የፓን አፍሪካ የንግድ ኢንዱስትሪ ም/ቤት እና የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የፊታችን ሐምሌ 18 እና 19 ቀን 2015 ዓ.ም ለመንግሥትና ለግሉ ዘርፍ ሀገራዊ የምክክር መድረክ አዘጋጅተዋል፡፡ የምክክር መድረኩ የሚካሄደው በንግዱ ማኅበረሰብና በመንግሥት በኩል ሲኾን ቦታውም ስካይ ላይት ሆቴል ነው፡፡ በመድረኩ ላይ ከመንግሥት በኩል ይሳተፋሉ ተብሎ የሚገመቱት በርካታ አካላት የሚኖሩ ሲኾን በተለይ በአግሮ ኢንዱስትሪ ዘርፍ፣ በቱሪዝም ዘርፍና በዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ የሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናት ይገኛሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ ይኽ ጽሑፍም ለመድረኩ በግብአትነት የሚቀርብ ሲኾን፣ በቀጣይ ደግሞ በኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች ማቀነባበርያ ዘርፍ እንቅፋቶች ዙሪያ እንዲሁም ቱሪዝም በኢትዮጵያ ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ የሚያትቱ የፖሊሲ ሐሳቦችን ይዘን የምንቀርብ ይኾናል፡፡
I. ዳራ እና ነባራዊ ሁኔታ
እንደ አጠቃላይ በኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ልማትና ተጠቃሚነት ላይ የመሪነቱን ድርሻ መያዝ ያለበት የግሉ ዘርፍ ነው ተብሎ ቢታመንም፣ መንግስትም ለኤሌክትሮኒክ ግብይት መሰረት በመጣል እንዲሁም አመቺ የፖሊሲ ከባቢ በመፍጠር፣ መሰረተ ልማት በመዘርጋት፣ ፋይናንስ በማቅረብ፣ የግብይቱ መሪ ተጠቃሚ በመሆንና በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውል በማበረታታት በዘርፉ የተሰማሩ የንግድ ተቋማትን ለመደገፍ ተጨባጭ እርምጃዎችን በመውሰድ ቁልፍ ሚና መጫወት ይኖርበታል፡፡ ለዚህም ሲባል መንግስት ከግሉ ዘርፍ ተዋንያን ጋር በመቀናጀት ተገቢነት ያለው ብሔራዊ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ስትራቴጂ ለመቅረጽ በትኩረት መስራት ይጠበቅበታል፡፡
የሚቀረጸው ስትራቴጂም የአገሪቱን ዲጂታል ፖሊሲ ተመተንተን የሚያግዝ እንዲሁም በሁሉም ደረጃዎች ከሚከናወኑ የንግድ ልማት ጥረቶች ጋር የሚናበብ መሆን ይኖርበታል፡፡
የኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክ ግብይት ገበያ ቅኝት
የኢትዮጵያ የወጪና ገቢ ንግድ ሚዛን ባለፉት 10 አመታት ጉድለት ያስተናገደ ሲሆን፣ አጠቃላይ የገቢ ንግዱ በየአመቱ በአማካይ በ12.5% ዕድገት ማሳየቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የንግድ ሚዛን ጉድለቱን ያሳደገው የገቢ ንግድ እያደገ መምጣቱ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ በ2010 ላይ 4.8 ቢሊዮን ዶላር የነበረው የንግድ ጉድለት በከፍተኛ ሁኔታ አድጎ በ2015 ላይ 14.4 ቢሊዮን ዶላር በመድረስ በአገሪቱ የንግድ ጉድለት ታሪክ ከፍተኛው ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ የንግድ ጉድለቱ በ2020/21 ወደ 10.6 ቢሊዮን ዶላር ሊጠብብ መቻሉንም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አመታዊ ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ከአጠቃላዩ የገቢ ንግድ ወጪ 27.2% ያህሉ (3.9 ቢሊዮን ዶላር) ለካፒታል ዕቃዎች የዋለ ሲሆን 38.3% ያህሉ (5.4 ቢሊዮን ዶላር) ደግሞ ለፍጆታ ዕቃዎች የዋለ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለዲጂታል ኢኮኖሚ አዲስ ወይም ጀማሪ እንደመሆኗ ዲጂታል ንግድን የምትቆጣጠርበት ስርዓት ራሱን ችሎ በተደራጀ ሁኔታ ያልተቀረጸ ሲሆን፣ በስራ ላይ የዋሉ ህጎችም ዘርፉ የሚነሱ ጉዳዮችን በሚገባ ተደራሽ ማድረግ የማይችሉ ናቸው፡፡ መንግስት ይህንን ክፍተት በማጤን አዳዲስ የዲጂታል ፋይናንስ፣ ኤሌክትሮኒክ የገንዘብ ዝውውር፣ ዲጂታል መለያ፣ የኮሙኑኬሽን አገልግሎቶችና የሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ህጎችን በማውጣት ላይ ይገኛል፡፡ ያም ሆኖ ግን፣ ዲጂታል ንግድን ለመቆጣጠር ታስበው የሚወጡ የፖሊሲ ማስፈጸሚያዎች በአንድ በኩል በግሉ ዘርፍ የሚመራ ነጻ ንግድን ማስፋፋትና አካባቢያዊ ትስስር መፍጠርን፤ በሌላ በኩል ደግሞ የህዝብን ፍላጎትና ብሄራዊ ጥቅምን ማስጠበቅን በሚዛናዊነት ከማስኬድ ጋር በተያያዘ ፈተናዎች ሲገጥሟቸው ማየት የተለመደ ክስተት ነው፡፡
የኤሌክትሮኒክ ግብይት ለኢኮኖሚውና ለማህበረሰቡ ያለው ጠቀሜታ
ከባለ ብዙ ድርሻና አካባቢያዊ የነጻ ንግድ ስምምነቶች ተሳትፎ አንጻር ሲታይ፣ ኢትዮጵያ ከተቀረው አለም ተገልላ የኖረች አገር ናት፡፡ አገሪቱ የአለም የንግድ ድርጅት (WTO) ወይም የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብን (EAC) የመሳሰሉ ሌሎች አካባቢያዊ ነጻ የንግድ ማዕቀፎች ወይም አደረጃጀቶች አባል አይደለችም፡፡ እርግጥ አገሪቱ አባል የሆነችበት ብቸኛ የባለ ብዙ ድርሻ የነጻ ንግድ ማዕቀፍ ቢኖር፣ አዲስ የተቋቋመው የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና (AfCFTA) ነው፡፡ አገሪቱ የዋና ዋናዎቹ አለማቀፍ የንግድ፣ ኢንቨስትመንትና የአእምሯዊ ንብረት ስምምነቶች ፈራሚም አይደለችም፡፡ በመሆኑም የዲጂታል ንግዱ የቁጥጥር ስርዓትና ከባቢ እንቅፋቶች ያሉበትና ከሞላ ጎደል ለንግድ ተቋማት የማያመች መሆኑ የሚጠበቅ ነው፡፡
የኤሌክትሮኒክ ግብይት ለኢትዮጵያ ከሚያስገኛቸው ቁልፍ ጥቅሞች መካከልም ውጤታማ የንግድ መስተጋብር የሚያስገኛቸው ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች፣ ግልጽነት በተሞላባቸው የንግድ መስተጋብሮች አማካይነት ሙስናን መዋጋት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን መሳብና በአግባቡ ማስተዳደር ይጠቀሳሉ፡፡
የፖሊሲ ፍሬ ኃሳቡ ወሰን፣ ጥቅምና ዓላማዎች
ደንብና መመሪያዎች ከሚገባው በላይ ጥብቅ ከሆኑ ነጻ ንግድንና ፈጠራን የመወሰን፣ አካባቢያዊ ትስስርን የመገደብ እንዲሁም በተለይ የቴክኖሎጂ ሃሳብ አፍላቂዎችንና ስራ ፈጣሪዎችን ዕድገት የማደናቀፍ ተጽዕኖ ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፤ በእጅጉ የላላ ወይም ቁጥጥር የማይደረግበት የዘፈቀደ ዲጂታል ንግድም ሚስጥራዊነትና የአእምሮአዊ ንብረቶች መብቶችን ለመሳሰሉ መሰረታዊ መብቶች ጥሰት፣ ለሸማቾች ብዝበዛ፣ ለተለያዩ የወንጀል ድርጊቶች መስፋፋት በር ሊከፍት እንዲሁም በገበያው ውስጥ ፍትሃዊ ውድድር እንዳይኖር ሊያደርግ ይችላል፡፡
የዚህ የፖሊሲ ፍሬ ኃሳብ ወሰን አገሪቱ ከአካባቢያዊና አለማቀፍ ንግድና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች በሚገባ ተጠቃሚ ለመሆን ልትወስዳቸው የሚገቡ ወሳኝ የፖሊሲና የስትራቴጂ እርምጃዎችን ማመላከት ነው፡፡
II. የኤሌክትሮኒክ ግብይት ወቅታዊ ሁኔታ በኢትዮጵያ
የገበያ ቅኝት
የኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክ ግብይት የሚገኝበት ሁኔታ፣ ከአጠቃላዩ የአገሪቱ ዲጂታል ኢኮኖሚ ንግድ ሁኔታ ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነው፡፡ ዲጂታል ኢኮኖሚው የበለጠ ባደገ ቁጥር፣ ኤሌክትሮኒክ ግብይቱም ጠንካራ ይሆናል፡፡ ይህም በመሆኑ፣ የኤሌክትሮኒክ ግብይት በኢትዮጵያ የሚገኝበት ወቅታዊ ሁኔታ ለመፈተሽ፣ የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎችን፣ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችንና የግዢ ፈጻሚዎችን ቁጥር መመልከት እንዲሁም የኢንተርኔት አገልግሎት ሽፋን እና በኤሌክትሮኒክ የገንዘብ ዝውውሮች የሚከናወነውን ሽያጭ መጠንን ወዘተ መቃኘት ይኖርብናል፡፡ በተለያዩ የዕቃዎች መደቦች ውስጥ ከሚፈጸመው አጠቃላይ ንግድ ውስጥ የኤሌክትሮኒክ ግብይት የሚይዘውን ድርሻ መገምገም ግብይቱ የሚገኝበትን ሁኔታና ደረጃ ከሞላ ጎደል ይጠቁማል፡፡ ችግሩ ግን፤ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ከላይ የጠቀስናቸውን መረጃዎች ለማግኘት አይቻልም፡፡ በመሆኑም ከዚህ ይልቅ ከተለያዩ ዘርፎች የተገኙ የተለያዩ መረጃዎችን በመጠቀም የኤሌክትሮኒክ ግብይት በኢትዮጵያ የሚገኝበትን ሁኔታ የማመላከት አማራጭ ጥቅም ላይ ሲውል ቆይቷል፡፡
ዋና ዋና ተዋንያን፣ የገበያ መዋቅርና አዝማሚያዎች
የሞባይል ስልክ ተጠቃሚነት በኢትዮጵያ – 2022
በኢትዮጵያ የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥር እ.ኤ.አ በ2022 መጀመሪያ ላይ 58.54 ሚሊዮን ደርሶ እንደነበር ጂኤስኤምኤ ኢንተለጀንስ (1) /GSMA Intelligence/ የተባለ ተቋም ያወጣው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ከአንድ በላይ የሞባይል ስልክ ወይም ሲም ካርድ የሚጠቀሙ (ለምሳሌ አንደኛውን ለግል ጉዳይ ሌላኛውን ለስራ ጉዳይ) ብዙ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ከግምት ውስጥ ካስገባን፣ ከላይ የተጠቀሰው ቁጥር ከትክክለኛው የሞባይል ተጠቃሚዎች ቁጥር በእጅጉ ሊበልጥ ይችላል፡፡ ተቋሙ ያወጣው መረጃ በጥር ወር 2022 ላይ ከኢትዮጵያ አጠቃላይ ህዝብ 49.1% ያህሉ የሞባይል ስልክ ተጠቃሚ እንደነበር ያሳያል፡፡ የተጠቃሚዎች ቁጥር ከአንድ አመት በፊት ከነበረው በ9.4 ሚሊዮን (+19.2%) ማደጉንም ያመለክታል፡፡
የኢንተርኔት ተጠቃሚነት በኢትዮጵያ – 2022
ዳታሪፖርታል (2) /Datareportal/ የተባለው ድረገጽ ይፋ ያደረገው መረጃ በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር እ.ኤ.አ በ2022 ጥር ወር 29.83 ሚሊዮን ደርሶ እንደነበር ያሳያል (3)፡፡ ይህም በ2022 አመት መጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት ሽፋን ከአጠቃላዩ ህዝብ 25% ያህሉን ይሸፍን እንደነበር ያሳያል፡፡ ኬፒዮስ (4) /Kepios/ የተባለው ተቋም በበኩሉ በኢትዮጵያ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ2021 እስከ 2022 በነበሩት ጊዚያት በ731,000 ማደጉን ይፋ አድርጓል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ በ2022 መጀመሪያ ላይ በኢትዮጵያ 89.5 ሚሊዮን ያህል ህዝብ ወይም ከአጠቃላይ የአገሪቱ ህዝብ 75% ያህሉ የኢንተርኔት ተጠቃሚ እንዳልነበር ማየት ይቻላል (5)፡፡ ዲጂታል እውቀትንና የዲጂታል ኢኮኖሚ አቅርቦትን ለማስፋፋት ከፈለግን፣ ይንን ትልቅ እንቅፋት መቅረፍ ግድ ይለናል፡፡
የኢንተርኔት አገልግሎት ፍጥነት በኢትዮጵያ – 2022 (ከህዳር 21 – ህዳር 22 አማካይ ፍጥነት)
ኦክላ (6) / Ookla/ የተባለው ተቋም በየአመቱ የአገራትን አማካይ የኢንተርኔት ፍጥነት በማስላት ደረጃ ያወጣል፡፡ ተቋሙ በህዳር ወር 2022 ያወጣው የአለማችን አገራት የሞባይል ዳታ ኢንተርኔት አገልግሎት ፍጥነት ሪፖርት፣ ኢትዮጵያ ከ142 አገራት መካከል 100ኛ ደረጃን መያዟን ያመለክታል፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ በመደበኛ (ብሮድባንድ) ኢንተርኔት አገልግሎት ፍጥነት ኢትዮጵያ ከ180 የአለማችን አገራት መካከል 170ኛ ደረጃን መያዟንም መረጃው ያሳያል፡፡ ከዚህም 5.2 ሜጋ ባይት በሰከንድ የሆነው የኢትዮጵያ የብሮድባንድ ኢንተርኔት ፍጥነት፣ በአለማችን እጅግ ዝቅተኛ ከሚባሉት የኢንተርኔት ፍጥነቶች ተርታ እንደሚሰለፍ መረዳት እንችላለን፡፡
የማህበራዊ ሚዲያ መረጃ በኢትዮጵያ – 2022
ዳታሪፖርታል (2) /Datareportal/ የተባለው ድረገጽ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚያሳየው፣ በኢትዮጵያ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ቁጥር እ.ኤ.አ በ2022 ጥር ወር 6.35 ሚሊዮን የነበረ ሲሆን፣ ይህም ከአገሪቱ አጠቃላይ ህዝብ 5.3% ይደርሳል፡፡ ያም ሆኖ ግን፣ የመረጃ ምንጮች (የማህበራዊ ሚዲያ ኩባንያዎች) የተጠቃሚዎቻቸውን ቁጥር በየጊዜው የሚያስተካክሉ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ከላይ የተጠቀሰው ቁጥር ሊለወጥ ይችላል፡፡ ሜታ (ፌስቡክ) ይፋ ያደረጋቸው የማስታወቂያ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በ2022 የመጀመሪያዎቹ ወራት በኢትዮጵያ 5.95 ሚሊዮን የፌስቡክ ተጠቃሚዎች የነበሩ ሲሆን፣ ይህም ከአገሪቱ አጠቃላይ ህዝብ 5.3% ይደርሳል፡፡ በኢትዮጵያ የፌስቡክ የማስታወቂያ ተደራሽነት፣ በጥር ወር 2022 ላይ ከአገሪቱ የአገር ውስጥ ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች (የዕድሜ ክልልን ሳያማክል) 19.9% ያህል ድርሻ እንደነበረውም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ሀ. የፖሊሲዎች ዝግጅት
- ብሔራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ (ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025)
- ብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ
- ብሔራዊ የዲጂታል ክፍያ ስትራቴጂ
- አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ
ለ. ተቋማዊ ዝግጁነት
- የኤሌክትሮኒክ መንግስታት/ ኤሌክትሮኒክ አገልግሎቶች (e-government/ e-services) ልማት
ሐ. ብሔራዊ የዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም
መ. ብሔራዊ የኢንፎርሜሽን፣ ኮሙኑኬሽን ቴክሎኖጂ መሰረተ ልማትና አቅርቦት/ተደራሽነት
III. የኤሌክትሮኒክ ግብይት ዋነኛ ተግዳሮቶች
- ተገቢ ህጎችና ቁጥጥሮች/ የቁጥጥር ማዕቀፍ
በኢትዮጵያ ኤሌክትሮኒክ ግብይትን ከማሻሻል ጋር በተያያዘ በዋነኝነት የሚጠቀሱና ሊሻሻሉ የሚገባቸው ክፍተቶች፣ የሚከተሉት ከቁጥጥር ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ናቸው፡-
- በምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥ ህጉ የኤሌክትሮኒክ ግብይት አገልግሎት ሰጪዎችን ሚና በግልጽ ማመልከት ይኖርበታል፤
- የግብር ምዝገባና ማሳወቅ በኢንተርኔት አማካይነት የሚከናወንበትን መንገድ መፍጠር ይመከራል፤
- ድንበር ተሻጋሪ የኤሌክትሮኒክ ግብይት አገልግሎት ለመስጠት በአገር ውስጥ ቢሮ መክፈት ያስፈልጋል፤
- የኤሌክትሮኒክ ግብይት አገልግሎት ሰጪዎች ከሚያቀርቧቸው ምርትና አገልግሎቶች ቢያንስ ግማሽ ያህሉ የአገር ውስጥ ምርቶችና አገልግሎቶች መሆናቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡ ይህም ማለት አንድ የንግድ ተቋም የኤሌክትሮኒክ ግብይት አገልግሎት በሚሰጥበት መድረክ ከውጭ አገራት የገቡ ምርቶችን ብቻ መሸጥ አይችልም፤
- ኢንቬስተሮች የቴሌኮም አገልግሎት ፈቃድ ለማግኘት ማመልከት የሚችሉት መንግስት የጨረታ ማስታወቂያዎችን በሚያወጣበት ወቅት ብቻ ነው፤
- በኢትዮ ቴሌኮም የሚፈጸም የአስገዳጅና የውስን የእርስ በእርስ ግንኙነት ትስስር ክፍያ፤
- የኮሙኑኬሽን አገልግሎቶች አዋጅና መመሪያዎቹን በመሳሰሉ የሚመለከታቸው ህጎች ውስጥ ከመድልዖ የነጻ የኢንተርኔት ትራፊክ አስተዳደር ማከናወን ያለበት አካል የትኛው እንደሆነ በግልጽ አልተጠቀሰም
- የኮሙኑኬሽን አገልግሎቶችን በተለይም ኢንተርኔትን ወይም ፌስቡክ፣ ቴሌግራምና ሌሎች ማህበራዊ ሚዲያዎችን የማቋረጥ ወይም የመዝጋት ስልጣንና ሃላፊነት ግልጽ በሆነ መልኩ ለማንኛውም የመንግስት አካል ባይሰጥም፤ በተግባር ግን ድርጊቱ ሲፈጸም ይታያል፤
- በባንክና የክፍያ ስርዓቶች ህጎች የተቀመጡ ክልከላዎችና ገደቦች በኤሌክትሮኒክ ክፍያ አጠቃቀምንና እንደ አጠቃላይ በዲጂታል ንግድ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራሉ፤
- የክፍያ መሳሪያዎች አቅራቢዎች አገልግሎት መስጠት የሚፈቀድላቸው ወደ አገር ውስጥ በሚገቡ አለማቀፍ የሬሚታንስ ገንዘቦች ላይ ብቻ ነው፤ ገንዘብ ማዘዋወር የሚፈቀድላቸው በብር ብቻ እንደመሆኑ ገንዘብ ከኢትዮጵያ ውጭ መላክ አይችሉም፤
- በሞባይልና የውክልና ባንክ አገልግሎት መመሪያ ውስጥ ገደቦች ወይም ክልከላዎች ተጥለው ይገኛሉ፤
- ለአገልግሎትና ሌሎች ግዢዎች ከኢትዮጵያ ሆኖ አለማቀፍ ክፍያዎችን ለመፈጸም አለመቻል፤
- የአገር ውስጥ ባንኮች የክሬዲት ካርድ አገልግሎት አለመስጠታቸውም ሌላኛው እንቅፋት ነው፤
- በአገር ውስጥ ባንኮች በኢንተርኔት አማካይነት ለሚደረጉ የገንዘብ ዝውውሮች የሚመደበው የውጭ ምንዛሬ በእጅጉ አናሳ መሆኑና፣ የኢትዮጵያ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ እጥረት ያለባቸው ከመሆኑ ጋር ተይይዞ እሱንም ለማግኘት አስቸጋሪ መሆኑ፤
- በኢትዮጵያ የባንኩ ዘርፍ ወይም የክፍያ ስርዓቶች ከሚመሩባቸው የአገሪቱ ህጎች (አዋጅ ወይም መመሪያዎች) አንዳቸውም ISO/IEC፣ EMV፣ payment token ወይም 3D Secureን የመሳሰሉ አለማቀፍ የክፍያ ደህንነት መስፈርቶችን አይጠቅሱም፤
- በብሔራዊ ባንክ የወጡ መመሪያዎች መሰል የአለማቀፍ የደህንነት መስፈርቶችን ማሟላት ግዴታ አድርገው አያስቀምጡም፤
- ድንበር ተሻጋሪ የመረጃ ፍሰትን የሚቆጣጠር ምንም አይነት አዋጅ የለም፤ በስራ ላይ የዋሉ አዋጆችም ግላዊ መረጃ ወይም ሚስጥራዊ መረጃ ምን ማለት እንደሆነ በግልጽ አያብራሩም፤ መረጃን በአገር ውስጥ ለመጠበቅ የሚያስችል ህጋዊ ማዕቀፍ ወይም ፖሊሲም የላቸውም፤
- የተጠቃሚን መረጃ ለተወሰነ ጊዜ ጠብቆ ማቆየትን ግዴታ የሚያደርጉ አንዳንድ ህጎች ቢኖሩም፣ ዋነኛ አላማቸው ግን ግላዊ መረጃን መጠበቅ አይደለም፤
- የብቃት የምስክር ወረቀት ሰጪዎች ኦዲት በሚከናወንበት ወቅት ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጪ የደንበኞቻቸውን ግላዊ መረጃ ለበላይ አካላት አሳልፈው መስጠት ግዴታቸው መሆንና አለመሆኑ በህጉ በግልጽ አልተቀመጠም፡፡
ኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክ ግብይትን ለማቀላጠፍ የወጡት የሚከተሉት ዋና ዋና አለማቀፍ ስምምነቶች ፈራሚ አገር አይደለችም፡-
- እ.ኤ.አ በ2005 የወጣው የተባበሩት መንግስታት በአለማቀፍ የስራ የውል ስምምነቶች፣ ሲአይኤስጂ (CISG)፣ ኤሌክትሮኒክ ኮሙኑኬሽን ስምምነቶች ውስጥ የኤሌክትሮኒክ ኮሙኑኬሽን አጠቃቀም ስምምነት እንዲሁም የኤሌክትሮኒክ ፊርማዎች ዩኤንሲትራል ሞዴል ህጎች (UNCITRAL Model Laws)፤
- የማድሪድ ስምምነትና ድንጋጌዎቹ፤
- የበርኒ የስነ-ጽሁፍና ስነ-ጥበብ ስራዎች ጥበቃ ስምምነት፤
- የደብሊው አይ ፒ ኦ (WIPO) የቅጂ መብት ውል፣ የደብሊው አይ ፒ ኦ የክዋኔና ፎኖግራሞች ውል (WIPO Performances and Phonograms Treaty) ወይም የአእምሮአዊ ንብረት መብቶች ንግድ ነክ ጉዳዮች ስምምነት (TRIPS)፣
- ለምሳሌ በሌሎች አገራት የታተሙ የውጭ ፊልሞች፣ ሙዚቃዎች ወይም መጽሐፍት በኢትዮጵያ ህጋዊ ጥበቃ የሚያገኙት በአገሪቱ ከታተሙ ወይም ከተለቀቁ ብቻ ነው፡፡
- ተተግባሪነት እና ውጤታማነት
የኤሌክትሮኒክ ግብይት ስርዓትና መሳሪያ ተተግባሪነት (በስራ ላይ የመዋል አቅም) እና ውጤታማነት የሚመሰረተው በተቋማት በተለይም በብሔራዊ ባንክ፣ በኢትዮ ቴሌኮም፣ በሳይበር ደህንነት ኤጀንሲና በአእምሮአዊ ንብረት ኤጀንሲ መካከል በሚኖረው የተናበበና የተቀናጀ አሰራር ላይ ነው፡፡ እነዚህ ተቋማት የሚያከናውኗቸው ስራዎች በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ምክር ቤት ክትትል ሊደረግባቸው ይገባል፡፡ ለህግ ህግ አውጭና አስፈጻሚ አካላት በግለሰብና በተቋማት ደረጃ የአቅም ግንባታ ድጋፎችን ማድረግ የወጡ ህጎችን በስራ ላይ የመዋል ብቃት አስተማማኝ ያደርጋል፡፡
- ክፍተቶችና ተግዳሮቶች
- በቂ መሰረተ ልማት አለመኖር
- በኤሌክትሮኒክ ግብይት ላይ እምነት ማጣት
- መንግስት በቂ ድጋፍና እገዛ አለማድረጉ
- ደረጃቸውን ያልጠበቁ የክፍያ ስርዓቶች
- የኤሌክትሮኒክ ግብይት ኢንቨስትመንትና የፋይናንስ አቅርቦት አነስተኛ መሆን
- የህዝብ ስብጥር
- የግንዛቤ እጥረት
- የሳይበር ደህንነት
- የመረጃ ማዕከል ቁጥጥር አለመኖር
- የዲጂታል ማስፋፊያ ወጪ ከፍተኛ መሆን
- ብቁ የሰው ሃይል እጥረት
- የአመራር አመለካከትና ክህሎት
- ያላደገ የቁጥጥርና ተቋማዊ ማዕቀፍ
- በእውቀት ላይ የተመረሰቱ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ የሚያግዙ አስተማማኝ መረጃዎች አለመኖር
- የቤት ለቤት ፖስታ እደላ አገልግሎት አለመኖር፤ እያንዳንዱ ሰው የፖስታ ሳጥን ቁጥር አድራሻ የሌለው መሆኑ፡፡
IV. ምክረ ሃሳቦች – በኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክ ግብይትን ከባቢ ለማጠናከር
ሀ. የቁጥጥር ማሻሻያዎች
- ህጋዊና የቁጥጥር ማዕቀፉን ለማሻሻል የቀረቡ ምክረ ሃሳቦች
- አለማቀፍ ስምምነቶች (የአእምሮአዊ ንብረት)
- የመረጃ ጥበቃ ግልጽነት
- ለፋይናንስ ቴክኖሎጂ (አነስተኛና መካከለኛ ተቋማት) ፖሊሲና ህግ ድጋፍ ማድረግ
- የወጡ ህጎችን ተፈጻሚነት ለማሻሻል የቀረቡ ሃሳቦች
- የብሔራዊ ባንክን የኤሌክትሮኒክ ክፍያ ስርዓት ቁጥጥር ክፍል ማጠናከር
ለ. መሰረተ ልማት ማስፋፋት
- የኤሌክትሮኒክ ግብይት መሰረተ ልማትንና በዘርፉ ያለውን ኢንቨስትመንት ለማሻሻል የቀረቡ ምክረ ሃሳቦች
- የቴሌኮም አገልግሎት አቅራቢዎች
- የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ዕቃዎችንና ሶፍትዌር ከውጭ ማስገባት
ሐ. የአነስተኛና መካከለኛ ተቋማት ድጋፍ
- የአነስተኛና መካከለኛ ተቋማት በኤሌክትሮኒክ ግብይት ገበያ እንዲሳተፉ ለማገዝ (ሁኔታዎችን ማመቻቸትና ማበረታቻዎችን ማድረግ) የቀረቡ ምክረ ሃሳቦች
- በፋይናንስ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ለተሰማሩ አነስተኛና መካከለኛ ተቋማት በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በኩል ድጋፍ ማድረግ
