‹‹ከእኛ ቁጥጥር ውጭ የሆኑ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ››

Date:

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በመጪው ዓመት ጥር ወር ላይ ዋናውን የምክክር ጉባኤ ለመጥራት “የሚቻለውን ጥረት” እያደረገ መሆኑን አስታወቀ። ኮሚሽኑ ከነሐሴ 18፤ 2015 ጀምሮ በአዲስ አበባ ከተማ የጉባኤውን ተሳታፊዎች መለየት እንደሚጀምርም ይፋ አድርጓል። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ይህን ይፋ ያደረገው፤ ረቡዕ ነሐሴ 17 በዋና ጽህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው። ባለፈው ዓመት ታህሳስ ወር ላይ በአዋጅ የተቋቋመው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፤ እስካሁን ድረስ በአምስት ክልሎች እና አንድ ከተማ አስተዳደር የጉባኤ ተሳታፊዎች ልየታን አከናውኗል። ኮሚሽኑ የጉባኤ ተሳታፊዎችን የለየባቸው አካባቢዎች፤ በሐረሪ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ ጋምቤላ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ ናቸው። በዕለቱ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኙት የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ሂሩት ገብረስላሴ፤ “እስከ ጥር ድረስ ዋናውን ሀገራዊ ምክክር ኮንፍረንስ ለመጥራት የሚቻለንን ጥረት እያደረግን ነው” ብለዋል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋነኛውን ሀገራዊ ምክክር ኮንፍረንስ ለማካሄድ አቅዶ የነበረው ባለፈው ህዳር ወር ነበር። በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ባሉ የጸጥታ ችግሮች ምክንያት በእቅዱ መሰረት መጓዝ አለመቻሉን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ ሀገራዊ ምክክሩን የማስጀመሪያ መርሃ ግብር በአምስት ወራት በማራዘም ኮንፍረሱን በግንቦት ወር እንደሚያካሄድ አስታውቆ ነበር።

ይህ የኮሚሽኑ እቅድም በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መካሄድ አልቻለም። የሀገራዊ ምክክር ሂደቱ ከተያዘለት ጊዜ በላይ መዘግየቱ፤ ባለፈው ሚያዝያ ወር መጨረሻ በተካሄደ በፓርላማ የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ጥያቄ አስነስቶ ነበር። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በዚህ ስብሰባ ላይ ለተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት፤ በኢትዮጵያ ካሉት “ተጨባጭ ሁኔታዎች አንጻር” በዕቅድ የተቀመጡ ተግባራት “ለትግበራ ረዘም ያለ ጊዜያትን ወስደዋል” ሲል ሂደቱ የዘገየበትን ምክንያት አስረድቶ ነበር። የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር በዕለቱ መግለጫቸው ሀገራዊ የምክክር ኮንፈረንሱን ከስድስት ወራት በኋላ ለመጥራት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ቢጠቁሙም፤ “ከእኛ ቁጥጥር ውጭ የሆኑ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ” ሲሉ ኮሚሽኑን ተገማች ያልሆኑ ክሰተቶች ሊፈትኑት እንደሚችሉ አመላክተዋል። “በእኛ ግምት እና በእኛ ዕቅድ መሰረት ያንን ለማድረግ ነው የምናስበው” ሲሉ ኮሚሽነሯ አክለዋል። ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ከሁለት ሳምንት ገደማ በፊት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያሉ ችግሮች ስራውን “አዳጋች እያደረጉበት” አስታውቆ ነበር። ኮሚሽኑ በመላው ሀገሪቱ የሚታዩ ግጭቶች “ያላንዳች ቅደመ ሁኔታ ቆመው” “በአስቸኳይ” በምክክር እንዲፈቱ ጥሪ ማቅረቡም ይታወሳል።

የምክክር ኮሚሽኑ በዚሁ መግለጫው ባለድርሻ አካላትን “በማቀራረብ፣ የልዩነት አጀንዳዎችን ሰብስቦ ለማወያየት እና ለማመካከር አመቺ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ዝግጁ መሆኑን” መግለጹ አይዘነጋም። በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኙ ጋዜጠኞች፤ ከነሐሴ ሁለቱ የኮሚሽኑ ጥሪ በኋላ በተቋሙ በኩል የተሰሩ ስራዎችን ስለመኖራቸው ጥያቄ አቅርበዋል። ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ ለዚህ ጥያቄ በሰጡት ምላሽ “እኛ ቀጥታ አስታራቂዎች አይደለንም። [ነገር] ግን የተለያዩ አካላት በጠረጴዛ ዙሪያ መገኘት እንዲችሉ የሚደረገውን ጥረት እያደረግን ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። “ከእኛ ጋር በቀጥታ አብሮ ለመስራት ዳተኛ የነበሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደዚሁም ደግሞ ችግራችንን በትጥቅ ትግል ነው የምንፈታው ብለው የተሰማሩ ኃይሎችንም ጭምር ለማነጋገር ወስነናል” ሲሉም ምክትል ኮሚሽነሯ አክለዋል። ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ይህን ውሳኔ የወሰነው “አካታች መሆን ስላለበት” እንደሆነ ሂሩት ጠቁመዋል ሲል የዘገበው ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ነው፡፡ 

በምስራቅ ጉራጌ እና በደራ ወረዳ ንጹሐን መገደላቸው እና መታገታቸው ተነገረ

በቅርቡ በተዋቅረው ምስራቅ ጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራውና መንግሥት “ኦነግ ሸኔ” በሚል በአሸባሪነት የፈረጀው ኃይል 14 የአካባቢው ነዋሪዎችን አግቶ በመውሰድ መግደሉን ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ ታጣቂዎቹ ጥቃቱን የፈጸሙት ነሐሴ 13/2015 በኦሮሚያ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አዋሳኝ አካባቢ በሚገኙ ዱግዳ፣ መቂ እና ጢያ ትክል ድንጋይ ተብለው በሚጠሩ የምስራቅ ጉራጌ ዞን ሶዶ ወረዳ ቦታዎች ላይ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል። “የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ‘ለመንግሥት አካላት መረጃ ትሰጣላችሁ’ በሚል 16 ሰዎችን በምሽት አግተው ከወሰዱ በኋላ፤ ኹለቱ ድብደባ ቢፈጸምባቸውም ‘ነጻ ናችሁ’ በሚል ሲለቀቁ፣ ቀሪዎቹ ተገድለዋል” ነው ያሉት።  የታጣቂ ቡድኑ አባላት ከላይ ወደተጠቁሱት አካባቢዎች በምሽት በመግባት አግቶ ከመውሰድ እና ከመግደል በተጨማሪ፤ ነዋሪዎቹ አካባቢውን ለቀው እንዲሰደዱ ድብደባና ዘረፋ እንደሚፈጽሙባቸውም ተናግረዋል። “ከኦሮሚያ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አዋሳኝ የሚገኙ ነዋሪዎችን ከአካባቢው በማፈናቀል መሬቱን የራሳቸው ለማድረግ ነው ተደጋጋሚ ጥቃት እየፈጸሙ ያሉት፡፡” ያሉት አንድ ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ነዋሪ፤ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ በሚፈጽሙት ድብደባና ዘረፋ በኦሮሚያ ክልል ወሰን አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎች ከአካባቢያቸው እየተፈናቀሉ ነው ብለዋል። በተለይም በኹለቱ ክልሎች አዋሳኝ ቦታዎች ከሚኖረው ሕዝብ የክስታኔ ጉራጌ ብሔር ተወላጆች ዋነኛ የጥቃቱ ሰለባ ናቸው የተባለ ሲሆን፤ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ወደ ሶዶ ወረዳ በሚገቡበት ቦታ የሚገኙ በመሆናቸው የመጀመሪያዎቹ ተጠቂ መሆናቸው ተመላክቷል። ታጣቂዎቹ በነዋሪዎች ቤት ምሽት በመግባት “ገንዘብ እና የጦር መሳሪያ አምጡ፣ ካላመጣችሁ ትገደላላችሁ፡፡” እያሉ እያሰቃዩ ነውም ተብሏል።  በተመሳሳይ ዜና በደራ ወረዳ 12 ሰዎች በኦነግ ሸኔ ታግተው መወሰዳቸው ተነግሯል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ 12 ያህል ሰዎች በኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ታግተው መወሰዳቸውን በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ተናግረዋል። ድርጊቱ የተፈጸመው ነሐሴ 16/2015 ከረፋዱ አራት ሰዓት አካባቢ ነው የተባለ ሲሆን፤ ከታጋቾች አብዛኞቹ በአደአ መልኬ ቀበሌ በመልኬ ማርያም ቤተክርስቲያን ስርዓተ አምልኮ ሲፈፅሙ ቆይተው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ የነበሩ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡ እገታው የተፈጸመባቸው ሰዎች ካህናት እንዲሁም የአማራ ተወላጆች መሆናቸውን የተናገሩት የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ታጣቂዎቹ ያገቷቸውን ሰዎች በወረዳው በሚገኘው ባቡ ድሬ ቀበሌ እንደወሰዷቸውም ገልጸዋል። አርብ ነሐሴ 12/2015 ኹለት የኦሮሞ ተወላጆች ራሳቸውን “ፋኖ” ብለው በሚጠሩ ታጣቂዎች ሬማ በምትባል ከተማ በመገደላቸው፤ የትናንቱ እገታ የዚያ አጻፋ ሊሆን እንደሚችል ነዋሪዎች ጠቁመዋል። በአካባቢው እየሆነ ያለው ሰዎችን በማንነታቸው ምክንያት የመግደል እና የማገት ተግባር የቂም እና የበቀል አዝማሚያ የሚታይበት መሆኑን በመግለጽም፤ “ይህም ለዘመናት ተጋብቶ እና ተዋልዶ በአብሮነት የኖረን ሕዝብ የሚያቃቃር ነው” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ቦታው የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል አዋሳኝ እንደመሆኑ ቀደም ሲል የኹለቱም ብሔር ተወላጆች ገበያ በጋራ ይገበያዩ እንደነበር የጠቀሱት ነዋሪዎቹ፤ በዚህ ወቅት ግን ከኦሮሚያ ወደ አማራ ክልልም ሆነ ከአማራ ወደ ኦሮሚያ ክልል ሄዶ የንግድ ልውውጥ ለማድረግ ከፍተኛ ስጋት መኖሩን ነው የገለጹት። በመሆኑም አሁን ላይ ከአማራ ክልል ወደ ደራ ወረዳ የሚወስደው ዋናው መንገድ ባለው የደህንነት ስጋት ምክንያት ዝግ መሆኑ እና ተጓዦች በኤጄሬ ወረዳ በኩል ያለውን አማራጭ መንገድ እንደሚጠቀሙ ተመላክቷል። የደራ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት “በወረዳው 12 ሰዎች በታጣቂ ቡድኑ መወሰዳቸው እውነት ነው” ካለ በኋላ፤ “ያሉበትን ሁኔታ እየተከታተልኩኝ ነው” ሲል መናገሩን አዲስ ማለዳ ዘግባለች፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በከተማዋ ከ24 ሺህ በላይ ንቁ የግንባታ ፈቃድ ያላቸው ሳይቶች መኖራቸው ተገለፀ

በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚደርሰውን የህይወትና የንብረት ጉዳት ለመቀነስ የቁጥጥርና የግንዛቤ...

አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ለሕክምና በወሰደችው መድኃኒት ምክንያት ከውድድር ታገደች

የቀድሞዋ የሁለት ጊዜ የዓለየቀድሞዋፒዮኗ ኢትዮጵያዊቷ ጉዳፍ ፀጋይ ከውድድር በፊት...

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ እውቅና ሊሰጣቸው ነዉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እውቅና የሚያገኙት የጎርጎርጎረሳዉያኑ 2026 በሞሮኮ...