ዐራት ዐይና ቆሞስ አባ ይባቤ በላይ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ

Date:

አጭር የሕይወት ታሪክ

ዐራት ዐይና ቆሞስ አባ ይባቤ በላይ ከአባታቸው ከአቶ በላይ ፈንታ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ይታይሽ ወርቄ በቀድሞው አጠራር በጎጃም ክፍለ ሀገር በዳንግላ አውራጃ አብሽካን ቅዱስ ጊዮርጊስ በተባለ ቦታ መጋቢት 27 ቀን 1951 ዓ.ም ተወለዱ።

በ1956 ዓ.ም በአያታቸው (የእናታቸው እናት) ሞት ምክንያት እናታቸው አባታቸውን ሊቀ ካህናት ወርቄ ጀምበሬን ለመጦር ወደ ናዳ ሲሄዱ ዐራት ዐይና ቆሞስ አባ ይባቤ በላይ በወቅቱ የ5 ዓመት ሕፃን ነበሩ።

ወዲያው ናዳ እንደደረሱ የወላጆቻቸውን ፍቅር አጣጥመው ሳይጨርሱ ገና በ5 ዓመታቸው ወደ አብነት ት/ቤት በመግባት ትምህርታቸውን በዝክረ አቦ ከፊደል ገበታ እስከ ጸዋትዎ ዜማ ከመምህር የኔታ ተአምር አስኪደዋል።

በመቀጠል ቻቫ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወደተባለ ቦታ በመሄድ የቅኔ እና የፍትሐ ነገሥት መምህር ከሆኑት ከየኔታ ወሀቤ ጸጋ ቅኔን ከእነአገባቡ፤ ግስን እስከ አመሉ እንዲሁም የአቡሻኽር ትምህርትን ተምረው በመምህራቸው ተመርቀዋል።

በተጨማሪም በመምህራቸው የኔታ ወሀቤ ጸጋ መልካም ፈቃድ ለግ ማርያም ወደተባለው ቦታ ወደሚገኙት መምህር የኔታ መንክር ጉባኤ ቤት ገብተው ለሁለተኛ ጊዜ የቅኔን ትምህርት ተምረው ተመርቀዋል። በሁለቱም ጉባኤ ቤት እየተመላለሱ የቅኔ ዘረፋን አስኪደዋል።

የቅኔ ትምህርታቸውንም ካስመሰከሩ በኋላ ምክትል መምህር በመሆን አስተምረዋል።

ዐራት ዐይና የኔታ ይባቤ በላይ ለትምህርት ባላቸው ፍላጎት የሊቃውንት መፍለቂያ ወደ ሆነው ደብረ ዲማኅ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገዳም በመሄድ ከመምህር አለቃ ወ/ማርቆስ የሐዲሳት ትርጓሜንና የፍትሐ-ነገሥትን ትምህርት ተምረዋል።

በዚህም ቦታ በመምህራቸው መልካም ፈቃድ በ1974 ዓ.ም ከትምህርታቸው ጎን ለጎን የቅኔ እና የአቡሻኽር ትምህርትን ወንበር ዘርግተው አስተምረዋል።

ዐራት ዐይና ቆሞስ አባ ይባቤ በላይ መጻሕፍተ ብሉያትን ከመምህር ገብረ አምላክ እና ከመምህር ገብረ ኢየሱስ ተምረው ተመርቀዋል።

መዓርገ ዲቁናን ከብፁዕ አቡነ ማርቆስ ቀዳማዊ በ1964ዓ.ም የተቀበሉ ሲሆን በፈቃደ እግዚአብሔር በ1985 ዓ.ም ግንቦት 12 ቀን በደብረ ሊባኖስ አቡነ ተክለሐይማኖት ገዳም ሥርዓተ ምንኩስናን ፈጽመዋል።

በ1986ዓ.ም ደግሞ መዓርገ ቅስናን እና ቁምስናን በወቅቱ የምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ከነበሩት ከብፁዕ አቡነ በርናባስ ተቀብለዋል።

ዐራት ዐይና ቆሞስ አባ ይባቤ በላይ ትምህርታቸውን እንደጨረሱ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ፈቃደ እግዚአብሔርን ለመጠየቅ ሱባኤ ገብተው ፈለገ ብርሃን ናዳ ማርያም ላይ ታላቅ ጉባኤና ገዳም እንደሚተከል በሱባኤ ተገልጦላቸው ጥቅምት 20 ቀን 1979ዓ.ም በመምህራቸው አለቃ ወ/ማርቆስ ሽኝት ተደርጎላቸው ወደ ናዳ መጥተዋል።

እንደመጡም ቀድሞ በሱባኤ የተረዱትን ሀሳበ እግዚአብሔር በቦታው የነበሩ አንዲት ባሕታዊት እናት በዚህ ቦታ ታላቅ ገዳም እና ጉባኤ ቤት እንደሚመሰረት ደግመው ነግረዋቸዋል።

ዐራት ዐይና ቆሞስ አባ ይባቤ በላይ ከ1974-1978 ዓ.ም ለዐራት ዓመታት ከአለቃ ወ/ማርቆስ እየተማሩ ቅኔ እና አቡሻኽርን፤ ከ1979-2018ዓ.ም ለ39ዓመታት በድምሩ ከ44ዓመታት በላይ ከ25,000-30,000 ደቀ መዛሙርትን በማስተማር በርካታ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን አፍርተዋል።

ዐራት ዐይና ቆሞስ አባ ይባቤ በላይ በተወለዱ በ67 ዓመታቸው ኅዳር 21 ቀን 2018 ዓ.ም ከዚህ ዓለም ድካም አርፈዋል።

ሥርዓተ ቀብራቸውም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ከሩቅም ከቅርብም የተገኙ ዘመድ ወዳጆቻቸው፣ ያስተማሯቸው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ከተለያዩ ቦታዎች የሄዱ የመንፈስ ልጆቻቸው በተገኙበት ለ40ዓመታት በጸለዩበት፣ ብዙ ተጋድሎ በፈጸሙበት እና ወንበር ዘርግተው ባስተማሩበት በክብረ ደናግል ናዳ ቅዱስ ላሊበላ አንድነት ገዳም ዛሬ ኅዳር 23 ቀን 2018ዓ.ም ተፈጽሟል።

©ማኅበረ ቅዱሳን

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

የእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ፣ የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አካልና የመንፈስ...

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ የአጼ ቴዎድሮስ የፀጉር ቁንዳል እና...

ፈረንሳይ የ54 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ለመስጠት ተስማምታለች

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ሀገራቸው ለኢትዮጵያ የኃይል...

ትራምፕ ኢራን ላይ ያላቸው ትዕግሥት እየተሟጠጠ መሆኑን ተናገሩ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከቻይናው መሪ ዢ ጂንፒንግ ጋር...