የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የአሠራር ስርዓቱን ለማዘመንና የደንበኞቹን ማንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ ከብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ጋር የትብብር ስምምነት ተፈራረመ።
ስምምነቱ፣ ተቋሙ በአሁኑ ወቅት ያሉትን ከ5 ሚሊዮን 500 ሺህ በላይ ደንበኞች መረጃ ከፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ጋር ለማቀናጀት ያለመ ነው።
የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ አቶ አንዋር አብራር እንደገለጹት፣ አሰራሩ በተለይም አዳዲስ የኃይል መስመር ፈላጊዎችና ነባር ተገልጋዮች መረጃቸው በዘመናዊ መልኩ እንዲደራጅ ይረዳል።
የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ሳሚናስ ሰይፈ በበኩላቸው፣ ስምምነቱ ደንበኞች ተመሳሳይ ቅጾችን በተደጋጋሚ ከመሙላት ታድጎ ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ምንም እንኳን አገልግሎቱ በይፋ የሚጀመርበት ቀን ባይቆረጥም፣ ወደ ተግባር ሲገባ የተቋሙን የስራ ጫና በመቀነስና የመረጃ አያያዝን በዲጂታል መንገድ በማሳለጥ ረገድ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
