የሬማ ጀነራል ቢዝነስ መስራችና ባለቤት የሆኑት አቶ ፍቅሬ አስፋው፤ ከ6 ቢሊየን ብር በሚበልጥ ወጪ የተለያዩ የግንባታ ፕሮጀክቶችን እያከናወኑ እንደሆነ ተናግረዋል።
በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህርዳር የሚከናወነው ይሄ ግዙፍ ኢንቨስትመንት፤ ከፍተኛ ደረጃ ያላቸው መንገዶችን፣ ባለ5 ኮከብ ሆቴል ግንባታ፣ ሰፊ የንግድ ማዕከሎችና ሌሎች በርካታ ፕሮጀክቶችን ያካትታል።
ወደ ግንባታ ዘርፍ የገቡት በጎንደር በአጎታቸው ኩባንያ እስከ ፎርማን ድረስ በመሥራት ልምድ ካገኙ በኋላ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
የ30 ዓመቱ አቶ ፍቅሬ ባለትዳርና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ሲሆኑ፤ ያቋቋሟቸው ድርጅቶች በዓመት 3.2 ቢሊዮን ብር ገቢ እንደሚያስገኙላቸው ተናግረዋል።
አሁን ላይ የሚያከናውኗቸው ፕሮጀክቶች 2,500 ለሚደርሱ ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠራቸውንም ጠቁመዋል፡፡
ሬማ ኮንስትራክሽን፤ በኤሌክትሮ-መካኒካልና በውሃ ሥራዎች ደረጃ 1 ፈቃድ ያለው ሲሆን፤ በሪል እስቴት፣ በአስመጪና ላኪ፣ በሆቴል አገልግሎት፣ በትራንስፖርትና ሌሎች የቢዝነስ ዘርፎች ውስጥ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ነው፡፡
ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ቡና ለውጭ ገበያ መላክ መጀመራቸውን የሚናገሩት ባለሃብቱ፤ በዚህም 11 ሚሊየን ዶላር ገቢ ማግኘታቸውን ከአርትስ ቲቪ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
