መዲናይቱ ለጎርፍ ፥ መሬት መንሸራተት ፥ የህንፃ መደርመስ እና እሳት ላሉ የአደጋ ክስተቶች ተጋላጭ መሆኗን ጥናት አሳይቷል።
በአዲስአበባ እሳት እና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮምሽን የአደጋ ቅነሳ ዘርፍ ሀላፊ የሆኑት አቶ ደሳለኝ ቱፋ የከተማዋን የአደጋ ስጋት በተመለከተ በኮተቤ ዩንቨርስቲ ጥናት መደረጉን ይገልፃሉ።
ሃላፊዉ ይህ ጥናት እንደገለፀዉ ከሆነም አዲስ አበባ አስር ለሚደርሱ የተፈጥሮ እና ሰዉሰራሽ የአደጋ ክስተቶች ተጋላጭ መሆኗን ጠቁሟል ብለዋል።
ከተማዋ በዋነኝነት ለጎርፍ ተጋላጭ መሆኗን የሚገልጹት ሀላፊዉ በመጪዉ የክረምት ወራት ዉስጥ ኮምሽኑ ተጋላጭ ቦታዎችን መለየቱን ተናግረዋል።
2 መቶ 38 አካባቢዎች ለጎርፍ እና ለመሬት መንሸራተት ተጋላጭ እንደሆኑ ተለይተዋል ያሉት አቶ ደሳለኝ ቱፋ 98 የሚሆኑን አካባቢዎች ለቅድመ አደጋ መከላከል ስራ እንዲሰራባቸዉ ለባለድርሻ አካላት ከምክረ ሀሳብ ጋር ተላልፎል ብለዋል።
የመሬት መንሸራተት ስጋት በታየባቸዉ አካባቢዎች እርምጃዎች እየወሰድን ነዉ የሚሉት ሀላፊዉ የጎርፍ ስጋት የሚያስከትሉ ክስተቶችን ለማስወገድ እየተሰራ ነዉ ይላሉ።
ከተማ አስተዳደሩበአዲስ አበባ በመጪው የክረምት ወቅት ጎርፍ ቢያጋጥም ክፍለ ከተሞች ተጠያቂ እንደሚሆኑ መነገሩ ይታወሳል።
በቅርቡ በተካሄዱት የኮሪደር ልማት ስራዎች ወቅት ሳይታዩ የታለፉ ወይም የተዘጉ የጎርፍ መውረጃዎች ካሉ፣ ክረምቱ ከመግባቱ በፊት በፍጥነት መለየትና ምላሽ መስጠት እንደሚገባ ማሳሰቢያም ተሰጥቷል
በዛሬዉ እለት የ2018 የበጀት አመት የስራ አፈፃፀም ሪፖርቱን የአዲስ አበባ የእሳት እና አደጋ ስጋት አመራር ኮምሽን አቅርቧል።
