የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የ2027 የአፍሪካ ዋንጫ ቅድመ ማጣርያ ጨዋታውን ከሳኦቶሜ እና ፕሪንሲፔ ጋር በመጋቢት ወር ያደርጋል። ይህን ጨዋታ በአሸናፊነት በመወጣት ወደ ምድብ ማጣርያ ለመሸጋገር ያለመ ቅድመ ዝግጅትም እየተደረገ ይገኛል።
ስኬታማ ብሔራዊ ቡድን ለመገንባት የክለቦች እና ብሔራዊ ቡድኑ ቅንጅት ወሳኝ በመሆኑ ተጫዋቾች በአካል ብቃትም ሆነ በስነ ልቦና ዝግጁ ሆነው በሚቀርቡበት ሁኔታ ዙርያ ከፕሪምየር ሊጉ ክለቦች ዋና አሰልጣኞች ጋር የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ዛሬ የተከናወነ ሲሆን ጥሪ ከተደረገላቸው የሃያው ክለብ አሰልጣኞች አምስቱ ብቻ ተገኝተዋል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ መሪነት በተካሄደው ውይይት የተጫዋቾች ጥሪ፣ የዝግጅት ሂደት እና በጨዋታው ትኩረት ሊሰጥባቸው የሚገባቸው ጉዳዮች ላይ ሀሳቦች ተነስተው ውይይት ተካሂዶባቸዋል።
በዛሬው ውይይት ላይ በጸሎት ልዑልሰገድ (ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ)፣ ደግአረገ ይግዛው (ባህር ዳር ከተማ)፣ ጸጋዬ ኪዳነማርያም (መቐለ 70 እንደርታ)፣ ይታገሱ እንዳለ (ድሬዳዋ ከተማ)፣ ዳንኤል ጸሐየ (ምድረገነት ሽረ) በውይይቱ ላይ የተገኙ አሰልጣኞች ሲሆኑ ፌዴሬሽናችንም በዚህ መድረክ ላይ በመገኘት ለብሔራዊ ቡድናችን ግብአት የሚሆን ሀሳብ በማንሸራሸራቸው ምስጋናውን ያቀርባል።
