ዶሜይን 2024/11/09
ሆስቲንግ 2024/09/17
ኤክስፓየር ያረጋሉ
በአዲስ አበባ ከተማ በሚከሰቱ ድንገተኛ አደጋዎች ምክንያት የሚፈጠሩ የሞት አደጋዎችን ለመቀነስ አገልግሎት ላይ የሚውሉት የታካሚዎች ማመላለሻ ተሽከርካሪ (አምቡላንሶች) በአገልግሎት ርዝማኔ ምክንያት ማርጀታቸው፤ የአገልግሎት ጥራቱ ላይ ችግር እየፈጠረበት እንደሚገኝ የከተማ አስተዳደሩ የእሳት እና አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።
የኮሚሽኑ የድንገተኛ አደጋዎችና የአደጋ ሠራተኞች ሕክምና ዳይሬክተር አቶ ኡመር አቡዱልአዚቅ ከአሐዱ ሁሉ ደህና ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በተቋሙ ውስጥ የሚገኙት አንቡላንሶች ከ10 ዓመት በላይ ያገለገሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከ2006 ዓ.ም. በኋላ አዳዲስ አምፑላንሶች እንዳልገቡ ያስታወሱት ኃላፊው፤ ጤና ሚኒስቴር ለተቋማት አምቡላንሶች ሲያሰራጭ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ያቀረቡት ጥያቄም ተግባራዊ እንዳልተደረገ ገልጸዋል።
ተቋሙ የገጠመውን የአምቡላንስ ችግር ለመፍታት፤ ከዚህኛው ዓመት በጀቱ ላይ አዳዲስ ተሽከርካሪዎችን ለመግዛት ጥረት እያደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም፤ የከተማ አስተዳደሩ ጥቅም ላይ የማይውሉ አምቡላንሶች ካሉት ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።
በድንገተኛ አደጋ ምክንያት የተጎዱ ሰዎችን ለመርዳት ባለድርሻ አካላት ግዴታቸውን በሚገባ ባለመረዳታቸው፤ በጤና ተቋማት ላይ ጫና እየተፈጠረ ስለመሆኑም ተናግረዋል።
በተጨማሪም ተቋሙ ያለበትን የሰው ኃይል እጥረት ለመፍታት ከፐብሊክ ሰርቪስ ጋር በመተባበር የማሟላት እና የማደራጀት ሥራ እየተሰራ ነው ተብሏል።
11 የአደጋ ስጋት ተቋማት ያሏት አዲስ አበባ ከተማ ከ20 በላይ የአደጋ ስጋት ተቋማት እንደሚያስፈልጓት በጥናት መለየቱን፤ የኮሚሽኑ የድንገተኛ አደጋዎችና የአደጋ ሠራተኞች ሕክምና ዳይሬክተር አቶ ዑመር ለአሐዱ ገልጸዋል።
(አሐዱ ሬዲዮ)
