ኢትዮ ቴሌኮም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ከፍትህ ሚኒስቴር እና ከፌደራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ጋር በመተባበር ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ድንበር ተሻጋሪ እና ዜጋ-ተኮር አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችል ብሄራዊ የዲጂታል ፊርማ ወይም ” ቴሌሳይን” የተሰኘ አገልግሎትን በይፋ አስጀምሯል።
የኢትዮቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ፥ የዲጂታል ፊርማ አገልግሎቱ፥ ከመንግስት ተቋማት ጋር የሚደረጉ ግንኙነቶችን በዲጂታል መንገድ በማሳለጥ ለዜጎች አስተማማኝ፣ ተደራሽነት እና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ሰው ተኮር አገልግሎት ነው ብለዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያን ግስጋሴ ለሚያፋጠን እየተከናወኑ ባሉ ተግባራት ተቋማትን በዲጂታል በማስተሳሰር ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት ትልቅ ሚና ያጫወታልም ብለዋል።
በመድረኩ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርሀኑ ጸጋዬ ባደረጉት ንግግር፥ የውክልናና የሰነድ ማረጋገጥ ለሀገር ኢኮኖሚ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፥ አገልግሎቱ ዜጋ ተኮር የመንግስት አገልግሎትን የሚያዘምንና የሚያቀላጥፍ መሆኑን ተናግረዋል።
በዲጂታል የተሳሰረ አገልግሎት በመሆኑ በሂደቱ ሊከሰቱ የሚችሉ መጭበርበሮችን የሚያስቀር ይሆናልም ብለዋል።
”የቴሌ ሳይን” አገልግሎት ከዓለማቀፍ ህጎች ጋር የተጣጣመ መሆኑም የተገለጸ ሲሆን፥ በውጪ አገር የሚገኙ ዜጎች ጭምር ባሉበት ሆነው መጠቀም የሚችሉት እንደሆነም ተመላክቷል።
