የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በሀገሪቱ ገዥ ፓርቲ ታላቅ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር የሀገሪቱን የኑክሌር ጦር መሣሪያ በከፍተኛ ሁኔታ ለማስፋፋትና ለማጠናከር ጥሪ አቅርበዋል።
እ.ኤ.አ ከጁን 20 እስከ 22 ቀን 2026 ለሦስት ቀናት በተካሄደው የሰሜን ኮሪያ የሠራተኞች ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ 9ኛው ምልአተ ጉባኤ ላይ መሪው ኪም ጆንግ ኡን እንደገለጹት፣ የሀገሪቱ የኑክሌር ኃይል ለሰሜን ኮሪያ ወታደራዊ ሉዓላዊነትና ጠላትን የመከላከል ስትራቴጂ ዋነኛው ምሰሶ ነው።
በመሆኑም ፒዮንግያንግ «ዓለምን የመቅደም» ግብ ሰንቃ ጠንካራ የመከላከያ አቅሟን «ያለ ምንም ማቋረጥ» መገንባት እንዳለባት መሪው በጥብቅ አሳስበዋል።
ኪም ጆንግ ኡን በዓለም ዙሪያ ለሚታዩት ግጭቶች አሜሪካንና አጋሮቿን ተጠያቂ ያደረጉ ሲሆን፣ በተለይም አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ በጋራ የሚያደርጉት የኑክሌር ስምምነትና ወታደራዊ ዝግጅት በኮሪያ ልሳነ ምድር ላይ ያለውን የጸጥታ ሁኔታ እጅግ አደገኛ እያደረገው ነው ብለዋል።
የሀገሪቱን የኑክሌር ኃይል ያለማቋረጥ ማሳደግና እንደ ኑክሌር ታጣቂ ሀገርነት ያለውን አቋም በተግባር ማሳየት፣ አሁን ያለውን የማይገመትና ውስብስብ ዓለም አቀፋዊ ወታደራዊ ሁኔታ ለመቋቋም ብቸኛውና ትክክለኛው መንገድ መሆኑን በስብሰባው ላይ ተገልጿል።
ይህ የፒዮንግያንግ አቋም ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ጦር መሣሪያዋን እንድትተው የሚቀርቡ ማናቸውንም ድርድሮች ሙሉ በሙሉ ውድቅ ማድረጓን በድጋሚ ያረጋገጠ ክስተት ሆኗል።
ሮይተርስ የሰሜን ኮሪያውን ይፋዊ የዜና ወኪል ኬሲኤንኤን (KCNA) ዋቢ በማድረግ እንደዘገበው፣ ምንም እንኳን መንግሥት ቀጣይ ስለሚወሰዱት የኑክሌር እርምጃዎች ግልጽ ዝርዝር መረጃዎችንና አዳዲስ ቁጥሮችን ይፋ ባያደርግም በስብሰባው ላይ ግን እጅግ ከፍተኛ ትኩረት የሳቡ አዳዲስ ወታደራዊ ውሳኔዎች ተላልፈዋል።
ሀገሪቱ የተለመዱ ባህላዊ የጦር መሣሪያዎችን ክምችት ከማሳደግ ባለፈ፣ የደቡብ ኮሪያን ዘመናዊ የጦር መርከቦች አቅም የሚበልጥ 10 ሺህ ቶን የሚመዝን እጅግ ግዙፍና ስትራቴጂካዊ የሚሳይል ተኳሽ የጦር መርከብ (Strategic Guided Missile Cruiser) ግንባታን በፍጥነት እንድታጠናቅቅ ትእዛዝ ተላልፏል።
ይህ የባሕር ኃይል መስፋፋት ሰሜን ኮሪያ በባሕር ላይ የኑክሌር ሚሳይል መተኮሻ መድረኮችን ለማጠናከር የምታደርገው ጥረት አካል ተደርጎ የተወሰደ ሲሆን፣ በኮሪያ ልሳነ ምድር ያለውን ወታደራዊ ውጥረት ይበልጥ ያባብሰዋል ተብሎ በከፍተኛ ሁኔታ ተሰግቷል ።
