‹‹በተሳሳተ ፖሊሲ ምክንያት ያለአግባብ የሚበለጽጉት በልጽገዋል››
አቶ ሙሼ ሰሙ (የምጣኔ ሐብት ባለሙያ)
ባለፉት ዐራት ወራት መንግሥት በሀገራችን ተግባራዊ ያደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሱ በብዙ ወገኖች ዘንድ የተለያየ አስተያየት ሲሰነዘርበት ቆይቷል፡፡ የብርን የመግዛት ዐቅም ያዳክማል ከሚለው ትችት አንስቶ የሀገሪቱን የገበያ ነጻነት ለውጪ ኃይሎች አሳልፎ ይሠጣል እስከሚለው ተቃውሞ ድረስ ልዩ ልዩ አቋሞች ሲንጸባርቁበትም ቆይተዋል፡፡ በዛሬው ቆይታችን ዕውቁን የምጣኔ ሐብት ባለሙያ ሙሼ ሰሙን በኢኮኖሚ ፖሊሲው አተገባበርና አንድምታው ዙርያ ተከታዩን ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ!
ግዮን፡- የውጪ ሀገራትና የውጪ ባንኮች ብድርም ኾነ ሥጦታ ሲሰጡ ቅድመ ሁኔታዎች ያቀርባሉ፡፡ ምክንያቱ ምንድነው?
ሙሼ፡- ዓለማችን የታላላቅ መንግሥታት የበላይነትን ለማረጋጋጥ እስከ ጦርነት የዘለቀ ውድድርና ፉክክር የሚያደርግባት መድረክ ነች፡፡ በዚህ የፉክክርና የውድድር መድረክ ላይ ያለ ምክንያትና ቅድመ ሆኔታ ማንኛውም ብድር ወይም እርዳታ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ማግኘት አይቻልም፡፡ ለዚህም ነው በራስ ሀገር አቅምና ችሎታ ላይ በተለይ ደግሞ ዜጎችን በራሳቸው የሚተማመኑ እንዲሆኑ ማብቃት የሚገባው፡፡ እርዳታ ለእርዳታነት ዓላማ ብቻ ሲባል የሚቸረው የተፈጥሮ አደጋ የመሳሰሉ ሁኔታዎች ሲከሰቱና እጅግ በጣም ጥቂት በሆኑ ሁኔታዎች ላይ ነው፡፡ በጥቅሉ ብድሮችም ሆኑ እርዳታዎች ለሰብአዊ ተግባር ብቻ ሲባል የሚፈጸሙ ተግባራት አይደሉም፡፡ ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ጂኦ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ወዘተ፣… አጀንዳዎችን ማዕከል አድርገው ተጽእኖ ለመፍጠር የሚፈጸሙ ናቸው፡፡
ግዮን፡- አዲሱ የመንግሥት ማክሮ ፖሊሲ ተግባራዊ መደረግ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የብር ዋጋ እየቀነሰ መጥቷል፡፡ የገንዘብ የመግዛት አቅም በዚህ ልክ እያሽቆቆለ የሚሔድ ከኾነ የፈጠረው ችግር እንዴት ይገለጻል?
ሙሼ፡- የአንድ ሀገር ገንዘብ የመግዛት አቅም የሚለካው የብዙ ነገሮች ድምር ውጤት ላይ ተመስርቶ ነው፡፡ የአንድ ሀገርን የገንዘብ የመግዛት አቅም ከሚወስኑ ሀገራዊ ፋይዳዎች መካከል የገንዘብ ስርጭት፣ በአገር ውስጥ ያለው የገንዘብ መጠን፣ የገንዘብ ዝውውር ፍጥነት፣ ባንኮች የሚጠቀሙባቸው የገንዘብ መሳሪያዎች እና የምርት አቅርቦቶችናና ፍላጎች የመሳሰሉት ናቸው፡፡ እነዚህንና መሰል የገንዘብን የመግዛት አቅም የሚገዳደሩ ሚዛኖች በተዛቡ ቁጥር የገንዘብ የመግዛት አቅም ይዳከማል ወይም ይጠናከራል፡፡ ስለዚህም በመርህ ደረጃ የገንዘብ የመግዛት አቅም በነጻ ገበያ ውድድር ስርዓት መመራቱ አስፈላጊ ነው፡፡
ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ከነበረችበት በቁጥጥር ከሚመራ የውጭ ምንዛሪ ወደ ነጻ የውጭ ምንዛሪ ዝውውር ሥርዓት መሸጋገሯ የጊዜ ጉዳይ እንጂ የማይቀር ነበር፡፡ ችግሩ ግን የሚመነጨው መቼና በምን ሁኔታ የሚለው ጥያቄ ሲነሳ ነው፡፡
ከ15 ዓመት በፊት በአንጻራዊነት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አቅም የፈጠረበት ጊዜ ነበር፡፡ አጠቃላይ ሀገራዊ ምርቱ በየዓመቱ በአማካይ ከ8 አስከ 10 በመቶ እድገት ያሳይ ነበር፡፡ የውጭ ምንዛሪ ከጥቁር ገበያው ጋር የነበረው አቻ የምንዛሪ ተመን 0.03 በመቶ በላይ እድገት አልነበረውም፡፡ ኢክስፖርትና እንደ ኮንፈረንስ ቱሪዝም ያሉ አዳዲስ ውጭ ምንዛሪ ማመንጫ መንገዶች ከፍተኛ እድገት ያሳዩበት ጊዜ ነበር፡፡
ግሽበት ከአንድ ዲጅት በታች የሆነበት፣ የሀገር ውስጥ ገበያ አስተማማኝ አቅርቦት ያስመዘገበበት፣ ጦርነት በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰበት፣ ግጭቶች የተመናመኑበት በአጠቃላይ የማይክሮና የማክሮ ኢኮኖሚያችን አመርቂ ሽግግርና መረጋጋት ያሳየበት ጊዜ ነበር፡፡ ያ ጊዜ የውጭ ምንዛሪ ዝውውሩን ወደ ነጻ ገበያ መር የምንዛሪ ሥርዓት ሽግግር በስኬት ማካሄድ የሚችልበት ትክክለኛው ወቅት ነበር፡፡
አሁን የወሰንበት ጊዜ ኢኮኖሚውን ጦርነት፣ ግጭት፣ የምርት መዳከም፣ የሰላም እጦት፣ የአቅርቦትና ዝውውር የፈጠረው ቀውስ ተደማምሮ፣ ኢኮኖሚው ከአቅም በላይ በሆኑ አስገዳጅ ሁኔታዎች ውስጥ እየተንገዳገደ ባለበትና የኢትየጵያ የውጭ ምንዛሪ ክምችትም የአንድ ሳምንት አቅርቦትን መሸመት የማይችልበት ወይም 1 ቢሊየን ዶላር አካባቢ የወረደበት ሁኔታ ላይ ሆነን ነው፡፡ ውሳኔውን ከአጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ድቀትና ውሎ በማደር መካካል ሆኖ የተወሰደ እርምጃ አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡
ከዚህ ውጭ ጥያቄህ ቀውስ ያስከትላል ወይ የሚል ከሆነ ገበያው በቂ ምስክር ይመስለኛል፡፡ የአቅርቦት እጥረት፣ የእቃ ዋጋ ንረት፣ የመግዛት አቅም መኮማተር፣ የዜጎች ገቢ እድገት አለማሳየት፣ የምርት መቀዛቀዝ የውጭ ምንዛሪ ዋጋ አለመረጋጋት (የውጭ ምንዛሪ እድገቱ አሁንም በመመርያ ከመገደቡ ውጭ) የመንግሥት ገቢና ወጭ አለመጣጣም፣ ትልልቅ የሥራ እድል ፈጣሪ የነበሩ እንደ ኮንስትራክሽን ማኑፋክቸሪንግ የመሳሰሉ ዘርፎች መሰነካከል እያንዳንዱ ዜጋ ላይ ከፍተኛ የኑሮ ጫና ማሳደሩና የእያንዳንዱ ዜጋ ዕለት ወደ ዕለት በአቅርቦት ዋጋ መናርና የመግዛት አቅም መዳከም ምክንያት የታየው የምግብ ጠረጴዛው መሳሳት በቂ ምስክር ነው፡፡
ግዮን፡- ብሔራዊ ባንክ በቅርቡ ለባንኮች የዶላር ዝግ ጨረታ አድርጓል፡፡ ይኼን አንዳንድ ባለሙያዎች ተገቢ አይደለም ብለዋል፡፡ ችግሩ ምንድነው ይላሉ?
ሙሼ፡- መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተግባራዊ ካደረገ በኋላ የሚፈጠረውን ክፍተት ለማረጋጋት የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ማድረጉ ተገቢ እርምጃ ነው፡፡ ለተወሰነ ጊዜም መቀጠል ነበረበት፡፡ ጨረታውም የተካሄደው በግልጽ ነው፡፡ ሀገራችን የውጭ ምንዛሪ በጨረታ መልክ ለግለሰቦች በቀጥታ የምታቀርብበት አሠራር የላትም፡፡
ግዮን፡- የፍራንኮ ቫሉታ ከተፈቀደ በኋላ ተመልሶ መታገዱ ለምን አስፈለገ?
ሙሼ፡- ፍራኮ ቫሉታ መጀመርያውንም ሲፈቀድ ትክክለኛ የፖሊሲ አቅጣጫ እንዳልነበር ማሳሰቢያ ተሰጥቶበታል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ምንጩ ባልታወቀበት ሁኔታ የፍራኮ ቫሉታን መተግብር የተፈቀደ የጥቁር ገበያ ግብይት ማለት ነው፡፡ ይህ እንደሚከተል እየታወቀ ፍራንኮ ቫሉታ እንዲቀጥል መፈቀዱ የጥቁር ገበያ ዋጋ ሕጋዊ ሥርዓት እንዲላበስ፣ የግዢና ሽያጭ ምጣኔው እንዲንርና እንዲስፋፋ አደርጓል፡፡ ውሳኔው ቢዘገይም አሁንም እንዲቋረጥ መደረጉ ተገቢ ነው፡፡ ያው እንደተለመደው በተሳሳተ የፖሊሲ አማራጭ ምክንያት ያለአግባብ የሚበለጸጉት በልጽገዋል፡፡ ዜጎችም የሚከፍሉትን ዋጋ በዚሁ ልክ ከፍለዋል፡፡
ግዮን፡- አንዳንድ ወገኖች መንግሥት በአንድ በኩል የብሪክስ አባል ኾኖ፣ ብሪክስ በዋነኝነት ለመመሥረቱ ምክንያት ከኾነባቸው ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጋር የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ውስጥ መግባቱ አይጣረስም ወይ የሚል ሐሳብ ያቀርባሉ? በእርሶ ዕምነት ይኽ እንዴት ይታያል?
ሙሼ፡- በዲፕሎማሲ ታሪካዊ ጠላትም ሆነ ወዳጅ የሚባል ጽንስ ሐሳብ የለም፡፡ ቅድሚያ የሚሰጠው የሃገር ጥቅም ብቻ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ላለች ትልቅ ሀገር ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ማኅበራት ጋር በኢኮኖሚያዊ፣ ልማታዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ዙርያ ጠንካራ ግንኙነት መመሥረቷ የሚደገፍና የሚጠበቅ ተግባር ነው፡፡
በተለያዩ አህጉራዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ከሀገራትና ከተቋማት ጋር መተባባርና መደጋገፍ አስፈላጊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እጅግ የተራራቀ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ርዕዮት ከሚያራምዱ እንደ ቻይና፣ ሩስያና አሜሪካና እንዲሁም መካከለኛው ምሥራቅ ሃገራት ጋር በኢኮኖሚያዊና ልማታዊ ጉዳዮች እየሰራቸው ነው፡፡ የብሪክስም ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡
ግዮን፡- በቅርቡ አይ.ኤም.ኤፍና መንግሥት የሁለት ወራት የኢኮኖሚ ሪፎርሙን አፈጻጸም በተመለከተ ሪፖርት አውጥተው ነበር፡፡ ከተቀመጡት አምስት የፖሊሲ ቅድመ ሁኔታዎች የመጀመሪያው የፖሊሲ ትግበራ መልካም ውጤት ተገኝቶበታል ተብሏል፡፡ እርሶ ሪፖርቱንና ጉድለቶቹን እንዴት ገመገሟቸው?
ሙሼ፡- ብሔራዊ ባንክ የሚያወጣቸው ሪፖርቶች መሠረት የሚያደርጉት መነሻዎችና የመረጃዎቹ ምንጮች ወይም የመረጃው ስፋትና ጥልቀት በተለያዩ ተቋማት ዘንድ በጥርጣሬ የሚታይ ነው፡፡ ስለዚህም በአብዛኛው የገለልተኛ ተቋማትን ምዘና ለንጽጽር መመልከት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አኳያ ግሽበቱ 17% ነው የሚባለው አሳማኝ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ዩ.ኤን.ዲ.ፒ እና ዓለም ባንክ (2024) ዓመታዊ ግሽበቱን 23.9 እና 23.6 እንደሆነ በዓመታዊ ሪፖርታቸው ላይ ገልጸውታል፡፡
ቁም ነገሩ ግን እሱ አይደለም፣ ግሽበት በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጫና ለመቀነስ እየተደረገ ያለው ጥረት በቂ አለመሆኑ ነው፡፡ ላለፉት በርካታ ዓመታት ገቢው ባለበት ሲረግጥ የቆየ ዜጋ በዓመታዊ ግሽበት መቀነስ ብቻ ችግሩ አለመፈታቱን መቀበልና ገቢውና ማሳደግና ምርታማነትንና አቅርቦትን ማሻሻል የግብይት ሥርዓቱን ማዘመን ላይ ሥራ መሠራት አለበት ነው፡፡
ጤናማ ኢኮኖሚ ባላቸውና የዜጎች ገቢ ግሽበቱን ተከትሎ በሚያድግባቸው ሀገራት የገንዘብ እንቅስቃሴን መገደብ በአስተማማኝ መልኩ ግሽበትን በመቆጣጠር የዜጎችን ኑሮ መታደግ ይቻላል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የዜጎች ገቢ ለዓመታት በማይሻሻልበት ሀገር ውስጥ የገንዘብ ቁጥጥርን በማጥበቅ ብቻ ግሽበትን መቀነስ ቢቻል እንኳ የዜጎች ገቢ ካላደገ ወይም ምርታማነት ካላደገ፣ የተሳለጠ የግብይት ስርዓታ ካልተዘረጋ፣ በተጓዳኝ ሳይሆን በቀጥታ የአቅርቦት ዋጋ እንዲቀንስ ካልተደረገ ለውጡ እዛው የመርገጥ ወይም የእንፉቅቅ ከመሆን አይዘልም፡፡
ግዮን፡- መንግሥት በአዲሱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምክንያት ለመንግሥት ሰራተኞች አደረግሁ ያለው የደሞዝ ጭማሪ፣ በየምዕራፉ ተተግባሪ ከሚኾኑት የፖሊሲው አቅጣጫዎች አንጻር ምን ያህል የሰራተኛውን ኑሮ መደገፍ የሚያስችል ነው ብለው ያምናሉ?
ሙሼ፡- ጭማሪ ሳይደረግ ግሽበት 64 በመቶ እድገት አሳይቶ በነበረት ሃገር ላይ ዓመታዊ ግሽበትን ብቻ ከግምት ውስጥ አስገብቶ የተደረገው ጭማሪ እጅግ በጣም የዘገየና ተመጣጣኝ ያልሆነ ነው፡፡ በዚህ ላይ ግብር የሚከፈልበት መነሻ ደሞዝ አለመሻሻሉና የገቢ ግብር ማዕቀፍና ተመን አለመለወጡ ሲደመርበት ጭማሪው ጭማሪ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ የገንዘብ የመግዛት አቅም በ100% ተኮማትሯል ፤ ቢያንስ በዛ ልክ ደሞዝ ማደግ ነበረበት፡፡
መንግሥት በዚህ ዓመት በአገልግሎቶች ላይ ብቻ ባደረገው ከ300% አስከ 1500% የሚደርስ ጫማሪ ገቢው በዛው ልክ አድጓል፡፡ የአዲስ አበባ መስተዳደር ከግብር የተገኘ ገቢን ብንመለከት እንኳን እስከ 45% ጫማሪ በማሳየት የመቶ ቢሊየኖችን ጣራ ተሸጋሯል፡፡ የፌደራል መንግሥትም ከግብርና ከአገልግሎት የሚገኘው ገቢ በዛው ልክ ጨምሯል፡፡ ከዚህ ቀደም ቫት የማይከፈልባቸው አገልግሎቶች በሙሉ በሙሉ ወደ ቫት ተካተዋል፡፡ መንግሥታዊ የልማት ተቋማት አየር መንገድ፣ ቴሌና መብራት ኃይል ወዘተ፣… ግዙፍ ጭማሪዎችን በማድረግ ገቢያቸውን በእጥፍ አሳድገዋል፡፡
ይህ ሁሉ የሚጠበቀው ከዜጎች ኪስ ለመሰብሰብ ነው፡፡ ዜጎች ይህንን ሁሉ ወጭ ተቋቁመው የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ሕይወት ለማቆየት ተመጣጣኝ ገቢ ያስፈልጋቸዋል፡፡ መንግሥት ተገቢውን የዜጎችን ሕይወት ሊያሻሽል የሚችል የደሞዝ ጭማሪ ለማድረግ ገቢዬ በቂ አይደለም የሚለው አመክንዮ አሳማኝ አይደለም፡፡ ድጎማ በማድረግ የተመጽዋችነት ባሕልን ከማዳበር ለድጎማና ለችሮታ የሚወጣውን ገንዘብ በደሞዝ መልክ ለዜጎች የጉልበትና የላብ ዋጋ መክፈል ተገቢ ነው፡፡
ግዮን፡- ከሀገር ውጪ የኾኑ ባንኮች በመጪዎቹ ጊዜያት ሀገር ውስጥ ተወዳዳሪ ኾነው ከመምጣታቸው ጋር ተያይዞ የሀገራችን የግል ባንኮች ዕጣ ፈንታ ምን ይኾናል ብለው ያስባሉ?
ሙሼ፡- ገበያው በነጻ ውድድር ላይ የተመሠረተ እስከሆነ ድረስ የውጭ ሀገር ባንኮች ሀገር ውስጥ በመግባታቸው ምክንያት በውድድር ውስጥ የቆዩ የግል ባንኮች ላይ የሚከሰት ምጸአትም ሆነ ተአምር የለም፡፡ በእርግጥ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የአሠራር ሥርዓት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና የአስተዳደራዊ ሥርዓት መሻሻልና መዘን ሊከሰት ይችላል፡፡
የውጭ ሀገር ባንኮች መምጣት ሥጋት ከሆነ ሥጋት ሊሆን የሚችለው ከውድድር ውጭ በድጋፍ በድጎማ ወይም በቤይል አውትና በተለያየ ጥበቃና ከለላ ለሚተዳደሩ መንግሥታዊና ብሔር ተኮር ባንኮች ሊሆን ይችላል፡፡
ከመንግሥት አኳያም ቢሆን የውጭ ባንኮች ሚና ተገድቦ በሂደት ሥራቸውን እያሰፉ የሚሄዱበት መንገድ እስካተዘረጋ ድረስ ኢኮኖሚውን በአብዛኛው ተቆጣጠረው በፖለቲካውም ኾነ በኢኮኖሚው ላይ ተጽእኖ ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ በተለያዩ ሀገራት ላይ እንደታየው የውጭ ሀገር ባንኮች መንግሥት እስከመገልበጥ የደረሰ ጣልቃ ገብነት ያካሄዱበት ዘመን ይታወሳል፡፡
ግዮን፡- በመጨረሻ ቀረ የሚሉትና እንደ ምክረ ሐሳብ የሚያስተላለፉት መልዕክት ካለ?
ሙሼ፡- በጥቅሉ በድጎማና በምጽዋት እድገትም ሆነ ለውጥ ይከሰታል የሚል እምነት የለኝም፡፡ የአንድ ሀገር ሕዝብ እንደልቡ ተንቀሳቅሶ እውቀቱና ክህሎቱን አቀናጅቶ በሰላማዊ መንገድ ማምረትና መሥራት በኢኮኖሚው ላይ ገንቢ ተጸእኖ ማምጣት የሚችልበትን ሥርዓት እስካልተዘረጋ ድረስ በእንፉቅቅ የሚሄዱ ነገር የሚቀጥል ነው፡፡ ለወራት ወይም ለአንድ ዓመት የተለያዩ የግብርና ቅናሽና የድጎማ የምገባ ሥርዓት በመዘርጋት ሕይወት የማቆየት ሥራ መሥራት ይቻላል፡፡
ሕዝባችን ከእንደዚህ ዐይነት ሰርቶ እንዳልሰራ ላቡን አፍስሶ እንዳላፈሰሰ ከሚሆንበት የጥገኝነትና የእጀ ሰባራነት ሥነ ልቦና ተጽዕኖ አላቆ በፈጠራ የታገዘ አምራችና ምርታማ ዜጋ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለሥራውና ለላቡም ተገቢውን ክፍያ የሚያገኝበት ሥርዓት በመዘርጋት ሥራን ሳይንቁ በመሥራት ለውጥ ይመጣል የሚል ማኅበረሰብ መፍጠር አለብን፡፡
እጅ ተመልካችነትና ተመጽዋችንት ሀገራችን ትውልዱን እየጎዳ ነው፡፡ ሥራ ጠልነት፣ ራስን ለሥራ አለመዘጋጀትና ያላሰሩበትን የሰው ኃብትና ጥሪት መመኝት፣ ሙስናና ሌብነት መገለጫችን ወደ የመሆኑ ጉዞ በአስደናቂ ፍጥነት ተጀምሯናል፡፡
በጊዜ ጠንካራ የሥራ ባህል ካላዳበርንና ምርታማነትን ለማሳደግ ሁሉንም ዓይነት መስዋዕትነት ካልከፈልን እንደ ሀገርና እንደ ሕዝብ ተመጽዋቸና ስደተኛ፣ የትንንሽ ሀገራት መጫወቻና መዘባበቻ መሆናች ይቀጥላል፡፡ ለዚህ ደግሞ አስተማማኝ ዘላቂነት ያላቸው እሴት ፈጣሪ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች ለመተግብር ሰላምንና የዜጎችን ደህንነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡
ግዮን፡- ለነበረን ቆይታ ከልብ እናመሠግናለን፡፡
———-
ቅጽ 6 ግዮን ቁጥር 218 ሕዳር 14 ቀን 2017 ዓ.ም
