በኢትዮጵያ ከግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ ፈቃድ እንጂ እውቅና ያላቸው ተቋማት አለመኖራቸውን የኢፌዲሪ ትምህርት እና ስልጠና ባለስልጣን አስታውቋል፡፡
ሁለቱን ከተማ አስተዳደሮች እና 14 ቱንም ክልሎች አጠቃሎ 375 የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ሲሆን፤ እነዚህ ተቋማት ፈቃዳቸውን ከኢፌዲሪ የትምህርት እና ስልጠና ባለስልጣን የሚወስዱ እና የሚያድሱ እንደሆነም ነው የተገለጸው።
ታዲያ እነዚህ ተቋማት የሚሰጡት ከዲግሪ ጀምሮ ያለው የትምህርት ደረጃ፤ በዓለም አቀፍ እውቅና ያለው እና በተማሩበት የትምህርት ዘርፍ የትኛውም ሀገር ላይ ሄደው ድጋሚ የሄዱበትን ሀገር ትምህርት መማር ሳያስፈልጋቸው መስራት የሚያስችል አይደለም።
“ይህ ለምን ሆነ?፣ ተቋማቱን ዓለም አቀፋዊ እውቅና እንዲኖራቸው እና በእነዚህ ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎችም በዓለማቀፍ ደረጃ ተስተካካይ እንኳን ባይሆን ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችል የትምህርት ደረጃ እንዲኖራቸው ማድረግ ለምን አልተቻልም?” ሲል አሐዱ ጠይቋል።
የኢፌዲሪ ትምህርት እና ስልጠና ባለስልጣን የተቋማት ቁጥጥር ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ቢኒያም ኤሮ በሰጡት ምላሽም፤ ይህን እውቅና ለመስጠት በመጀመሪያ ተቋሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ሊያገኝ እንደሚገባው ገልጸው፤ እስካሁን ግን እውቅናውን አለማግኘቱን ተናግረዋል።
“በዚህ ምክንያት በኢትዮጵያ የሚገኙ ሁሉም የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ፈቃድ እንጂ እውቅና ገና ያልተሰጣቸው ናቸው” ብለዋል።
ተቋሙም ከዓለም አቀፍ ደረጃ ሰጭ ተቋም ማለትም (አይሶ) ገና እውቅና እንዳልተሰጠውም ተናግረዋል። እሱን ለማድረግ እና እውቅና ያላቸው የትምህርት ተቋማትን ለማፍራት ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ተናግረዋል።
አሁን ላይ ተቋሙ የግልም የመንግሥትም ትምህርት ተቋማትን በአንድ ለመቆጣጠር የሚያስችለውን ሥራ እየሰራ መሆኑም ነው የተገለጸው። (አሐዱ ሬዲዮ)
