“የአልነጃሽ መስጊድ ጥገና በቱርክ መንግሥት ድጋፍ እየተጠናቀቀ ነው”
በትግራይ ክልል በነበረው ጦርነት የወደሙ ከ6 በላይ የሚሆኑ ቅርሶች የጥገና ሥራ እየተደረገላቸው መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን አስታውቋል፡፡
በባለስልጣኑ የቋሚ ቅርስ ጥበቃ ባለሞያ አቶ ገብረማርያም አናንያ፤ በክልሉ በጦርነቱ ወቅት ጉዳት የደረሰባቸው በርካታ ቅርሶች መሆናቸውን ገልጸው፤ የሠላም ስምምነቱ ከተደረገ በኋላ ቅርሶቹ ያሉበትን ሁኔታ ለማየት መቻሉን ለአሐዱ ተናግረዋል።
ይህን ተከትሎም በ2016 ዓ.ም ሁለት ቡድን በማቋቋም ጥገና የሚያስፈልጋቸውን በመለየት፤ የአክሱም ዓለም አቀፍ ቅርስን ጨምሮ በዙሪያው የሚገኙት ቅርሶች ሙሉ ጥናት እንደተደረገላቸው ጠቁመዋል፡፡
በተጨማሪም በቱርክ መንግሥት ድጋፍ ጥገና እየተደረገለት ያለው የአል ነጃሽ መስጊድ ወደ መጠናቀቁ እየቀረበ መሆኑን ባለሙያው ለአሃዱ ተናግረዋል።
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ቅርሶችን መጠበቅ፣ መንከባከብና መጠገን ዋና ተግባሩ ሲሆን፤ በዘርፉ ከሚስተዋሉ ችግሮች መካከል በሕብረተሰቡ ዘንድ በቂ ግንዛቤ አለመኖር፣ በዘርፉ በቂ የሆነ ባለሙያ አለመኖርና በሀገር ደረጃ ለጥገና ጥናት የሚያስፈልጉ መሳሪያዎች አለመኖር እንደሚጠቀሱ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
