ትጥቅ ፈቱ የተባሉ ታጣቂዎች ቁጥር ላይ ባለስልጣናት የሰጡት መረጃ የተለያየ ነዉ

Date:

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን “የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ትጥቃቸውን የፈቱ ታጣቂዎችን” አስመልክቶ በሁለት ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች በአንድ ቀን ውስጥ የወጡ የቁጥር መረጃዎች በእጅጉ የሚቃረኑ መሆናቸውን በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ በመጠቆም ትችት ሰነዘሩ።

በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ባሳለፍነው ሐምሌ ወር ብቻ ከ3ሺህ 100 በላይ ታጣቂዎች “የመንግስትን የሰላም ጥሪ ተቀብለው ትጥቃቸውን በመፍታት ወደ ህብረተሰቡ መቀላቀላቸውን” የዞኑ ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ሃላፊ የሆኑት ይደሰቱ ክፈተው ነሐሴ 7 ቀን 2017 ዓ.ም ገልጸው ነበረ።

አዲስ ስታንዳርድ ትጥቅ አስረከቡ የተባሉት ታጣቂዎች “የመንግስትና የሕዝብ ተቋማትን በማውደም፣ መንገድ በመዝጋት፣ ህጻናት እንዳይማሩ በማድረግ፣ እናቶች በጤና ተቋም እንዳይወልዱና ሕብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዳያገኝ ለፈጠሩት ችግር በመጸጸት በስራ ለመካስ መዘጋጀታቸውን” የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።

በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ኮሚኒኬሽን ቢሮ በተመሳሳይ የዞኑ ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ሃላፊ የሆኑት ይደሰቱ ክፈተው ለኢዜአ የሰጡትን ቃለመጠየቅ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ አሰራጭቶታል።

የኮሚዩኒኬሽን ቢሮው በተመሳሳይ ቀን የሰሜን ሸዋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሆኑትን አቶ ኤልያስ አበበን በመጥቀስ ትጥቅ ፈቱ የተባሉ ታጣቂዎችን ቁጥር አስመልክቶ አስቀድሞ በዞኑ ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ሃላፊ ይደሰቱ ክፈተው ከተገጸው ቁጥር በእጅጉ የሚያንስ አሃዛዊ መረጃን አቅርቧል።

የሰሜን ሸዋ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኤልያስ አበበ ከሐምሌ ወር 2017 ዓ.ም ጀምሮ “ከ1,300 በላይ ታጣቂዎች” በሃይማኖት አባቶች፣ በሀገር ሽማግሌዎች እና በፀጥታ ኃይሎች ጥረት ትጥቅ መፍታታቸውን ተናግረዋል።

የፓርላማ አባሉ ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) በሁለቱ የስራ ሃላፊዎች የተገለጹትን መረጃዎች አሃዛዊ ልዩነት በመጥቀስ “ከአዲስ አበባ የመርካቶ ነጋዴ” ጋር አነጻጽረውታል።


“አቶ ይደሰቱ እና አቶ ኤልያስ በአንድ ዞን ውስጥ የካቢኔ አባላት ናቸው” ያሉት የፓርላማ አባሉ “የሚጠሩት ቁጥር ግን ልክ መርካቶ በቫት እና ያለ ቫት ዋጋ እንደሚጠራው ነጋዴ ይመስላል። የአቶ ይደሰቱ በቫት፣ የአቶ ኤልያስ ያለቫት ነው?” ብለዋል።


ቀጠል አድርገውም “በዚች አገር ውስጥ በተፈጠረው ማባሪያ የሌለው የርስ በርስ ጦርነት፣ ግጭቶች እና መፈናቃሎች፣ ቅጥ ያጣው የኑሮ ውድነት ህይዎቱን ላመሰቃቀለው የዞኑም ሆነ የክልሉ ህዝብ ብሎም ለመላው ኢትዮጵያዊ ሠላም እንደ ሰማይ ርቆታል፣ እውነተኛ ሠላም ቢመጣ የሚጠላ አይኖርም” ሲሉ ገልጸው ነገር ግን መሰል አሃዛዊ መረጃዎች ሲነገሩ ቢያንስ በመንግስት የስራ ሀላፊዎች መካከል መነጋገር ይኑር ብለዋል።


አክለውም “እንደዚህ ያሉ እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ቁጥሮችን በሠላሳ ደቂቃ ልዩነት ውስጥ መጥቀስ አጠያያቂ ነው” ብለዋል።


የመከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በሰኔ ወር 2017 ዓ.ም ላይ “በአማራ ክልል 90 በመቶ የሚሆነው  ኦፕሬሽን ተጠናቋል ቀሪው 10 በመቶ ደግሞ ክልሉን ከታጣቂ ቡድኖች ነጻ ለማውጣት በመካሄድ ላይ ነው” ሲሉ ለፓርላማ አባላት መናገራቸው አይዘነጋም።


ይሁን እንጂ የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ከሰሞኑ በክልሉ የተለያዩ አከባቢዎች ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች “የሰላም ጥሪውን ተቀብለው ወደ ማህበረሰባቸው እየተቀላቀሉ መሆናቸውን” በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል።


ይህ በእንዲህ እንዳለ የብሄራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ማክሰኞ ነሐሴ 6 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ከህዳር ወር 2017 ዓ.ም አንስቶ እስከአሁን ድረስ ከ65 ሺህ 500 በላይ የቀድሞ ተዋጊዎችን በተሃድሶ ሂደት በማሳለፍ ወደ ማህበረሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረጉን አስታውቆ ከእነዚህም ውስጥ 5 ሺህ 168 የሚሆኑት ከአማራ ክልል ናቸው ብሏል። 

አዲስ ስታንዳርድ 

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

የእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ፣ የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አካልና የመንፈስ...

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ የአጼ ቴዎድሮስ የፀጉር ቁንዳል እና...

ፈረንሳይ የ54 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ለመስጠት ተስማምታለች

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ሀገራቸው ለኢትዮጵያ የኃይል...

ትራምፕ ኢራን ላይ ያላቸው ትዕግሥት እየተሟጠጠ መሆኑን ተናገሩ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ ጋር...