ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ወይም ሰው ሰራሽ እጥረት ለመፍጠር ምርት የሚሰውሩ እና አላግባብ የሚያከማቹ ሕገ-ወጥ ነጋዴዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የንግድ እና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር አሳሰበ፡፡
ሚኒስቴሩ ይህንን ማሳሰቢያ ያወጣው ከመስከረም 2018 ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረገውን የደሞዝ ማሻሻያ አስመልክቶ ነው፡፡
” ከዚህ በፊት ካለው ልምድ ለመገንዘብ እንደሚቻለው አብዛኛው የንግዱ ማህበረሰብ ሕግና ስርዓትን ጠብቆ የሚሠራ መሆኑ የሚያስመሰግን ቢሆንም የተወሰኑ በአፍቅሮተ-ነዋይ የታወሩ ነጋዴዎች ለሠራተኛው ኑሮ ማሻሻያ የሚደረገውን የደሞዝ ጭማሪ ምክንያት በማድረግ ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት መሯሯጥ ተስተውለዋል” ሲል ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
በዚህም በየደረጃው የሚገኝ የንግድ መዋቅር ከሚመለከታቸው የፍትህ እና ፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የተጠናከረ የገበያ ማረጋጋት፣ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ በማጠናከር በአጥፊዎች ላይ አስተማሪ እርምጃ እየተወሰደ የግብይት ሂደቱ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲቀጥል እናደርጋለን ሲል መስሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡
