ከህግ ውጪ ከሥራቸው የተሰናበቱ 942 ሰራተኞች ወደ ሥራቸው እንዲመለሱ መደረጉን የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም አስታወቀ፡፡
“የዳኝነትና የዲሞክራሲ ተቋማት እመርታ፤ ለተሳካ ሀገረ መንግስት ግንባታ” በሚል መሪ ሀሳብ ሀገራዊ የዳኝነትና የዲሞክራሲ ተቋማት የሪፎርም ጉዞን የሚዳስስና ቀጣይ አቅጣጫዎችን የሚመለከት ኮንፈረስ ተካሂዷል፡፡
የተቋሙ ዋና ዕንባ ጠባቂ ወይዘሮ ስመኝ ውቤ በኮንፈረንሱ ላይ እንደገለጹት፤ የህዝብ አስተዳደር እንዲሻሻልና የመንግስት ተጠያቂነት ለማሳደግ ይሰራል፡፡
አስተዳደራዊ በደል የደረሰባቸው ግለሰቦች የሚያቀርቧቸውን ቅተሬታዎችና አቤቱታዎች በመከታተል መምርምሮ እልባት እንዲያገኙ እየሰራ ይገኛል፡፡ በቀጣይም የአቤቱታ ምላሽ አሰጣጡን ከ78 በመቶ ወደ 85 በመቶ ለማድረስ መታቀዱን ገልጸዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት በተሰሩ ሥራዎች ወደ ተቋሙ ከሚመጡ አቤቱታዎች መካከል 78 በመቶው እልባት እንዲያገኙ የተደረገ ሲሆን፤ ለአስተዳደራዊ በደል ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች የቁጥጥር ሥራዎችን በመስራት 87 በመቶ መፍትሔ እንዲያኙ መደረጉንም ተናግረዋል፡፡
እንደዋና ዕንባ ጠባቂዋ ገለጻ፤ መሬታቸው ያለአግባብ የተወሰደባቸው 828 አቤቱታ አቅራቢዎች ጉዳያቸው ተመርምሮ ምትክ ቦታ እንዲሰጣቸውና 14 ሚሊየን ብር ካሳ እንዲከፈላቸው ተደርጓል፡፡ ከህግ ውጪ ከሥራቸው ተሰናብተው የነበሩ 942 ሰራተኞች ደግሞ ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ መደረጉን አብራርተዋል፡፡
አቤቱታ አቅራቢዎች ከህግ አግባብ ውጪ የተከለከሉትን ልዩ ልዩ መንግሥታዊ አገልግሎቶች እንዲያገኙ መደረጉን ጠቅሰው፤ ዜጎች መረጃ የማግኘት፤ የመጠየቅ፣ የማዘጋጀት መብታቸው እንዲከበርና የመረጃ ነጻነት ህጉ እንዲተገበር ክትትል እያደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡፡
የተጠናከረ የቁጥጥርና የምርመራ ሥርዓትን መዘርጋት፤ የአስተዳደራዊ በደል እንዲቀንስ መስራት የተቋሙ የትኩረት አቅጣጫዎች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
የህዝብ አስተዳደር በግልጽነትና በተጠያቂነት መርህ እንዲመራ ለማድረግና ህገ መንግሥታዊነትን ለማስፈን እንደሚሰራ በመግለጽ፤ ተቋማት የሚሰጧቸው ፍትሃዊነት የጎደለው ውሳኔዎችና ትዕዛዞች በወቅቱ ለማረምና ለመከላከል እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
