ይህን ተከትሎም ጎግል ለክሮም መረጃ ማፈላለጊያዉ Browser በአስቸኳይ ሊተገበሩ የሚገባቸው ሶስት አደገኛ ክፍተቶች መድፈኛ አዲስ ማሻሻያ Patch መልቀቁን አስታውቋል።
ከእነዚህ ክፍተቶች መካከል አንዱ በተለይ እጅግ አደገኛ ሲሆን፣ የግል መረጃዎችን ለመጥለፍ በመረጃ ጠላፊዎች በንቃት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለ Zero_day ጥቃት መሆኑ ታዉቋል።
የደህንነት ባለሙያዎች እንዳስጠነቀቁት ከሆነም ይህ አደገኛ ክፍተት የመረጃ ጠላፊዎች ኮምፒውተራችንን ወይም ስልካችንን ዘልቀው በመግባት የይለፍ-ቃሎችንና ሌሎች ሚስጥራዊ መረጃዎችን እንዲሰርቁ የሚያስችል መሆኑ ታዉቋል።
እስካሁን መለያ ቁጥር (CVE) ያልተሰጠውና በጎግል የውስጥ መለያ 466192044 ብቻ የሚታወቀው ይኸው ክፍተት፣ በክሮም ተጠቃሚዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ተገልጿል።
ይህ ጥቃት በፈረንጆቹ 2025 ዓ.ም. የመረጃ ጠላፊዎች በስፋት ሲጠቀሙበት የተገኘ ስምንተኛው የክሮም “ዜሮ-ዴይ” ጥቃት መሆኑም ተረጋግጧል። ይህ የሚያሳየው የክሮም ተጠቃሚዎች በተደጋጋሚ የጥቃት ኢላማ መሆናቸዉን ነው።
ታኅሣሥ 1, 2018 ዓ.ም. የተለቀቀው ይህ ማሻሻያ ከላይ ከተጠቀሰው ከፍተኛ አደጋ በተጨማሪ፣ ሁለት መካከለኛ ደረጃ የተሰጣቸውን የደህንነት ክፍተቶችም ይደፍናል ተብሎለታል።
ሁሉም የክሮም ተጠቃሚዎች የግል መረጃቸዉ ሳይጠለፍ እና የባንክ አካውንታቸዉ አደጋ ላይ ሳይወድቅ ለመከላከል፣ እንዲችሉ ሁሉንም የክሮም የመረጃ ማፈላለጊያቸዉን በአስቸኳይ እንዲያዘምኑ Update እንዲያደርጉ በጥብቅ ይመከራል።
