ሃይንከን ኢትዮጵያ በደራሽ የጋራ መኖርያ ቤት ፕሮጀክት አማካይነት ለበደሌ ከተማ ነዋሪዎች 20 ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶችን ገንብቶ ታህሳስ 16 ቀን 2018 ዓ.ም አስረከበ።
በኢኮኖሚ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ የበደሌ ነዋሪዎች በከተማ አስተዳደሩ ትብብር በጥንቃቄ ተመርጠው ተጠቃሚ መደረጋቸውን የሃይንከን ኢትዮጵያ የሰስቴይኔቢሊቲ የውጭ እና መንግስታዊ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ፍቃዱ በሻህ ገልፀዋል።
ቤቶቹ ከ33 ሚልየን ብር በላይ የወጣባቸውና በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ የተገነቡ ናቸው። ቤቶቹ የጋራ መጸዳጃ፣ መታጠቢያ እና ማብሰያ ቤቶችን ያካተቱ መሆኑን ለመመልከትችለናል።
አቶ ፍቃዱ በሻህ ለሥራው መሳካት አስተዋፅኦ ያደረጉ የቡኖ በደሌ ዞንና የከተማ የአስተዳደር አካላት፣ በግንባታው የተሳተፈው ስራ ተቋራጭ ድርጅት፣ የሄኒከን የበደሌ ቤተሰቦችና ሰራተኞችን አመስግነዋል።
ሃይንከን ኢትዮጵያ ደራሽ በተሰኘ ኘሮጀክቱ ብቻ ለአቅመ ደካማ ወገኖች ድጋፍ ሲያደርግ ይኸ ለ6ኛ ጊዜ ነው።
በተመሳሳይ ሁኔታ ሃይንከን ኢትዮጵያ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የኀብረተሰብ ክፍሎች የኑሮ ሁኔታ ለማሻሻል ያለመ በጠቅላላው በ 7 ሚልየን ብር ወጪ 22 አባወራዎችን ተጠቃሚ ያደረገ የወተት ላሞች እርባታ እና የዶሮ እርባታ ማዕከላት ሐምሌ 2 ቀን 2017 ዓ.ም ተመርቀው ለአገልግሎት መብቃታቸው የሚታወስ ነው።
ሃይንከን ኢትዮጵያ “ደራሽ” የተሰኘውን ለችግረኛ ወገኖች ቤት የሚገነባበት የመጀመሪያው ፕሮጀክቱን የጀመረው በልደታ ክፍለ ከተማ ከረዩ ሰፈር 53 ደረጃቸውን የጠበቁ መኖርያ ቤቶች ለነዋሪዎች በማስረከብ ነው፡፡
በደራሽ ቁጥር 2 ደግሞ በቀጨኔ ከዕድሜ ብዛት ሊፈርስ በመቃረቡ ምክንያት የነዋሪዎቹን ህይወት አደጋ ላይ ሊጥል የነበረን ከእንጨትና ጭቃ የተሰራ ፎቅና ምድር ህንጻ አፍርሶ በመስራት ለነዋሪቹ መልሶ አስረክቧል።
ሶስተኛውና ፕሮጀክት ቂርቆስ አካባቢ የተከናወነ ሲሆን፤ በዚህም 50 ቤቶችን በመስራት ቆርቆሮ በቆርቆሮ በተሰራ ቤት ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ወገኖችን ደረጃውን ወደጠበቀ መኖሪያ ቤት አሸጋግሯል፡፡ አራተኛው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ፣ አምስተኛው በሐረር ከተማ በተመሳሳይ መንገድ ድጋፉን ለግሷል።
የከተማ አስተዳደሩ ሃይኒከን ኢትዮጵያን ጨምሮ በስራው የላቀ አስተዋጽኦ ያደረጉ አካላት የምስጋና ምስክር ወረቀት የሰጠ ሲሆን እንግዶች የችግኝ መትከል መርሐግብር አከናውነዋል።
ሃይንከን ኢትዮጵያ ባለፈው የበጀት ዓመት ከ18 ቢልየን ብር በላይ የግብር ግዴታውን በመወጣት በፌደራል መንግስት መሸለሙ አይዘነጋም።
