“የትግራይ የሰላም ሃይልን” የትግራይ ኃይል አባላትና ወጣቶች  እንዲቀላቀሉት ጄ/ ፃድቃን ጠየቁ

Date:

” አራት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሁለት ነባር ወታደራዊ አመራሮች ‘ ምንቅስቓስ ደለይቲ ለውጢ ‘ (የለውጥ ፈላጊዎች እንቅስቃሴ) የሚባል ስብስብ ፈጥረናል ! ” – ሌ/ጄነራል ፃድቃን ገብረትንሳኤ

” ‘ ከኮር በላይ በሚሉ የሰራዊት አመራር ነን ‘ በሚሉ ጥቂት አመራሮችና የሻዕብያ ሰላይ ሰርገ ገቦች ምክንያት ወደ ትግራይ ለመግባት የማልችል መሆኔ እጅግ እጅግ ይቆጨኛል ! “

የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ሌተናል ጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሳኤ አዲስ የለውጥ እንቅስቃሴ እየመሩ ናቸው።

ጄነራሉ የሚመሩት እንቅስቃሴ ” ምንቅስቓስ ደለይቲ ለውጢ (የለውጥ ፈላጊዎች እንቅስቃሴ) ይባላል።

ትላንት ትግራይ ብሮድካስቲንግ ስርቪስ  ( TBS) ከተባለ ሚዲያ ጋር ቃለምልልስ ያደረጉ ሲሆን ሰፊ ጉዳዮችን አንስተዋል።

ምን አሉ ?

በአቶ ጌታቸው ረዳ እና በራሳቸው በተመራው ጊዜያዊ አስተዳደር ወቅት ፦
– ሁሉም አስተሳሰቦች ማስተናገድ የሚችል ካውንስል እንዲቋቋም ፣
– ለወደፊቱ በምርጫ የሚቋቋሙ የህዝብ ምክር ምክር ቤቶች እውነተኛ የህዝብ ችግር የሚንፀባረቅባቸው እንዲሆኑ ፣
– ብዙህነት አስተሳሰብ የማራመድ ልምድ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ሁኔታ እንዲፈጠር ጥረት ቢያደርጉም እንዳልተሳካ ገልጸዋል።

” ጠቅላይ አስተሳሰብ ካላቸው ቡድኖች ከፍተኛ ተግዳሮት ገጥሞኛል ” ያሉት ጄነራሉ ” በብዙ ጥረት የተለያዩ ፓርቲዎችና አስተሳሰቦች የተካተቱበት ጊዚያዊ ምክር ቤት ቢቋቋምም እንደታለመለት አልቀጠለም ” ብለዋል።

የመንግስትንና የፖርቲ መደበላለቅ እንዲለያይ በጥናት የተደገፈ መፍትሄ ቢቀርብም በክልሉ ለ30 ዓመታት በብቸኝነት ተቆጣጠሮ የቆየው የህወሓት አስተሳሰብና አሰራር ሊያራምዳቸው እንዳልቻለ ተናግረዋል።

በተደረገው ጥናት የ19 ወረዳ አመራሮች በምክር ቤት ሳይሆን በህወሓት የተሾሙ ሆኖው እንደተገኙ ፤ ይህንን ለመቀየር ብዙ ርቀት እንዳይሄዱ ለዓመታት የተተበተበው ኔትወርክ ሊያሰራቸው እንዳልቻለ ተናግረዋል።

ጄነራል ፃድቃን ሲመሩት የነበረው ጊዚያዊ አስተዳደር ተቆጥረው የተሰጡትን ሃላፊነቶች እንዳይወጣ በተለይ የያኔው ምክትል ፕሬዚዳንት የአሁኑ ፕሬዜዳንት ታደሰ ወረደ (ሌ/ጀነራል) የሚመራው የፀጥታ ሃይል አኗኗሩ እንዲበላሽ በማድረግ በጊዚያዊ እስተዳደሩ ተቃዉሞ እንዲኖረው በመስራት ለስልጣን መወጣጫ እንደተጠቀመበት ከሰዋል።

ጄነራሉ ” ከኮር በላይ የሰራዊት አመራር ነን ” የሚሉ በግላጭ የህወሓት ደጋፊ የሆኑ አካላት ጊዚያዊ አስተዳደሩን አላሰራ አላንቀሳቅስ እንዳሉት ፤  የተከመሩ ችግሮችን ፣ የውጭውን ይቅርና የውስጥ ስራዎችን ለመስራት እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

አሁን ሌ/ጀነራል ታደሰ ወረደ ስለሚመሩት አስተዳደርም ተናግረዋል። ይህ አስተዳደር ለውጥ የማምጣት አቅምና ቅንነት የለውም ብለዋል።

” ያለፉት 30 ዓመታት በትግራይ የነበረው መንግስትና ፓርቲ አንድ ናቸው የሚል የቆየ አስተሳሰብ ነው እያራመደ ያለው ፤ በዚህ መሰል መንገድ ደግሞ በአሁናዊ የትግራይ ሁኔታ ህዝብን የሚጠቅም ለውጥ ማምጣት አይቻልም ” ብለዋል።

” አሁን ያለው የጊዚያዊ አስተዳደሩ ፕሬዜዳንት ወደ ስልጣን የመጣበት መንገድ ትክክለኛ አይደለም ” ያሉት ጄነራሉ ” የህዝብ አጀንዳ ያለው አስተዳደር አይደለም ፣ ለዚህ ነው በደቡባዊና ደቡባዊ ምስራቅ ዞን የሚታየው የህዝብ ንቅናቄ ለማፈን የሚንቀሳቀሰው ” ብለዋል።

ጄነራሉ ቢያንስ 49 (ተፎኳኳሪዎች)  በ51 (ህወሓት) የነበረው የጊዚያዊ አስተዳደሩ አወቃቀር አሁን መቶ በመቶ በሚባል መልኩ በህወሓት ቁጥጥር ስር እንዲውል መደረጉን አሳውቀዋል።

” የፌደራል መንግስት ለዚህ መሰል አስተዳደር ትግራይ እንዲመራ ፍቃደኝነት ማሳየቱ በበኩሌ የምቀበለውና የሚገባኝ አይደለም ” ብለዋል።

አዲሱን የለውጥ ስብስብ በተመለከተም ጄነራል ፃድቃን ” የትግራይ ህዝብ መሪ ነው ያጣው እንጂ ለለውጥ ዝግጁ ነው ፤ በመሬት ላይ የምናየው ይህንን ነው ይህንን የለውጥ ፍላጎት በሰላማዊ መንገድ በተገቢው መመራት አለበት ” ብለዋል።

” ከዚህ በመነሳት አራት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሁለት ነባር ወታደራዊ አመራሮች ‘ ምንቅስቓስ ደለይቲ ለውጢ ‘ (የለውጥ ፈላጊዎች እንቅስቃሴ) የሚባል ስብስብ ፈጥረናል ” ሲሉ ገልጸዋል።

” ይህ የተፈጠረው ፦
– በዓረና ፣
– በውናት፣
– በባይቶና ፣
– በስምረት ሲሆን ፣ ወታደራዊ አመራሮቹ ደግሞ እኔ (ጀነራል ፃድቃና) እና ጀነራል ተኽላይ አሸብር ነን ” ሲሉ ተናግረዋል።

” የእንቅስቃሴው ሰብሳቢ እኔ ነኝ ” ያሉት ጄነራሉ ” የፈጠርነው እንቅስቃሴ ምንጭ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ሆኖ  ጦርነት መልሶ እንዳይጀመር ለመከላከል ፣ የፖለቲካ ለውጥ እንዲደረግ ለመስራት ሲሆን ፣ ዋነኛ ዓላማዎቹ ሦስት ሆነው እነሱ ደግሞ ፦
– መንግስት ስለ ሌለ መንግስት መመስረት ፣
– በትግራይ ጦርነት እንዳይፈጠር ድምፅ መሆን ፣
– ህወሓት ቅቡልነት ስለአጣ ለመተካትና ለቀጣይ ምርጫ ለመዘጋጀት የሚሉ ናቸው ” ብለዋል።

” የጀመርነው ለውጥ የእኛ ሳይሆን የተተኪው ሃይል ድርሻ ነው ፣ እኛ እያደርግን ያለነው ለተተኪው መንገዱን የማሳየት ስራ ነው፣ የትግራይ ህዝብ በተለይ ወጣቱ የጀመርነው እንቅስቃሴ ባለቤት መሆኑ ማወቅና መደገፍ አለበት ፣ የፌደራል መንግስትም ይህንን የለውጥ ጥያቄ የመደገፍ ሃላፊነት አለበት ” ሲሉ ገልጸዋል።

ጄነራል ፃድቃን ገ/ትንሳኤ ” ህዝቡ ምርጫዬ ሰላም ነው እምቢ ለጦርነት ማለት መቻል አለበት ፣ የአንድ ፓርቲ የእድሜ ልክ አገዛዝ በቃኝ የብዙሃን አመራር ነው የምፈልገው ማለት መቻል አለበት ” ብለዋል።

” ‘ ከኮር በላይ በሚሉ የሰራዊት አመራር ነን ‘ በሚሉ ጥቂት አመራሮችና የሻዕብያ ሰላይ ሰርገ ገቦች ምክንያት ወደ ትግራይ ለመግባት የማልችል መሆኔ እጅግ እጅግ ይቆጨኛል ” ያሉት ጄነራሉ ” ወደ ትግራይ መግባት የሚከለክል ይህንን መሰል አደገኛ ፖለቲካ ቶሎ መቀየር አለበት ” ብለዋል።

” እንደ ህዝብ የሚያጠፋን ፖለቲካ ቶሎ እንዲቀየርና ምዕራፉ እንዲዘጋ ተቀናጅተን በጋራ መታገል አለብን ” ሲሉ አክለዋል።

” ‘ የትግራይ የሰላም ሃይል ‘ በሚል የተጀመረውን የሰራዊት እንቅስቃሴ እደግፈወለሁ ” ያሉት ጄነራሉ  የትግራይ ኃይል አባላት እንዲቀላቀሉት ፤ ወጣቶች በራያ በዓዲጉዶምና ሌሎች አከባቢዎች የጀመሩትን የእምቢታ እንቅስቃሴ እንዲቀጥሉ ጥሪ ሲያቀርቡ ተደምጠዋል።

ቃለ ምልልሱ የተወሰደው ከTBS ቴሌቪዥን ነው።

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የተፈናቀሉ ዜጎች በተጠለሉበት አካባቢ በቋሚነት መኖር የሚያስችላቸው 

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን የዳሰነች ወረዳ ከበኦሞ...

ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ 11ኛውን የኃይሌ ሆቴልና ሪዞርት በደብረ ብርሃን ከተማ አስመረቀ

ታዋቂው አትሌትና ባለሀብት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ በደብረ ብርሃን ከተማ...

በኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር የተዘጋጀው የመጀመሪያው አህጉራዊ የሪል ስቴት ኤግዘቢሽን ተከፈተ

በኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር አዘጋጅነት የመጀመሪያው አህጉራዊ የሪል...

በሊባኖስ እና በእሰራኤል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ተራዘመ

ትራምፕ በሊባኖስ እና በእሰራኤል መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም በሦስት...