የመንግሥት ሠራተኞች በቀጣዩ 2019 ዓ.ም የጤና መድን አገልግሎት ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ ጤና መድን አገልግሎት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ጤና መድን አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ወርቁ እንደገለጹት፤ መደበኛ በሆኑ የሥራ መስኮች የተሰማሩ ዜጎች የጤና መድን አገልግሎት እንዲያገኙ ታስቦ የተዘጋጀው የማኅበራዊ ጤና መድን አገልግሎት በአዋጅና ደንብ ከጸደቀ 14 ዓመታትን አስቆጥሯል።
አዋጁ ሠራተኛው ከደመወዙ ሦስት በመቶው እንዲቆረጥና የፌዴራልና የክልል መንግሥታትም ለቀጠሩት ሠራተኛ ሦስት በመቶውን እንዲሸፍኑ ይደነግጋል።
ሆኖም ግን ባለፉት ዓመታት በመንግሥት በኩል በቂ ገንዘብ ባለመኖሩና በኑሮ ዉድነት አማካኝነት ሳይተገበር ቢቆይም በዘንድሮዉ ዓመት ግን የተሻለ ተስፋ ታይቷል ብለዋል።
በዘንድሮው ዓመት በጤናው ዘርፍ የተሰማሩ ከ500 ሺህ በላይ ሠራተኞች ለአገልግሎቱ መመዝገባቸውን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ ከገንዘብ ሚኒስቴርም 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መጽደቁን ተናግረዋል።
በሚቀጥለው ዓመትም ሁሉም የመንግሥት ሠራተኛ ተጠቃሚ እንዲሆን የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት በጀት ይይዛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመላክተዋል።
