ኢትዮ ቴሌኮምና የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ የተቀናጀ የግብርና እሴት ሰንሰለት መረጃ ለማቅረብ የሚያስችል ስምምነት አደረጉ።
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ እንደገለጹት፣ የግብርናውን ዘርፍ ለማገዝ ቀደም ሲል የግብርና እሴት ሰንሰለትን ከምርት እስከ ገበያ የሚያስተሳስር ቴክኖሎጂ እንዲሁም ለአርሶ አደሩ ፋይናንስ ተደራሽ ለማድረግ የሚያግዙ የዲጂታል ሥራዎች መከናወናቸው ገልፀዋል፡፡
ከኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ጋር የተደረገዉ ስምምነትም በግብርናዉ ዘርፍ ያሉ ተዋናዮችን ሁሉ የሚያገናኝ እና በርካታ ችግሮችን የሚፈታ መሆኑን አንስተው አዳዲስ የሥራ ዕድሎችም እንዲፈጠሩ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡
ስምምነቱ የግብርናውን ዘርፍ ዲጂታላይዝ ለማድረግ እና በዘርፉ ያለውን ሰንሰለት ለማስተሳሰር እንዲሁም በቴክኖሎጂ እንዲደገፍ ለማድረግ እንደሚያግዝ ጠቁመዋል፡፡
የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ጌቱ ገመቹ በበኩላቸዉ፣ የግብርናዉ ዘርፍ ለኢኮኖሚ የሚያበረከትዉ አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አንስተው የኦሮሚያ ክልል መንግስት ግብርናዉን በቴክኖሎጂ መደገፍና በዲጂታላይዜሽን የማስተሳሰር ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የተደረሰው የትብብር ስምምነትም የዚሁ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል። ስምምነቱ አርሶ አደሩ የወቅቱን የገበያ ዋጋ ጨምሮ በርካታ መረጃዎችን የሚያገኝበት እንዲሁም ከባህላዊ ግብርና ወደ ዕውቀት ተኮር ግብርና የሚያሸጋግር እንደሆነም ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም ስምምነትቱ ተግባራዊ ሲሆን የሚኖረዉ መተግበሪያ የአየር ሁኔታን፣ በቦታዉ ላይ ወጤታማ የሚያደርጉ አዝርቶችን የመምከር፣ በሽታን የመጠቆም እና የገበያ መረጃዎችን በመስጠት አርሶ አደሩን ከኪሳራ የሚታደግ መሆኑ አብራርተዋል፡፡
NBCEthiopia
