የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪትን ሰበብ በማድረግ፣ ከሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ወይም ከሌሎች የመንግሥት ተቋማት ውክልና አለን የሚሉ ሕገ-ወጥ አካላት መበራከታቸውን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ማስጠንቀቂያ አመልክቷል።
ሚኒስቴሩ አጭበርባሪዎች በግል ስልክ፣ በአጭር የጽሑፍ መልዕክት (SMS)፣ በቴሌግራም እና በዋትስአፕ ገንዘብ በመጠየቅ ዜጎችን እያጭበረበሩ መሆኑን ነው የጠቆመው።
ሚኒስቴሩ ለውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት አገልግሎት በማንኛውም የማኅበራዊ ትስስር ገጽ ወይም በስልክ ጥሪ በፍጹም ገንዘብ እንደማይጠይቅ አረጋግጧል።
ማንኛውም ሰው የመንግሥት ተቋምን በመወከል በዲጂታል መንገዶች የገንዘብ ጥያቄ ሲያቀርብ፣ የግል ወይም የባንክ መረጃዎችን (የባንክ ሂሳብ ቁጥር፣ የይለፍ ቃል ወይም የOTP ሚስጥራዊ ኮድ) አሳልፎ ከመስጠት መቆጠብ እንደሚገባው ጠቁሟል።
ዜጎች እንዲህ ዓይነት አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎች ሲያጋጥሙ መረጃውን ወዲያውኑ በአቅራቢያ ለሚገኙ የሕግ አስከባሪ አካላት ወይም ለሥራና ክህሎት ሚኒስቴር መዋቅሮች በአስቸኳይ እንዲያሳውቁም ጥሪ አቅርቧል።
