የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኢራን ብሔራዊ ቡድንን በዓለም ዋንጫው ልንቀበለው ዝግጁ ነን ግን ለራሳቸው ህይወት እና ደህንነት ሲሉ ባይሳተፉ እንደሚሻል ተናገሩ።
የትራምፕ አስተያየት የመጣው የኢራን የስፖርት እና የወጣቶች ሚኒስትር አህመድ ዶንያማሊ አገራቸው ከፈረንጆቹ ሰኔ 11 ጀምሮ በዩናይትድ ስቴትስ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ በሚካሄደው ውድድር ላይ እንደማትሳተፍ ከተናገሩ በኋላ ነው።
ዶናልድ ትራምፕ በ Truth Social ገፃቸው ላይ “የኢራን ብሔራዊ ቡድንን ልንቀበለው ዝግጁ ነን ፤ ነገር ግን ለራሳቸው ሕይወትና ደህንነት ሲሉ እዚያ መገኘታቸው ተገቢ ነው ብዬ አላምንም” ሲሉ ጽፈዋል።
አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ በከፈቱት የተቀናጀ ጥቃት ሁለንተናዊው መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ከተገደሉ በኋላ በውድድሩ ያላቸው ተሳትፎ አጠራጣሪ ሆኖ ቆይቷል።
የኢራን የስፖርት እና የወጣቶች ሚኒስትር አህመድ ዶንያማሊ ማክሰኞ ዕለት ከአይሪብ ስፖርት ኔትወርክ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዲህ ብለዋል “ይህ ብልሹ መንግሥት መሪያችንን ስለገደለ በምንም አይነት ሁኔታ በዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ ተገቢው ቅድመ ሁኔታ የለንም” በማለት ተናግረው ነበር።
የፊፋ ደንቦች ለአስተዳደር አካሉ ምትክ የመምረጥ ነፃነትን የሚሰጡ ሲሆን ነገር ግን ማን ኢራንን ሊተካት እንደሚችል ግልጽ አይደለም።
