በመካከለኛው ምሥራቅ በተከሰተው ጦርነት ምክንያት የበረራ መስተጓጎል በመፈጠሩ፣ ኢትዮጵያ ወደ ተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ (ዱባይ) የምትልከው የሥጋ ምርት ሙሉ በሙሉ መቋረጡ ተገለጸ።
ቀደም ሲል ከአገሪቱ አጠቃላይ የሥጋ ኤክስፖርት 30 በመቶ የሚሆነውን የምትቀበለው ዱባይ ብትሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ምርቱ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ እንዲዞር ተደርጓል።
የሥጋ አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ከሊፋ ሁሴን እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ዱባይ በረራ ቢያቋርጥም፣ ወደ ሪያድና ጂዳ በረራዎች መቀጠላቸው ለዘርፉ እፎይታ ሆኗል።
በተለይም ወቅቱ የረመዳን ጾም በመሆኑ በሳዑዲ ዓረቢያ ያለው ከፍተኛ ፍላጎት የገበያ መጥፋቱን ተፅዕኖ እንደቀነሰው ተጠቁሟል።
ይሁን እንጂ የዱባይ ገበያ መቋረጥ በረጅም ጊዜ ሂደት በዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጫና ሊፈጥር እንደሚችል ስጋት ተደቅኗል።
