ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መልሰው ከኢራን ጋር ጦርነት የሚገቡ ከሆነ ኢራን፣ አውሮፓ ውስጥ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋማትን እንደምትመታ መዘገቡን ተከትሎ ኔቶ ምላሽ ሰጠ።
ጋብ ያለው ጦርነት ከተባባሰ ኢራን በአውሮፓ ውስጥ ያሉ የአሜሪካ ወታደራዊ ዒላማዎችን ልትመታ እንደምትችል ፋይናንሻል ታይምስ የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል።
አሜሪካ ዋነኛ አባል የሆነችበት የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን አገራት ማኅበር (ኔቶ) አንድ ባለሥልጣን ለዚህ ዛቻ በሰጡት ምላሽ፣ ድርጅቱ የትኛውንም ስጋት ለመጋፈጥ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል። ሁሉንም አጋሮቹን ለመከላከል አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።
ስማቸው ያልተጠቀሰው የኔቶ ባለሥልጣን “የኔቶ የአየር መከላያ ሥርዓት ከዚህ ቀደም ኢራን በተለያዩ ጊዜያት ወደ ቱርክ ሚሳዔሎችን ባስወነጨፈችበት ጊዜ በተሳካ ሁኔታ ጥቃቱን መከላከሉን” አስታውሰው፤ “ጥቃቶችን የማስቀረት እና የመከላከል አቋማችን ጠንካራ እና ውጤታማ ነው” ብለዋል።
ፋይናንሻል ታይምስ ጋዜጣ ለኢራን መንግሥት ቅርብ የሆኑ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው ትራምፕ ጦርነቱን የሚቀጥሉ ከሆነ “ኢራን በጦርነቱ የሚፈጠረውን ጫና ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ አማራጮችን እየፈተሸች” እና በአውሮፓ ያሉ የአሜሪካ ወታደራዊ ተቋማትን ዒላማ ለማድረግ እያጤነች ነው።
የኢራን ኃይሎች ባለፈው ወር የአሜሪካ አውሮፕላኖች ከአየር ኃይል ሰፈራቸው ነዳጅ እንዲሞሉ ፈቃድ እንደሰጠችው ቤልጂየም ባሉ የደቡባዊ የአውሮፓ አገራት የሚገኙ የአሜሪካ ወደታራዊ ተቋማትን እየገመገሙ መሆኑን የጋዜጣው ምንጮች ገልጸዋል።
BBC
