ግዮን መጽሔት :- ኢትዮጵያውያን ወጣቶች፣ እንኳን ለ2019 ዓ.ም. አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ! አዲሱ ዓመት ለእያንዳንዳችሁ፣ ለቤተሰቦቻችሁ እና ለሀገራችን ሰላም፣ ተስፋ፣ ጤናና ብልጽግና እንዲያመጣ ከልብ እመኛለሁ። ይህንን መልካም የአዲስ ዓመት ምኞት ራሴንና ቤተሰቦቼን፣ እንዲሁም ዩዝ ካልቸራል ኤንድ ዴቨሎፕመንት (YCDF)ን በመወከል አቀርባለሁ።
አዲስ ዓመት የቀን መለወጥ ብቻ አይደለም። ያለፈውን ዓመት ሥራዎቻችንን በመመርመር፣ ከጥንካሬዎቻችንም ሆነ ከስህተቶቻችን በመማር፣ አዲስ ተስፋ ለመሰነቅ እና ለተሻለ ነገ የሚያደርሱንን ውሳኔዎች ለመውሰድ የሚሰጠን ዕድል ነው። ስለዚህ 2019 ዓ.ም. ያለፈውን በመድገም የምናሳልፈው ሳይሆን፣ ከተሞክሮዎቻችን በመማር የተሻለ ነገን የምንገነባበት ዓመት ይሁን።
በዚህ መንፈስ 2019 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ወጣቶች ካለፈው ዓመት በበለጠ ለሰላም የምትሠሩበት፣ ሰላምን የምትመርጡበት እና የሰላም አምባሳደሮች የምትሆኑበት ዓመት እንዲሆን ከልቤ እመኛለሁ።
ወጣቶች በማኅበረሰብ ውስጥ የሚከሰቱ ግጭቶችን ለመከላከል፣ ውይይትን ለማበረታታት፣ እርቅን ለማስተዋወቅ እና የተሻለ የጋራ ኑሮ ለመገንባት ትልቅ አቅም አላችሁ። ወጣትነት የኃይል፣ የፈጠራ፣ የድፍረት፣ የቴክኖሎጂ እና የለውጥ ዘመን ነው። ይህ ኃይል ለግጭት እና ለጥፋት ሳይሆን ለሰላም መገንቢያ፣ ለልማት እና ለሀገር ግንባታ ሲውል ትልቅ ሀገራዊ ኃይል ይሆናል።
ሰላም የመንግሥት ወይም የፖለቲካ መሪዎች ብቻ ኃላፊነት አይደለም። ሰላም የጋራ ኃላፊነት ነው። እያንዳንዳችን በየቀኑ በምንናገረው፣ በምንጽፈው፣ በምንሠራው እና በምንመርጠው ተግባር ሰላምን ልንገነባ ወይም ልናዳክም እንችላለን። ስለዚህ የራሳችንን፣ የቤተሰቦቻችንን፣ የማኅበረሰባችንን እና የሀገራችንን ደህንነት ማስጠበቅ በእያንዳንዳችን ላይ የወደቀ የጋራ ኃላፊነት ነው።
በተለይም በዛሬው የቴክኖሎጂና የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመን የወጣቶች ተጽዕኖ እጅግ ከፍተኛ ነው። አንድ ወጣት በማኅበራዊ ሚዲያ የሚያሰራጨው መረጃ፣ የሚጽፈው አስተያየት ወይም የሚጠቀመው ቃል በሺዎች ሊነበብ እና በሌሎች ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥር ይችላል። ስለዚህ ከጥላቻ ንግግር፣ ከሐሰተኛ መረጃ፣ ከማኅበረሰብ ክፍፍል እና ከግጭት ቋንቋ መራቅ ትንሽ ተግባር የሚመስል ቢሆንም ትልቅ የሰላም አስተዋጽኦ ነው። አንድን መረጃ ከማሰራጨታችን በፊት እውነተኛነቱን መጠየቅ፣ የሌላውን ሰው ክብር ማስጠበቅ እና ቃላቶቻችን ምን ዓይነት ውጤት ሊያመጡ እንደሚችሉ ማሰብ ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ ባህሪ ነው።
እርስ በርሳችን የምንለያይበትን ነገር ከማጉላት ይልቅ የምንጋራቸውን እሴቶች ማጠናከር ይገባናል። ቋንቋችን፣ ባህላችን፣ ታሪካችን እና ማንነታችን የሚለያዩ ቢሆኑም በመከባበር፣ በመደማመጥ እና በውይይት ሲመሩ ለሀገራዊ ጥንካሬ መሠረት ሊሆኑ ይችላሉ። ልዩነት የግጭት ምክንያት ብቻ ሳይሆን የሀገር ሀብትም ሊሆን ይችላል። ይህንን ሀብት ወደ ጥንካሬ መለወጥ ግን በሰላማዊ ውይይት፣ በመከባበር እና በጋራ ኃላፊነት ይቻላል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ሆይ፣ እያንዳንዳችሁ ለሀገራችሁ ሰላም የምታደርጉት አስተዋጽኦ ዋጋ አለው። ወጣቶችን በስፋት ያላሳተፈ ማንኛውም ማኅበራዊ ንቅናቄ የመሳካት ዕድሉ እንደሚያንስ ሁሉ፣ ወጣቶችን ያላሳተፈ የሰላም ጥረትም ዘላቂ ውጤት ማስገኘት ይከብደዋል። የወጣቶች ተሳትፎ ለሰላም ሂደት ተጨማሪ ኃይል ብቻ ሳይሆን፣ ዘላቂነቱንም የሚያጠናክር መሠረት ነው።
ስለሆነም ስለራሳችሁ፣ ስለቤተሰቦቻችሁ እና ስለሀገራችሁ ሰላም ግድ የሚላችሁ ወጣቶች፣ 2019 ዓ.ም. ግብዣና ጋባዥ ሳትጠብቁ ለሰላም ተግባራት በንቃት የምትሳተፉበት ዓመት እንዲሆን ከልቤ እጠይቃለሁ። የሰላም አምባሳደር መሆን ሁልጊዜ ትልቅ ፕሮጀክት መጀመር ወይም ታላቅ ንግግር ማድረግ አይጠይቅም። አንዳንድ ጊዜ የሰላም አምባሳደር መሆን ሌላውን ሰው ማዳመጥ፣ በቁጣ ጊዜ መታገስ፣ የሚያከፋፍል መረጃን አለማሰራጨት፣ ሁለት ተጋጭተው ያሉ ሰዎችን ማስታረቅ ወይም በልዩነት ውስጥ የጋራ ነገርን መፈለግ ሊሆን ይችላል።
ሰላም የሚገነባው በትልልቅ ውሳኔዎች ብቻ ሳይሆን፣ በየቀኑ በምናደርጋቸው ትንንሽ ምርጫዎች ጭምር ነው። ስለዚህ በአዲሱ ዓመት እያንዳንዳችን “እኔ ለኢትዮጵያ ሰላም ምን ማድረግ እችላለሁ?” ብለን እንጠይቅ። ትናናሽ የሚመስሉ ሆኖም ትልቅ ዋጋ ያላቸውን የሰላም ተግባራትን እንከውን።
2019 ዓ.ም. የሰላም፣ የውይይት፣ የእርቅ፣ የትብብር እና የተስፋ ዓመት እናድርገው። የኢትዮጵያ ወጣቶች፣ እናንተ የሀገራችን ነገ ብቻ ሳትሆኑ፣ የዛሬዋም ሰላም ገንቢዎች ናችሁ። ሰላምን እንምረጥ፣ ውይይትን እናስቀድም፣ እርስ በርሳችን እንስማ፣ እንከባበር፣ በልዩነታችን ውስጥ የምንጋራውን እንፈልግ እና ለተሻለች፣ ሰላማዊትና የበለጸገች ኢትዮጵያ በጋራ እንሥራ።
እንኳን ለ2019 ዓ.ም. አዲስ ዓመት አደረሳችሁ! ዓመቱ የሰላም፣ የስኬት፣ የእርቅ፣ የትብብር እና የተስፋ ይሁንላችሁ!
ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር 236 መስከረም 2019 ዓ.ም
