝብን ማስቆጣት ፖለቲካ ሳይሆን ስሜት ነው።

ፖለቲካ የስሌት ጉዳይ ነው። እኛ ትክክለኛው አቋም ላይ ነው ያለነው። ፓርቲው ከማንኛውም ጊዜ በተሻለ የጠራ ሃሳብ እና የጠራ አቋም ያላቸው አመራሮች በሚመሩት ወቅት ላይ ነው ያለው። ተግባራዊ የሆነ እንቅስቃሴ ላይ ነው ያለነው። ፓርቲውም፣ የተጠቀሱት ሰዎችም ከመንግሥት ጋር የሚሠሩትም አገራቸውን እያገለገሉ ነው ያሉት።

በአብዛኛው በአማራ ሕዝብ ስም የሚደረግ ጩኸት ለሻዕቢያ እና ለወያኔ የሚደረግ ራስን የማሳየት ጩኸት እንጂ ለአማራ ሕዝብ የሚጮህ ጩኸት ነው ብለን አናምንም። አየን እኮ! ለአማራ ሕዝብ በጠመንጃ መንግሥት እንጥልልሃለን ያሉት ሰዎች የአማራን ሕዝብ ጥለው አሳዩን እኮ። በጩኸት በጫጫታ ሕዝብን በፕሮፖጋንዳ በማደንዘዝ ምን ያህል ዋጋ እንደተከፈለ አየን እኮ!

ለሦስት ዓመት ትምህርት ቤት አልተከፈተም። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ናቸው። ኢንዱስትሪዎች ከሥራ ውጪ ናቸው። መሠረተ ልማቶች እየወደሙ ነው። የትምህርት ቤት ጣራ ተገፎ እየተሸጠ ነው። ይህንን የሚቀሰቅሱ ሰዎች ታጋይ ሆነው እኛ ከሃዲ የምንሆንበት ምንም ዓይነት የሞራልም፣ የመርኅም ሌላም ምክንያት የለም።

ምን አልባት ሕዝብ መስማት የሚፈልገውን መናገር እና እንዲሆንለት የሚፈልገውን ማድረግ የተለያዩ ናቸው። እኛ ሕዝብ እንዲሆንለት የሚፈልገውን፣ ቢሆንለት ይጠቅመዋል የሚለውን በመሥራት ላይ እንገኛለን።

ቢቢሲ፡ ወደ ምርጫ እንምጣ። በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል በሚካሄዱ ግጭቶች ምክንያት አስቻይ ሁኔታ የለም ሲሉ ስጋታቸውን የሚገልጹ አሉ። እናንተ የምትወክሉት ሕዝብ ግጭት ውስጥ ነው ያለው። እናንተስ አስቻይ ሁኔታ አለ ብላችሁ ታምናላችሁ?

አቶ ጋሻው፡ ዲሞክራሲ የአንድ ቀን ሥራ አይደለም። ሁልጊዜ በአበባ ላይ መራመድም አይደለም። አንዳንዴ ተግዳሮቶችን ማለፍም ያስፈልጋል። ሁኔታው የተመቸ ስለሆነ አይደለም እኮ የምንታገለው። ሁኔታው የተመቸ ቢሆንማ ፓርቲ አቋቁመን አንታገልም ነበር እኮ። የተመቸ ሁኔታ ስለሌለ ነው ፓርቲ አቋቁመን እየታገልን ያለነው።

ቢቢሲ፡ስለድሎትና ምቾት አይደለም ያነሳሁት። ወደ ክልሉ ሄዶ ከሕዝብ ጋር መወያየት ያስፈልጋል። ክልሉ ግጭት ውስጥ ነው። ነዋሪዎችም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ ነው የሚናገሩት።ይህንን እንዴት ነው የምትጋፈጡት?

አቶ ጋሻው፡ ፖለቲካ ማለት ይህንን መጋፈጥ ነው። ነገሩ ሁሉ አልጋ ባልጋ ከሆነማ እኛም ወደ ሌላ ሥራ እና ልጆቻችን ወደ ማሳደግ እንሄድ ነበር እኮ። ነገር ግን ይህንን ፈተና ተጋፍጦ እዚያ ተግዳሮት ጋር በሚደረግ ትግል የሚመጣ ውጤት ነው የፖለቲካ ውጤት የምንለው።

ሆኖም አገሩ ሰላም በሰላም ነው፤ ፍቅር በፍቅር ነው እያልኩ አይደለም። ትግራይ፣ አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እንዲሁም በየቦታው ግጭት አለ፤ ግን አጠቃላይ የአገሪቱ መገለጫ አይደለም።

የተወሰነ የተወሰነ ኪስ ቦታዎች እና ወረዳዎች ላይ ግጭት አለ። ለምሳሌ አማራ ክልልን ብንወስድ ከ95 በመቶ በላይ ያለው አካባቢ ሰላም ነው።

ግጭቱ በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚጮህ አገሩ በሙሉ ችግር ውስጥ ያለ መስሎ ስለሚታይ ነው እንጂ ኪስ ቦታዎች ላይ ነው ግጭቶች ያሉት። እነዚያ ቦታዎችም ላይ ቢሆን አስፈላጊ ነው የሚል እምነት የለንም። የሚገለውም የሚሞተውም የራሳችን ወንድሞቻችን ናቸው። ይህ የመገዳደል አዙሪት በቃን ማለት ይገባል የሚል ከፍተኛ የሆነ ፅኑ አቋም አለን።

ይህም እስከ ግንቦት ድረስ የመሻሻል ዕድል ይኖራል የሚል ተስፋ አለኝ። ባይሆንም እንኳን ባለው ፈተና ውስጥ አልፎ መውጣት ነው እንጂ ፖለቲካ ትግል የሚባለው አበባ እየተነሰነሰ በእርሱ ላይ መራመድ አይደለም። ፈተና ሲኖር የምንወጣበት፤ ፈተና ሳይኖር ደግሞ ከፊት ለፊት የምንቀድምበት አይደለም። ይህ ነው ፖለቲካ፣ ሕዝባዊነት፣ ከሕዝብ ጋር መወገን ማለት። ስለዚህ ምንም እንኳ ችግር ቢኖርም ያን ችግር ለመጋፈጥ ዝግጁ ነን።

በቢሲ፡ ቀደም ብለው የቀድሞ የፓርቲው አመራሮች ‘በጉልበት በትጥቅም ቢሆን መንግሥትን መገልበጥ አለብን ብለው የሚያምኑ ኃይሎች ነበሩ’ ሲሉ ከሰዋል።በአማራ ክልል በሚካሄደው የትጥቅ ግጭት ውስጥ እነዚህ የቀድሞ የፓርቲው አመራሮች እጃቸው አለበት ወይም ምክንያት ናቸው ብላችሁ ታምናላችሁ?

አቶ ጋሻው፡ እሱን መንግሥት ያጣራ። እሱን አላልኩም። እሱን መንግሥት ነው ማጣራት ያለበት። እኔ ፖለቲከኛ ነኝ የፖለቲካ አስተያየት ነው የምሰጠው እንጂ ከእዚህ ታጣቂ ጀርባ እገሌ ነው የሚያደራጀው የሚል ሃሳብ የለኝም። ነገር ግን በአማራ ክልል የሚደረገው ትግል የትጥቅ ትግል ነው ብዬ አላምንም። የሻዕቢያ እና የወያኔ የውክልና ጦርነት ነው የሚል በጣም ፅኑ አቋም ነው ያለኝ።

ቢቢሲ፡ . . . እዚህ ድምዳሜ ላይ የደረሳችሁት በምን ምክንያት ነው? መንግሥት ስለሚል ነው ወይስ ተጨባጭ መረጃ አላችሁ?

አቶ ጋሻው፡ በነገርሽ ላይ ባያዝድ [ወገንተኛ] ናችሁ።

ቢቢሲ፡ ወገንተኛ አይደለንም። ጥያቄ ነው የጠየቅክዎት። ተጨባጭ መረጃ አላችሁ ወይ?

አቶ ጋሻው፡ እኔ እዚህ አገር ነው የምኖረው። የዚህችን አገር እያንዳንዷን እንቅስቃሴ የማውቅ ሰው ነኝ። ላለፉት 20 ዓመታት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ እያንዳንዱን መውጣት መውረድ ተከታትያለሁ፤ ተሳትፌያለሁ። ‘መንግሥት ስለሚል ነው ወይ?’ ብለሽ መጠየቅሽ ለእኔ ስድብ ነው። መንግሥት ሰዎች ናቸው እንደኔ።

አማራ ክልል ውስጥ በሚደረግ ውጊያ ላይ የሻዕቢያ እና የወያኔ ሰዎች ይማረካሉ። የአማራ፣ የኦሮሚያ ፣ የጋምቤላ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ እንዲሁም ሌሎችም ታጣቂዎች ኤርትራ ሄደው፤ ትግራይ ሄደው ሠልጥነው ይመጣሉ። መሳሪያ ይላካል፤ ይያዛል። እዚህ እኮ ነው ያለነው። ይህ ተጨባጭ ማስረጃ አይደለም እንዴ? ወስጄ ላሳይሽ እንዴ? የምን ተጨባጭ መረጃ ነው የምትይኝ። ቢቢሲ አማርኛ ለወያኔ የሚያደላ ሚዲያ ነው። እንዲያውም የህወሓት ሚዲያ ሴንተር ነው። እውነት እንነጋገር ከተባለ . . . [አቶ ጋሻው በቁጣ ስልካቸውን ዘግተው ቃለ መጠይቁን አቋረጡ]. . .

BBC Amharic

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚያደርጉት ድርድር እስኪጠናቀቅ ድረስ የተኩስ አቁሙ መራዘሙን አስታወቁ

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፓኪስታን ጥያቄ መሠረት ከኢራን ጋር የገቡትንየተኩስ...

ለኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ የሚውል የ40 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ ተፈቀደ

የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ የልማት ክንፍ የሆነው ኢአይቢ ግሎባል (EIB...

ሃይንከን በአልኮል መጠኑ ጠንከር ያለ ቢራ ለኢትዮጵያ ገበያ አስተዋወቀ

ሃይንከን ኢትዮጵያ በእለም አቀፍ ደረጃ ዝነኛ የሆነውን ዴሰፔራዶስ (Desperados)...