የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ለቀረበባቸው የሙስና ክስ የይቅርታ ጥያቄያቸውን ለሐገሪቱ ፕረዚደንት አቀረቡ። ኔታንያሁ ለፕሬዚደንቱ ያቀረቡት የይቅርታ ጥያቄ በእሳቸው ላይ የተመሰረተውን የሙስና ወንጀል ክስ እንዲሰረዝላቸው ነው።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅሕፈት ቤት እንዳስታወቀው በቤንጃሚን ኔታንያሁ የተመሰረተው የሙስና ክስ ሐገሪቱን ክፉኛ መከፋፈሉንና ረዥም ጊዜ የወሰደው የክስ ሂደት ዶሴ መዘጋቱ ለሐገሪቱ ብሔራዊ አንድነት እንደሚጠቅም ገልጿል።
የአሜሪካው ፕረዚደንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤልን በጎበኙበት ወቅት የእስራኤል ፕረዚደንት አይዛቅ ሔርዞግ ለኔታንያሁ ምህረት እንዲያደርጉ ጠይቀው ነበረ። ከሳምንታት በፊትም ትራምፕ ለእስራኤል ፕረዚደንት በላኩት ደብዳቤ ይህን ጥያቄያቸውን በድጋሚ አቅርበዋል።
የኔታንያሁ የይቅርታ ጥያቄ ግን ከሐገሪቱ ተቃዋሚዎች ብርቱ ነቀፌታን አስከትሏል። ጥያቄው የሐገሪቱን የዴሞክራሲ ተቋማትን የሚያዳክምና እሳቸው ከሐግ በላይ መሆናቸውን የሚያሳይ አደገኛ መልእክት የሚያስተላልፍ ነው የሚል ትችት ተቃዋሚዎች ሰንዝረዋል።
DW Amharic
