ህዳር 12 2018
የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን በአዲስ አበባ የሚገኙ የሕግ ታራሚዎችን ከ7ኛ እስከ 12ኛ ክፍል በርቀት ለማስተማር የሚያስችለኝን ፈቃድ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትምህርትና ስልጠና ጥራት ቁጥጥር ባለስልጣን አግኝቻለሁ ሲል ተናግሯል፡፡
ማረሚያ ቤቱ ያገኘው ፈቃድ፤ የጤና እክል ላለባቸው፣ በማረሚያ ቤት ሥራ እየሰሩ ለመማር ለሚፈልጉ እና ዕድሜያቸው ከፍ በማለቱ በክፍል ወስጥ ተቀምጠው መማር ለማይፈልጉ ታራሚዎችን በርቀት ለማስተማር በእጅጉ ይረዳል ብሏል፡፡
በፌደራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የትምህርትና ስልጠና መሪ ስራ አስፈፃሚ አስመራ አብደታ፤ የተገኘው የርቀት ትምህርት ፈቃዱ በማረሚያ ቤት የሚሰጠውን የትምህርት ዕድል የሚያሰፋ ነው ብለውናል፡፡
በዚህ ፈቃድ አሁን ላይ ከ2,000 በላይ የሚሆኑ የሕግ ታራሚዎች የዕድሉ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ከኮሚሽኑ ሰምተናል፡፡
በሌሎች የፌደራል ማረሚያ ተቋማትም ማለትም በድሬዳዋ፣ በዝዋይና በሸዋ ሮቢት ማረሚያ ማዕከል የሚገኙ የሕግ ታራሚዎች የዕርቀት ትምህርት ዕድል እንዲያገኙም ከሚመለከታቸው ጋር እንደሚሰሩ አቶ አስመራ ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የርቀት ት/ት መማር የሚፈልጉና ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ ታራሚዎች ወደ አዲስ አበባ አምጥቶ የእድሉ ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱንም ሰምተናል፡፡
