የውጭ ዜጎች በሪል ስቴትና ኮንስትራክሽን ዘርፍ ንብረት እንዲያፈሩ የሚያስችል ስምምነት፣ የኢትዮጵያ የሪል ስቴት አልሚዎች ማኅበርና ሃርቨስት ሰርክል ኢንክ ተፈራረሙ::
ስምምነቱ የተፈረመው በአሜሪካና በአፍሪካ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ፣ የኢንቨስትመንትና የሪል ስቴት ትስስር ለማጠናከር በሚሠራውና ዋና መሥሪያ ቤቱ አሜሪካ በሆነው ሃርቨስት ሰርክል ኢንክ (Harvest Circle Inc.) አማካይነት፣ በሪል ስቴትና በኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ ያተኮረ የንግድና የኢንቨስትመንት ኤክስፖ በመጪው ሐምሌ 18 እና 19 ቀን 2018 ዓ.ም. በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ እንደሚካሄድ በተገለጸበት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
በመግለጫው የአገር ውስጥ ሪል ስቴት አልሚዎች የዋጋ ቅናሽ በማድረግ በአሜሪካ የቤት ሽያጭ እንዲፈጽሙ እንደሚያስችል ተገልጿል።
የኢትዮጵያ የሪል ስቴት አልሚዎች ማኅበር ዋና ጸሐፊ ዝናቡ ተበጀ (ኢንጂነር)፣ የውጭ አገር ዜጎች በኢትዮጵያ የማይንቀሳቀስ ንብረት እንዲኖራቸው የሚያስችል አዋጅ መውጣቱን አስታውሰዋል።
የውጭ ዜጎች እስከ 150 ሺሕ ዶላር ድረስ ሀብት ማፍራት እንደሚችሉ ያወሱት ዝናቡ (ኢንጂነር)፣ በስምምነቱ መሠረት የሚደረገው ኤከስፖ የውጭ አገር ዜጎችና ዳያስፖራዎች በዘርፉ የሕዝብ አመኔታ ኖሯቸው ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ግዥ እንዲፈጽሙ ለማድረግ እንደሚያገለግል ተናግረዋል።
ለዚህም ሪል ስቴት ሲመርጡ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ከማድረግ ጀምሮ፣ ዋና ዋና የብቃት አመላካቾችን በማየት ውሳኔያቸውን እንዲያሳልፉ ለማድረግ ከሀርሽስት ሰርክል ጋር የጋራ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ዋና ጸሐፊው ገልጸዋል፡፡
በተለይ ባንኮች ለዳያስፖራው ማኅበረሰብ የብድር አማራጮችን በማመቻቸት ቤት የሚገዛበትን ዕድል እንዲፈጥሩ እንደሚሠራ ጨምረው ተናግረዋል።
ኤክስፖው በአገር ውስጥ ያለውን የቤት ፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣምን መቅረፍ የሚያስችሉ ተሞክሮዎችን ወደ አገር ውስጥ ማስገባት የሚያስችል መሆኑን አስረድተዋል።
ኤክስፖው በዘርፉ ያለውን የአቅርቦት ክፍተት ለመሙላትና ተዓማኒነትን ወደ መሬት ለማውረድ ይረዳል ተብሎ እንደሚጠበቅ፣ ማኅበሩም ወደ ኢትዮጵያ የተሻለ ኢንሸስትመንትና የውጭ ምንዛሪ እንዲመጣና ቀጥተኛ የገበያ ትስስር እንዲጎለብት እንደሚሠራ ጨምረው ገልጸዋል።
የሃርሸስት ሰርክል ኢንክ ተወካይ ቅድስት ወልደ አምላክ በበኩላቸው፣ በዘርፉ በታማኝነት የሚሠሩ የሪል ስቴት ኩባንያዎች በኤክስፖው እንዲገኙ ለማስቻል ከኢትዮጵያ የሪል ስቴት አልሚዎች ማኅበር ጋር እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ኤክስፖው አንድ ዳያስፖራ ወደ አገር ቤት መጥቶ ቤት ለመግዛት የባንክ አካውንት ከመክፈት ጀምሮ ያጋጥሙት የነበሩ ውስብስብ ውጣ ውረዶችን የሚያስቀር፣ በአንድ ጣሪያ ሥር ግዥ እንዲፈጽም ለማስቻል በማሰብ ጭምር የተደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
የባንክና የሕግ አገልግሎት በአንድ ጊዜ ማግኘትንም እንደሚጨምር ጠቁመዋል።
በተለይ በውጭ የሚገኙ ዳያስፖራዎች ለቤት ብለው በሚልኩት ገንዘብ ምክንያት ቤተሰቦቻቸውን ጨምረው ይታለሉ የነበረበትን ሁኔታ የሚያስቀር እንደሚሆን ገልጸዋል።
ለኢትዮጵያውያን የሪል ስቴት አልሚዎች ደግሞ የኢንቨስትመንት ዕድል ይዞ እንደሚመጣ ሳይገልጹ አላለፉም።
በሪል ስቴትና በኮንስትራክሽን ላይ መሠረት ያደረገ የአሜሪካና የኢትዮጵያ የጋራ መድረክ መክፈት፣ ለዳያስፖራውና ለዓለም አቀፍ ኢንሸስተሮች የፋይናንስ፣ የሞርጌጅና የኢንሹራንስ አማራጮችን ማመቻቸት፣ በኢትዮጵያ ያሉ የመኖሪያ፣ የንግድና የሕዝብ ልማት ፕሮጀክቶችን ማስተዋወቅ፣ በአሜሪካና በኢትዮጵያ አልሚዎች፣ ተጠቃሚዎችና የፋይናንስ ተቋማት መካከል አጋርነትን ማበረታታት፡ ዘላቂና በግል ዘርፍ የሚመራ የከተማ ልማትን መደገፍ ሌሎች የኤከስፖው ዓላማዎች መሆናቸው በመግለጫው ተነግሯል፡፡
reporter
