ቡና ባንክ ከትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በማንኛውም አይነት ሞባይል ስልክ እንዲሁም በኢንተርኔት ወይንም ያለኢንተርኔት በመላው ኢትዮጵያ ለሚገኙ ሁሉም ደንበኞች ተደራሽ መሆን የሚያስችል፤ የዲጂታል ነዳጅ ክፍያ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን በዛሬው ዕለት አስታውቋል፡፡
ከትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተቀረጸው አገልግሎቱ ከብሔራዊ የነዳጅ ስርጭት መከታተያ ስርዓት ጋር በመቀናጀት በአገር አቀፍ ደረጃ የነዳጅ አቅርቦት ሰንሰለትን ለማሻሻል የሚያስችል የክፍያ አማራጭ ነው ተብሏል።
በየጊዜው ተለዋዋጭና ፈጣን ለሆነው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ፍላጎት ምላሽ በመስጠት የቀረበ አገልግሎት መሆኑን ባንኩ አስታውቋል።
ይህም አገልግሎት ጥሬ ገንዘብ ከመያዝ ጋር የተያያዙ ስጋቶች፣ ግልጽ ያልሆነ ግብይት እና በነዳጅ ማደያዎች ውስጥ የሚስተዋሉ ረጃጅም ወረፋዎችን የመሳሰሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችን ማገዝ እንደሚያስችል ተገልጿል።
ስለሆነም ደንበኞች ቡና ባንክን ተጠቅመው የነዳጅ ግዢን መፈጸም የሚችሉት፤ ከነዳጅ ማደያዉ *820# በመጠቀም ስልካቸው ላይ በሚደርሳቸው የማረጋገጫ መልእክት፣ “አቦል የሞባይል ባንኪንግ” መተግበሪያ ውስጥ በመግባት QR ኮድን ተጠቅመው ስካን በማድረግ ወይም በነዳጅ ማደያው የቀረበውን የማጣቀሻ ቁጥር በመጠቀም ነው ተብሏል።
ባንኩ በተወሰኑ የተመረጡ የነዳጅ ማደያዎች የጀመረውን ይህን አገልግሎት በመላ ሀገሪቱ ከሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ጋር በመተባበር ለማስፋፋት ማቀዱን የገለጸ ሲሆን፤ አገልግሎቱ በሙከራ ላይ በዋለበት ጊዜ ከ12 ሚሊየን ብር በላይ በዲጂታል መዘዋወሩን አስታውቋል።
አሐዱ ሬዲዮ
