ዶ/ር ዳንኤል በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁ ሂዩማን ራይትስ ዎች ጠየቀ

Date:



የጤና ባለሙያዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ካደረጉት የስራ ማቆም ጋር በተያያዘ በባህር ዳር ከተማ በእስር ላይ የሚገኙት ዶ/ር ዳንኤል ፈንታነህ በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ የመብት ተሟጋች ድርጅት ሂዩማን ራይትስ ዎች ጠይቋል።

ዶ/ር ዳንኤል በቅርቡ የተሻለ የሥራ ሁኔታን፣ በቂ ደሞዝን እና ለሀኪሞች ደህንነት ጥበቃ እና ከለላ እንዲሰጥ በመጠየቅ በመላው ኢትዮጵያ በጤና ባለሙያዎች ሲደረግ በነበረው እንቅስቃሴ ላይ ንቁ ተሳታፊ እንደነበረ ድርጅቱ ትናንት ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታውሷል።

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመጨረሻ አመት የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊቲ ሬዚደንት ዶ/ር ዳንኤል ፈንታነህ በአማራ ክልል መዲና ባህር ዳር ከተማ ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ያስታወቀው መግለጫው፤ የክልሉ ፖሊስ የእጅ ስልካቸውንና ላፕቶፓቸውን መውሰዱን አመልክቷል።

ሂዩማን ራይትስ ዎች ዶክተር ዳንኤል ዓርብ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ.ም ፍርድ ቤት ቀርበው “የስራ ማቆም አድማ አነሳስተዋል፣ አስተባብረዋል እንዲሁም በሰው ህይወት ላይ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል”  በሚል ፖሊስ ክስ እንዳቀረበባቸው ገልጿል።

በሌላ ቀጠሮ ለሁለተኛ ጊዜ ሀሙስ ሰኔ 26 ቀን 2017 ዓ.ም ፍርድ ቤት መቅረባቸውን  የገለጸው የመብት ተሟጋች ድርጅቱ መግለጫ፤ አያይዞም ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ክሱን የሚያጠናክርበትን ማስረጃ እንዲያቀርብ ተጨማሪ አምስት ቀናት እንደፈቀደለት አስታውቋል።

መግለጫው አክሎም ዶ/ር ዳንኤል በአሁኑ ሰዓት በባሕር ዳር ከተማ በሚገኘው ሰባታሚት ማረሚያ ታስሮ እንደሚገኝ ጠቅሶ፤ “የተሻለ የሥራ ሁኔታና ክፍያ እንዲኖር በሰላማዊ መንገድ ጥሪ በማቅረቡ ብቻ መታሰር የለበትም፤ ፖሊስ በአስቸኳይ ሊለቀው ይገባል” ሲል ጠይቋል።

“የኢትዮጵያ መንግስት እንደ ዶ/ር ዳንኤል ከመሳሰሉ ቅሬታዎቻቸውን በሰላማዊ መንገድ ከሚያቀርቡ የህክምና ባለሙያዎች ጋር መነጋገር አለበት” ያለው ሂውማን ራይትስ ዎች፤ “አሁን ያለው አካሄድ ግን ኢትዮጵያን ለመናገር እና ሀሳብን ለመግለጽ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ከሆኑ ቦታዎች መካከል አንዷ መሆኗን ያረጋግጣል” ብሏል።

ዶ/ር ዳንኤል ከመታሰሩ አራት ቀናት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ከጥቂት የጤና ባለሙያዎች ጋር ተገናኝተው እንደነበረ ያወሳው መግለጫው፤ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ የጤና ባለሙያው ያነሳው ጥያቄ ተገቢ መሆኑን አምነው ቢቀበሉም፣ ጥያቄውን ነጩን ጋዎን ወደ ፖለቲካዊ መሣሪያ የለወጡ የፖለቲካ ትርፍ  ጠባቂዎች እንደተቆጣጠሩት ተናግረዋል” ብሏል።

“የጤና ማኅበራት እና የንቅናቄው አስተባባሪዎች ላይ የሚካሄደው አፈና ገና አላበቃም” ያለው ሂውማን ራይትስ ዎች፤ የኢትዮጵያ መንግስት በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ የጤና ባለሙያዎችን ጥያቄ በይፋ የሚደግፈውን የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ማኅበርን ማገዱን አስታውሷል።

ሂዩማን ራይትስ ዎች ሰኔ 19 ቀን 2017 ባወጣው መግለጫ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በቁልፍ የጤና ባለሙያዎች ማህበራት ላይ የተጣለውን እገዳ በአስቸኳይ እንዲያነሳ እና ያልተፈቱ የጤና ባለሙያዎችን ጥያቄዎች እንዲፈታ መጠየቁ አይዘነጋም።

አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ ሰኔ 23 ቀን 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በባህር ዳር ከተማ በቁጥጥር ስር አውሎ ለእስር የዳረጋቸውን ዶ/ር ዳንኤል ፈንታነህ “ያለምንም ቅድመ ሁኔታና በአፋጣኝ” ሊፈታቸው ይገባል ሲል መጠየቁን መዘገባችን ይታወሳል።

የዶ/ር ዳንኤል ፈንታነህ “የዘፈቀደ እስር አሳስቦኛል” ያለው አምነስቲ “እስሩ የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ለህግ የበላይነት ተገዢ ባለመሆን የግለሰቦችን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ በነጻነት የመሰብሰብ መብትን ባለማክበር በተደጋጋሚ ህግ እንደሚጥሱ ማሳያ ነው” ሲል ተችቷል።

አምነስቲ በመግለጫው “ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል ግለሰቦችን እያሰሩ መክሰስ አሳሳቢ ልማድ ሁኗል” ሲል አስጠንቀቋል፤ እንዲህ ያሉ ድርጊቶች “የህግ የበላይነትን ከመሸርሸራቸው ባለፈ በሀገሪቱ ውስጥ ፈላጭ ቆራጭ የሆኑ አካሄዶች እንዲለመዱ ያደርጋል” ሲልም አሳስቧል።

ዶ/ር ዳንኤል በቁጥጥር ስር የዋሉት የጤና ባለሙያዎች የተሻሻለ ክፍያ፣ የተሻለ የስራ ሁኔታ እና ሌሎች ጥያቄዎቻቸው እንዲመለስላቸው ከግንቦት 4 ጀምሮ ሀገራ አቀፍ የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው።

ዶ/ር ዳንኤል በጤና ባለሙያዎች እና በህብረተሰቡ ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት ያገኘውን “ዶ/ር ደቦል” የተሰኘ የፌስቡክ ገፅን በመጠቀም በጤና ባለሙያዎች ንቅናቄ ላይ ጉልህ ሚና ተጫውተዋል።

እስሩን በተመለከተ የዶ/ር ዳናኤል የቤተሰብ አባል “ግራ ገብቶን ቁጭ ብለናል፤ እንደ ማንኛውም ጤና ባለሙያ ነው ጥያቄ የጠየቀው ያጠፋው ጥፋት የለም” ሲሉ ለአዲስ ስታንዳርድ ተናግረዋል።

ዶ/ር ዳንኤል “ከልጅነታቸው አንስተው በማህበረሰቡ ዘንድ የት ይደርሳል የተባለ ልጅ ነው” ያሉት እኚሁ የቤተሰብ አባል አያይዘውም “የህክምና ባለሙያዎችን ሊያግዙ የሚችሉ መጽሐፍቶችን በማዘጋጀት ሳይቀር ብዙ ህልም ያለው ነው” ብለዋል።

በአዲስ ስታንዳርድ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ሴቶችን በቤት ውስጥ በማገዝ  መልካም ማህበረሰብ መፍጠር ተጀምሯል

በቤት ውስጥ የሚሠሩ ተግባራትን ተከፋፍሎ በመሥራት ሴቶችና እናቶችን መደገፍ...

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

የእግዚአብሔር ሕዝብ ጉባኤ፣ የጌታችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አካልና የመንፈስ...

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ ቅርሶች ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል

በመቅደላ ጦርነት ጊዜ የተዘረፉ የአጼ ቴዎድሮስ የፀጉር ቁንዳል እና...

ፈረንሳይ የ54 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዩሮ ብድር ለመስጠት ተስማምታለች

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው ሀገራቸው ለኢትዮጵያ የኃይል...