ለ11 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነውን የቅዳሜ ዕለት የእስራኤል ጥቃት “አደገኛ የውጥረት መባባስ” ሲል የጠራው አረብ ሊግ፣ አገሪቱ በደቡባዊ ሊባኖስ የምታደርሰው ጥቃት መቀጠሉን አወገዘ።
የአረብ ሊግ ቃል አቀባይ ባወጡት መግለጫ፣ ከቅዳሜ ጠዋት ጀምሮ የተፈጸሙት የእስራኤል ጥቃቶች “የሊባኖስን ሉዓላዊነት በግልጽ የጣሱ” መሆናቸውን አስታውቀዋል። “እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለመፍታት እና ወረራውን ለመቋጨት የሚደረጉ ማናቸውም ጥረቶች ስጋት ላይ የሚጥል አደገኛ የውጥረት መባባስ ነው” ብለዋል።
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው፤ የእስራኤል ፖሊሲዎች እና እርምጃዎች “ወራሪው አካል ግጭቱን ለማራዘም፣ ድርድሮችን ለማሰናከል እና መሬት ላይ አዲስ እውነታን ለመጫን ያለውን ፍላጎት በግልጽ የሚያሳዩ ናቸው” ሲሉ ወቅሰዋል።
የእስራኤል እርምጃ “ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት እንደሌለው እና ውድቅ” መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ በተለይም አሜሪካ የእስራኤልን “የጦርነት ማሽን” እስካላስቆሙ እንዲሁም አገሪቱ ለተመድ የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔ እንድትገዛ ካላስገደዱ በስተቀር፣ ግጭቱ ሊስፋፋ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
በአውሮፓውያኑ 2006 የጸደቀው ይህ ውሳኔ፣ በእስራኤል እና ሄዝቦላህ መከካል ሙሉ ግጭት ማቆም እንዲደረግ የሚጠይቅ ነው።
እስራኤል ትናንት በደቡባዊ ሊባኖስ በፈጸመችው ጥቃት ሦስት ሕፃናትን ጨምሮ 11 ሰዎች መገደላቸውን የሊባኖስ ባለሥልጣናት ተናግረዋል። ከዚህ ጥቃት በኋላ በርካታ ነዋሪዎች ከደቡባዊ ሊባኖስ መሸሽ ጀምረዋል።
