ፍሬዘር ተሾመ
(የኤሮ አይረን ኢንቴሪየር ዲዛይንና ኮንስትራክሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ)
በሀገራችን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኢንቴሪየር ዲዛይን መስክ ተፈላጊ እየኾነ መጥቷል፡፡ ቴክኖሎጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየረቀቀ ከመሔዱ አንስቶ፣ አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች ትኩረት ሳቢ እየኾኑ መምጣት፣ በርካቶች በዘርፉ ለመሠማራት ፍላጎት እንዲያድርባቸው ምክንያት ኾኗል፡፡ ዛሬ ላይ በመዲናችን አዲስ አበባ እጅግ ውብ ከኾኑ ሕንጻዎች እና ከሚያምሩ ስቱዲዮዎች በስተጀርባ የእነኚህ ኢንቴሪየር ዲዛይን አሻራዎች በስፋት ይገኛሉ፡፡ በዛሬው ቆይታችንም የዘርፉን ዕውቀት ባሕር ተሻግረው ከቀሰሙ በኋላ በሀገራቸው ተሰማርተው ውጤታማ ተግባር እያከናወኑ ካሉ ተቋማት ከፊት የሚጠቀሰው የኤሮ አይረን ኢንቴሪየር ዲዛይንና ኮንስትራክሽን መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ ፍሬዘር ተሾመ ከጋዜጠኛ ፍቃዱ ማህተመ ወርቅ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል ፡፡ መልካም ንባብ፡፡
ግዮን፡- በቅድሚያ ራስዎን ለአንባቢያን በማስተዋወቅ ቢጀምሩ?
ፍሬዘር፡- ፍሬዘር ተሾመ እባላለሁ፡፡ ድጅታችን ‹‹ሪቪዚት ኢንስቲትዩሽን ኦፍ ዲዛይን›› ይባላል፡፡ ይኼ ድርጅት እንዲመሠረት ዋናው ባለሚና ግን ‹‹ኤሮ አይረን ኢንቴሪየር ዲዛይንና ኮንስትራክሽን›› ነው፡፡ እኔም የዚህ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅና መሥራች ነኝ፡፡ የዚህን ተቋም ልምድ መሠረት በማድረግም አሁን ያለንበትን የማሰልጠኛ ተቋም ለመመሥረት ችያለሁ፡፡
ግዮን፡- ድርጅቱ ከተቋቋመ ምን ያህል ዓመት ኾነው? ምን ምን ሥራዎችንስ ሠርተችኋል?
ፍሬዘር፡- ድርጅቱ ከተቋቋመ ስምንት ዓመታት ኾኖታል፡፡ በዚህ ስምንት ዓመት ውስጥም የመኖሪያ ቤቶችን ዲዛይን አድርገናል፡፡ የንግድ እንቅስቃሴ ያለባቸውን ሕንፃዎች፣ ሆስፒታልና መሰል ሥራዎችን ዲዛይን አድርገን ሠርተን አስረክበናል፡፡ ዲዛይን ለሚፈልጉ ደንበኞች ዲዛይን አድርገን ሠርተን ለበርካታ ደንበኞችም አስረክበናል፡፡
ግዮን፡- የኢንቴሪየር ዲዛይን ትርጉም ምን ማለት ነው?
ፍሬዘር፡- የቃሉ ትክክለኛ ትርጓሜ የውስጥን ነገር ማሳመር የሚል ነው፡፡ የመኖሪያ ቤትም ይሁን የቢሮ ሕንፃ ውስጡን የማሳመር ሥራ ኢንቴሪየር ዲዛይን ይባላል፡፡ ኢንቴሪየር ዲዛይን በጣም በርካታ ጥቅሞች አሉት፡፡ ለምሳሌ ሥነ ልቦናን ያርቃል፡፡ በሰው ልጆች ደህንነት ላይም ከፍ ያለ ጥቅም አለው፡፡ ከዚህ ባለፈም በቤት ውስጥ ያለ ውበትን ለማምጣት ቀለም፣ ብርሃን፣ የቤቱ አጠቃላይ ሴትአፕ እንዲስብና መንፈስ እንዲታደስ ያደርጋል፡፡ ቤት ውስጥ የምንጠቅማቸው ቀለማትና አጠቃላይ ነገሮች ዲዛይን መደረግ ይኖርባቸዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ለምሳሌ ጠረጴዛና ወንበሮች አቀማመጥ፣ የብርሃን አጠቃቀማቸው ዲዛይን መደረግ ይኖርባቸዋል፡፡ ያ ካልሆነ ግን በሥራ ላይ ያለንን ውጤታማነት ይቀንሳል፡፡ ሰዎች እንዲቁነጠነጡ፣ የሥራ ተነሳሽነታቸው እንዲቀንስ ያደርገዋል፡፡
ግዮን፡- የትምህርት ዝግጅትዎ ምን ነበር?
ፍሬዘር፡- የትምህርት ዝግጅቴ ሲቪል ኢንጂነሪንግ ነው፡፡ ነገር ግን መጀመሪያ ትምህርቴን ተመርቄ በዘርፉ ሥራ ባለማግኘቴ ለአንድ ዓመት ሥራ የሠራሁት ኢንቴሪየር ዲዛይን የሚሠራ ድርጅት ውስጥ ነበር፡፡ ስለዚህ ሥራውን ሳየው በጣም ደስ ይላል፡፡ ከዛም በፊትም ለሥራው የተለየ ስሜት ነበረኝ፡፡ በዚህ ምክንያትም የኢንቴሪየር ዲዛይን ሥልጠና ወስጄ ወደራሴ ሥራ ገባሁ፡፡
ግዮን፡- ወደዘርፉ ለመግባት ያነሳሳዎት ነገር ምንድነው?
ፍሬዘር፡- እውነት ለመናገር በዘርፉ ላይ የፈጠራ ችግር ክፍተት አለ፡፡ በዘርፉ ከቢዝነስ አንፃር ያለውን ክፍተትም በደንብ ስላየሁት ወደ ሥራው እንድገባ አስችሎኛል፡፡ የምንሠራባቸው የኢንቴሪየር ዲዛይን ሶፍትዌሮችም እኛ ጋር ከደረሱ በኋላ ቶሎ ወደ ሥራ አንገባባቸውም፡፡ ለምሳሌ ሶፍትዌሩ ውጭዎች በደንብ ተጠቅመውት ሊጥሉት ሲሉ ነው እኛ ጋር እንደ አዲስ የሚጀምረው፡፡ ይሄ ልምድ ደግሞ መቅረት ይኖርበታል፡፡ ምክንያቱም ዘመኑን የሚዋጅና የሚመጥን ሥራ ሲኾን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሥራ ይኖረናል፡፡ የእኛም ሀገር ከዘመኑ ጋር የሚራመድ የኢንቴሪየር ዲዛይን ሥራ ያስፈልጋታል፡፡
ግዮን፡- ወደ ሥራው ከገባችሁ በኋላ ከሀገራችን ባሕልና ሁኔታ ጋር የሚስማማ የኢንቴሪየር ዲዛይን ሶፍትዌር አበልጽጋችኋል?
ፍሬዘር፡- ቀደም ሲል የምንጠቀመው በውጭው ዓለም የበለፀጉ አዳዲስ ሶፍትዌሮችን ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን አዳዲስ ሥራዎችን ለማከናወን እየተዘጋጀን ነው፡፡ የተቋሙ ባለቤት እኔ ብኾንም በዘርፉ እውቀት ያላቸው ሰዎች የሚሳተፉበት ነው፡፡ ስለዚህ በሶፍትዌር ማበልፀጉ ላይ ብዙ ወገኖች አሉ፡፡ በመኾኑም የራሳችንን የሶፍትዌር ሥራ ለመፍጠር እየተጋን ነው፡፡
ግዮን፡- ሶፍትዌሮቹን ስታበለጽጉ ምን ሀገርኛ ይዘት እንዲኖራቸው ነው የምትፈልጉት?
ፍሬዘር፡- ሶፍትዌር ማበልጸግ፣ ብዙ ነገር የሚፈልግ ትልቅ ሳይንስ ነው፡፡ እኛም ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ጋር በመተባበር የውጭ ሥልጠናዎችንም በመውሰድ ነው ሶፍትዌሩን ለመፍጠር ያቀድነው፡፡
ግዮን፡- በዚህ ዙሪያ ከመንግሥት ጋር አብሮ ለመሥራት የተጓዛችሁበት ሂደት ከነበረ ምን ይመስላል?
ፍሬዘር፡- ለጊዜው የሥልጠና ሂደቱን በበላይነት የሚቆጣጠረው ‹‹የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና›› ወይም TVET ነው፡፡ የእኛ ክፍለ ከተማ ቦሌ በመኾኑ የቦሌው TVET ነው እየተከታተለን ያለው፡፡ ወደፊት ግን እያሰብን ያለነው ከሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ለመሥራት ነው፡፡ ምክንያቱም እኛ እቅድ የያዝነው በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በዩኒቨርሲቲና በኮሌጅ ደረጃ ኢንቴሪየር ዲዛይን የኾነ ማሰልጠኛ ተቋም መገንባት ነው፡፡ ስለዚህ ይህን እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ ግዴታ ከመንግሥት ጋር መሥራት ይኖርብናል፡፡ የዘርፉ የመንግሥት አካልም እኛን የመደገፍ ኃላፊነት አለበት፡፡
ግዮን፡- ኤሮ አይረን ኮንስትራክሽን እስካሁን የሠራቸው የኢንቴሪየር ዲዛይን ሥራዎች ምን ምን ናቸው? ለታዋቁ ሰዎች የሠራችሁት ካለም ብትጠቅሱልን? የመጀመሪያ ሥራዎቻችሁስ የእነማን ናቸው?
ፍሬዘር፡- በዚህ ስምንት ዓመት ውስጥ ከ200 በላይ ፕሮጀክቶችን ሠርተናል፡፡ ይህ ማለት መኖሪያ ቤትን እና ሕንፃን ጨምሮ ነው፡፡ በተቋማት ደረጃ ግን ሴማ ሆስፒታል፣ ኔክሰስ ሆቴልና በርካታ ተቋማትን ሠርተናል፡፡ በግለሰብ ደረጃ ደግሞ የሰይፉ ፋንታሁንን ስቱዲዮ ጨምሮ አሁን አገልግሎት እየሰጠ ያለውን የመቄዶንያ አረጋውያን መርጃ ማዕከልን ከዲዛይን እስከ ስቱዲዮ ግንባታ ድረስ አለንበት፡፡ ለእነ መንሱር አብዱልቀኒ፣ ለእነ አብነት አጎናፍርም አሁን ላይ በተመሳሳይ እየሠራን ነው፡፡
ግዮን፡- ብዙ ከመሥራትዎ አኳያ ምሥጋናም ይሁን ሌላ የተሰጥዎ ዕውቅና አለ?
ፍሬዘር፡- ከሁሉም በላይ ደንበኞች በእኔ በኩል ሥራውን አጠናቅቄ ስጨርስ የሚያሳዩት የደስታ ስሜት ለእኔ ሽልማት ነው፡፡ ሥራው አልቆ ገጣጥመን ባለቤቶቹን ስናሳያቸው በጣም ደስተኛ ይኾናሉ፡፡ እነሱ ላይ የምናየው እርካታ ደግሞ ለእኛ ትልቅ ስጦታ ነው፡፡ ለምሳሌ አንዱ ደንበኛችን ኃይሌ ጋርመንት አካባቢ መኖሪያ ቤቱን ሰርተንለት ስርፕራይዝ አድርጎኛል፡፡ በሥራው ላይ የተሳተፉ ሠራተኞችን ሁሉ ሰብስቤ እንዳቀርብ አዞኝ አስደናቂ ሰርፕራይዝ አድርጎኛል፡፡ ለእኔም በሠራተኞቼ ፊት ትልቅ ብራንድ ሰዓት ሸልሞኛል፡፡ ሌሎችም ሰዎች እንዲሁ በርካቶች ከአሜሪካ እንደ ላፕቶፕ ያሉ ልዩ ልዩ ስጦታዎችን አምጥተው ይሸልሙኛል፡፡
ግዮን፡- ለሥራ ከምትገናኝዋቸው ባለቤቶች ጋር የመግባባት ሂደት ላይ እንቅፋት ገጥሟችሁ ያውቃል? እንዴት ነው ስለሥራችሁ ግንዛቤ የምትሰጡት?
ፍሬዘር፡- የደንበኞችን ፍላጎት በመስማት ከኢንቴሪየር ዲዛይን ሙያ አንፃር ይኼ እንዲህ ቢኾን የሚለውን ሃሳብ እናቀርብላቸዋለን፡፡ በመጀመሪያ የምናደርገው የደንበኞቻችንን ፍላጎት መጠየቅ ነው፡፡ ለምሳሌ የአንድ ሰው ቢሮ ስንሰራ የአራት ሰው መቀመጫ ፈልጎ የስምንት ሰው አድርገን ብንሠራው አለመግባባት ይፈጥራል፡፡ ስለዚህ በቢሮም ይሁን በመኖሪያ ቤት ወይም በተቋማት፣ ባለቤቶቹ በሚፈልጉት ዓይነት የቀለም ምርጫ የመብራት ሁኔታና የዲዛይን ስታይል መሠረት የተለያዩ ዲዛይችን በማሳየት ከደንበኛችን ጋር እንግባባለን፡፡
ግዮን፡- በቅርቡ የማሰልጠኛ ተቋም እንደምትከፍቱ አስታውቃችኋል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ቢነግሩን?
ፍሬዘር፡- ‹‹ሪቪዚት ኢንስቲትዩሽን ኦፍ ዲዛይን›› የሚባል የማሰልጠኛ ተቋም ከፍተናል፡፡ ዋናው ዓላማችን የኢንቴሪየር ዲዛይን ማሰልጠን ብቻ ሳይኾን ለኢንቴሪየሮች እና ለሶፍትዌር ኢንጂነሮችም የሚሰጥ ኮርስን ማቅረብ ነው፡፡ የትምህርት ዝግጅታቸው አርክቴክትና ኢንጂነር ለኾነ ብቻ የሶፍትዌር ማበልጸጊያ ሥልጠና ለመስጠትም አቅደናል፡፡ ሙሉ ሥልጠናዎቹ ግን እነኚህ ናቸው፡፡ የውስጥ ዲዛይን (መታወቂያ)፣ ሞዴሊንግ ሶፍትዌር (Revit)፣ ፖስት ፕሮዳክሽን (PP) እና ንግድ እና ሥራ ፈጠራ (ቢአይዲ)፡፡
ግዮን፡- የሥልጠና አሰጣጥ ሂደቱ ምን ይመስላል? የሚጠይቀው ነገርስ ምንድነው?
ፍሬዘር፡- ለመሰልጠን መስፈርቱ ከ12ኛ ክፍል በላይ መኾን ነው፡፡ የሥልጠናው ጊዜ የ3 ወር ጊዜ ያለው ነው፡፡ ሥልጠናውን አጠናቀው ሲጨርሱ ሰርተፍኬት እንሰጣለን፡፡ በዚህ ዙሪያ የእኛን ተቋም ከሌላው የሚለየው 80 በመቶ ሥልጠናው ተግባር ተኮር መኾኑ ነው፡፡ ይህ ማለት ንድፈ ሐሳቡ ትንሽ ኾኖ በተግባር የሚማረው ግን ብዙውን ነው፡፡ እኛ 8 ዓመት በሥራ ላይ የቆየን ነን፡፡ በዘርፉ በቂ ወርክ ሾፕ አለን፡፡ የፈርኒቸር ማምረቻ ተቋምም አለን፡፡ ስለዚህ አንድ ዲዛይን እንዴት ወደ ተጨባጭ ሥራ መለወጥ እንደሚቻል እራሳቸው ሰልጣኞቹ በተግባር ሠርተው ያዩታል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ እኛ በርካታ የሳይት ሥራዎች ስላሉን፣ በእሱ ላይ በመሳተፍ እያንዳንዱን ሥራ እየሠሩ መሰልጠን ይችላሉ፡፡ በዚያውም የደንበኞችን ግብረ መልስ የመመልከት እድል ይኖራቸዋል፡፡
ግዮን፡- በኦንላይን የምትሰጡት የሥልጠና ዓይነትስ ምንድነው?
ፍሬዘር፡- የኦንላየን ፕላት ፎርም ሶፍትዌር ላይ መማር ለሚፈልጉ ነው፡፡ የኢንቴሪየር ዲዛይን ፍላጎት ኖሯቸው በአካል መገኘት ለማይችሉ ወገኖች የሚሰጥ ሥልጠና ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ዙሪያ እቅድ የያዝነው ቋንቋውን እንግሊዝኛ በማድረግ በመላው ዓለም ለሚገኙ ሰልጣኞች ማስተማርን ነው፡፡ በካሪኩለም ዝግጅቱ ላይም በቂ የኾነ እውቀት ያላቸው አካላት ተሳትፈውበታል፡፡ ለምሳሌ እኔ የተማርኩት እንግሊዝ ሀገር ለንደን ነው፡፡ ስለዚህ አንዱ ካሪኩለም አዘጋጅ እኔ ነኝ፡፡ ያሬድ የሚባል አርክቴክትም አለ፡፡ ማስተርሱን የተማረው ጣሊያን ሀገር ነው፡፡ በተመሳሳይ ጎንደር ዩኒቨርስቲ ከ10 ዓመት በላይ ልምድ ያላቸው መምህራኖችን አምጥተን ነው ካሪኩለሙን ያዘጋጀነው፡፡
ግዮን፡- ለሥልጠና የሚጠየቀው ክፍያና የአከፋፈል ሒደቱ ምን ይመሥላል?
ፍሬዘር፡- የእኛ የመጀመሪያው ዓላማ ሰዎች በሥልጠናው ብቁ የዘርፉ ሙያተኞች እንዲኾኑ ማስቻል ነው፡፡ በዘርፉ ሙያዊ ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩና የመፍጠር አቅማቸው እንዲጨምር ማድረግ እንጂ ገንዘብ እንዲያሳስባቸው አንሻም፡፡ ፈጠራ ያለጭንቀት የሚሠራ ነው፡፡ የክፍያ ጭንቀት ያለበት የሥልጠና ዘርፉ የሚሻውን እውቀት ማግኘት ስለሚያስችል የሥልጠናው አካል መኾን አይችልም፡፡ እኛም ይህ ችግር እንዳይኖር በማሰብ ከዳሽን ባንክ ጋር በመተባበር የክፍያ ሥርዓት አመቻችተናል፡፡
ግዮን፡- ከዳሽን ባንክ ጋር ያላችሁ ውል ምንድነው?
ፍሬዘር፡- ከዳሽን ባንክ ጋር ያለን ስምምነት ተማሪው የሚጠበቅበትን ክፍያ ከባንኩ ጋር እንዲጨርስ የሚል ነው፡፡ ለምሳሌ ሰልጣኙ በዓመት 20 ሺህ ብር የሚከፍል ከኾነ ዳሽን ባንክ ይከፍልለታል፡፡ ይህ ማለት ሰውየው በወር መክፈል የሚችለው አንድ ሺህ ብር ብቻ ቢኾን በባንኩ ያን ብር እየቆጠበ ባንኩ ግን ሙሉ 20 ሺህ ብሩን ለሥልጠና ተቋሙ ይከፍልለታል፡፡
ግዮን፡- ዳሽን ባንክ ይኽን ኃላፊነት የወሰደው ለሙያው ባለው ድጋፍ ነው ማለት ይቻላል?
ፍሬዘር፡- በትክክል! ባንኩ ከሐሳብ ጀምሮ ነው ድጋፍ እያደረገልን ያለው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ዳሽን ባንክን ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡
ግዮን፡- ትምህርት ቤቱ የት ነው የሚከፈተው?
ፍሬዘር፡- የሚከፈተው አሁን ያለንበት ሕንፃ ላይ ነው፡፡ ቦሌ ኤድናሞል ገልፍ አዚዝ ሕንጻ አኛ ፎቅ፡፡ እውቅና እንዲሰጡን ጠይቀን የተግባርና የቲዎሪ ክፍሉ ይለያይ ብለውን እየጠበቅን ነው፡፡
ግዮን፡- ፈርኒቸር ቤት እንዳላችሁ ሰምተናል፡፡ ፈርኒቸር ተማሪዎች የሚማሩበት ብቻ ነው? ወይስ ለሽያጭም ይውላል?
ፍሬዘር፡- አምርተን የምንሸጥበት ነው፡፡ ነገር ግን ተማሪዎቹ አጋጣሚውን በመጠቀም የተግባር ትምህርት ይወሰዱበታል፡፡ ተቋሙ ጁዪል ፈርኒቸር የሚባል ነው፡፡ በርካታ የቤትና የቢሮ እቃዎችን ያመርታል፡፡ እንደ ሶፋ፣ ጠረጴዛ፣ ወንበር የመሳሰሉትን ያመርታል፡፡ አካባቢውም አንበሳ ጋራዥ ቶቶት ክትፎ ቤት አካባቢ ነው፡፡ ተማሪዎቻችንን በሰርቪስ ወስደን እዚህ ምቹ ቦታ ነው የምናስተምራቸው፡፡
ግዮን፡- ደንበኞች የፈርኒቸር ምርቶቹን ከእናንተ በመግዛታቸው የሚያገኙት ጥቅም ምንድነው?
ፍሬዘር፡- ደንበኞች ከእኛ ፈርኒቸር ሲገዙ ከሚያገኟቸው ጥቅሞች አንዱ በኢንቴሪየር ዲዛይን የተሰሩ እቃዎችን ማግኘት ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በከፍተኛ ጥራት የሚመረቱ ናቸው፡፡ እኛ ፋብሪካውን የመሠረትነው በቅርቡ ቢኾንም በሥራው ላይ ስምንት ዓመት ቆይተናል፡፡ ደንበኞቻችን እቃውን ወደውት የመክፍል አቅም ባይኖራቸው እንኳን አሁንም ዳሽን ባንክ አብሮን እየሠራን በመኾኑ የሚከፍሉበት ሌላ አሠራር ዘርግተናል፡፡
ግዮን፡- በውጪው ዓለም በዘርፉ ያለው የሥራ ሒደት ምን ይመሥላል?
ፍሬዘር፡- አውሮፓ በዚህ ዘርፍ ብዙ እየሰሩበት አይደለም፡፡ ዱባይ ላይ ግን ብዙ እየተሰራበት ያለ ነው፡፡ ቻይናም በደንብ ይሠራል፡፡ የማየት እድሉን ስላገኘሁ በደንብ ታዝቤያለሁ፡፡ ዱባይ የቁሳቁስ አቅርቦታቸው ለሥራቸው እድገት ትልቅ ሚና አለው፡፡ የእኛን ሥራ በመጠኑም ቢኾኑ ውስን የሚያደርገው በቂ የቁሳቁስ አቅርቦት አለመኖር ነው፡፡ ትዕዛዞችን ስንቀበልም ግብዓቱ የሚገኘውንና የማይገኘውን ከግምት አስገብተን ነው፡፡ በውጭ ሀገራት ግን ይህ ችግር የለም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በእኛ ሀገርና በውጭ ያለው ልዩነት ሥነ ምግባር ነው፡፡ እኛ ሀገር የሥነ ምግባር ግድፈቶች አሉ፡፡ ይኼ ማለት ከደንበኛው ጀምሮ ሥራው እስከሚመለከታቸው ሁሉም አካላት ድረስ የሥነ ምግባር ችግር አለ፡፡ በአጭሩ ለመናገር በ45 ቀን ለማድረስ ተዋውለን በሠራተኛው የሥነምግባር ጉድለት ሳቢያ በተባለው ቀን አይደርስም፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ሰራተኛው በተለያዩ ምክንያቶች ይቀራሉ አልያም በሌላ ምክንያት ይጓተታል፡፡ በዚህም ምክንያት ሥራዎች ይበላሻሉ፡፡ ለምሳሌ ይህን ያደረገው ሰራተኛ የሳኒተሪ ባለሙያ ቢኾን ከፍ ያለ መስተጓጎል ይፈጥራል፡፡ ምክንያቱም ሳኒተሪ ሳይዘረጋ ሴራሚክ ስለማይሠራ፡፡
ግዮን፡- እናንተስ ለተማሪዎችችሁ ይህን ችግር በተመለከተ የምትሰጡት ኮርስ አለ?
ፍሬዘር፡- አዎ አለ፡፡ ‹‹ቢዝነስ ኢንተርፕሪነርሺፕ ፎር ኢንቴሪይር ዲዛይን›› የሚባል አንድ ኮርስ አለ፡፡ ይኼ ኮርስ የኢንቴሪይር ዲዛይን ቢዝነስ፣ ሥነምግባርና አጠቃላይ አሠራሩን እንዲያውቁት የሚረዳ ኮርስ ነው፡፡ የደንበኛ አያይዘንም እንዲያውቁ ይረዳል፡፡
ግዮን፡- እንግሊዝ ሀገር ሲማሩ ከሥራዎ ጋር በተያያዘ ያገኙት ልዩ ነገር ምንድነው?
ፍሬዘር፡- የትምህርት ቆይታ ጊዜዬ 15 ወር ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ማስተርሴን እየሠራሁ የተማርኩት ቴክኖሎጂን የተመለከቱ ጉዳዮች ናቸው፡፡ እኔ ማስተርስ የተማርኩት ኮንስትራክሽን ዴቨሎፕመንት ላይ ነው፡፡ በዚህ ዘርፍ ከተማርናቸው 6 ኮርሶች ቢም፣ ቢዩልዲንግ፣ ፎርሜሽን፣ ሞዴሊንግ እና የመሣሠሉት ላይ ነው፡፡ ይህን ነበር በጥልቀት ሲያስተምሩን የነበረው፡፡ በሕንፃ ሥራ ቢም የሚባለው በሳይንስ እንደሰው የሰውነት ክፍል ነው ማለት ይቻላል፡፡ የሕንጻው የጀርባ አጥነት ቢም ነው፡፡ ወደፊት እኛ የምንሠራውም በዚህ ዓይነት መንገድ ነው፡፡
ግዮን፡- በሀገራችን ያለውን የኮንስትራክሽን ሂደት እንዴት ይገልጹታል?
ፍሬዘር፡- በዘርፉ ብዙ ዓይነት ችግሮች አሉ፡፡ በጣም የሚያስቸግረው የዕቃ ግዢ ገበያ አለመረጋጋት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር በተደጋጋሚ ከስረን እናውቃለን፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ተዋውለን ሐምሌ ላይ ዶላር ጨመረ፡፡ ያ ሥራ እኛን በጣም የጎዳን ሥራ ነው፡፡ በገንዘብ ብዙ ያጣንበት ነው፡፡ ስለዚህ የገበያው አለመረጋጋት ዘርፉ ላይ ተግዳሮት ኾኗል፡፡ የሠራተኛ ሥነምግባር ደግሞ ሥራውን በማጓተት በኩል ሌላው የተለየ እንቅፋት ነው፡፡ የአከፋፈል ሁኔታውም በዘርፉ ያለ ሌላው ችግር ነው፡፡
ግዮን፡- የእናንተ ኢንቴርየር ዲዛይን ከሌላው መሰል ተቋም የሚለየው በምንድነው?
ፍሬዘር፡- እኛ የምንሠራው የፈጠራ ሥራ ነው፡፡ ይኼ ከሌላው ይለየናል፡፡ በተጨማሪም ሥራን በጥራትና በሰዓቱ ሠርተን እናስረክባለን፡፡
ግዮን፡- የተቋማችሁ የወደፊት ሕልም ምን ደረጃ መድረስ ነው?
ፍሬዘር፡- ቢዝነስ ትልቅ ጥቅም የሚኖረው ዓለም አቀፋዊ ሲኾን ነው፡፡ በሀገር አቀፍ ደረጃ የዘርፉ መሥራቾች አካባቢ የምንመደብ ነን፡፡ ዘርፉን በመመሥረት ከመጀመሪያዎቹ ተርታ ነን፡፡ ሕዝቡ ለዘርፉ እውቀት በሌለው ሰዓት ነው እኛ የጀመርነው፡፡ ስለዚህ የእኛ ተቋም ሕልም ዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት ውስጥ መግባት ነው፡፡ አሁን ላይ ከሀገር ውጭ በዱባይ ቅርንጫፍ ከፍተናል፡፡ ነገር ግን ከሀገር ውጭ የከፈትነው እዚህ ሀገር ከበቂ በላይ አገልግለን አይደለም፡፡ እዚህ ያለውንም እየሠራን ዱባይም ስንሠራ ለቴክኖሎጂ ሽግግር ይጠቅመናል፡፡ እዚያ የምንሠራ ብንኾን ተወዳዳሪነታችንን ከመጨመሩም በላይ የግብዓት አቅርቦት ችግር አይገጥመንም፡፡ ሶፍትዌሩ ተመሳሳይ ስለኾነ የሀገራቱ መለያየት ለውጥ የለውም፡፡ እኛ የምንጠቀመው ሶፍትዌር ዓለሙ ሁሉ የሚጠቀመውን ነው፡፡ ይህን ሶፍትዌር ወደ ሀገራችን ከማምጣት ባሻገር በሌላ ሀገር ላይም እኛው መሥራታችን ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡
ግዮን፡- ከመንግሥት እንዲስተካከሉ የምትፈልጓቸው ፖሊሲዎች ወይም እገዛዎች ካሉ ቢጠቅሷቸው?
ፍሬዘር፡- እንደሀገር ይኼ ሥራ ቀላልና የቢዝነስ ሥራ ብቻ አይደለም፡፡ የትውልዱ ሥራ ነው፡፡ የእኛ የወደፊት እቅድ ተቋሙን ዩኒቨርሲቲ ማድረግ ነው፡፡ ይህን እቅድ ለማሳካት የመንግሥት እገዛ ያስፈልገናል፡፡ ከዚህም እገዛ አንዱ ቦታ ማግኘት ነው፡፡ እኛ ሕንፃ መሥራት እንችላለን፡፡ የሕንፃ መሥሪያ ገንዘቡን ደግሞ ከባንኮች ጋር የምንሠራበትን ነገር እናመቻቻለን፡፡ ነገር ግን ለዚህ እቅዳችን የሚመጥን ቦታ ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም በአምስት ዓመት ውስጥ ዩኒቨርሲቲ የማድረግ እቅድ ካለን ተከራይተን መሥራት አንችልም፡፡ ስለዚህ መንግሥት ከወዲሁ ዓላማችንን ተረድቶ እንዲያግዘን እንሻለን፡፡ ወደፊት ፕሮፖዛል አዘጋጅተን መጠየቅ ያለብንን የመንግሥት አካል እንጠይቃለን፡፡
በአጠቃላይ ሥራችንን ለማዘመን አስፈላጊውን ጥረት እያደረግን እንገኛለን፡፡ ነጮች ከፈጠሯቸው ተቋማት ጋር ተወዳዳሪ የሚኾን ተቋም መገንባት እንችላለን፡፡ ለምሳሌ እኔ ይሄን ትምህርት እንግሊዝ ሀገር ስማር ሚሊዮን ብሮችን አውጥቼ ስለተማርኩ ሥጋት ነበረኝ፡፡ በሥራ ሂደቴ ውስጥ ያወጣሁትን ብር ባልተካስ ብዬ አስብ ነበር፡፡ ነገር ግን ስማር እንደፈራሁት አይደለም፡፡ በትምህርቴም ከነጮቹ የተሻለ ውጤት አምጥቻለሁ፡፡ በሥራው ስሰማራም ውጤታማ ኾኛለሁ፡፡ ይኼ ሥራ እውቀቱ በብዙ መንገድ ለሁሉም ሰው የሚጠቅም ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ በገንዘብ ደረጃም ትልቅ ቢዝነስ የሚንቀሳቀስበት ዘርፍ ነው፡፡ በተጨማሪም የዘርፉ ዕውቀት ያለው ሁሉ ተቀጣሪ ከመኾን፣ የቢዝነሱ ፈጣሪ የመኾን እድሉ ተቋዳሽ መኾን ይኖርበታል፡፡ ኢንቴሪየር ዲዛይን ተማሪ ማለት አንድ ግለሰብ እንደኛ ቢሮ ከፍቶ መሥራት ላይጠበቅበት ይችላል፡፡ እውቀቱ ሰፊ ስለኾነ ፈርኒቸር ሊያስመጣ ይችላል፤ የኤሌክትሪክ እቃዎች መብራትና ሶኬቶችንም ሊያስመጣ ይችላል፡፡ ሌላም ሌላም መሥራት ይችላል፡፡ ነገር ግን መጀመሪያ ዕውቀቱን ሊይዝ ይገበዋል፡፡
ግዮን፡- በመጨረሻ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ እድሉን ልስጥዎ?
ግዮን መጽሔት ቅጽ 7 ቁጥር 224 መጋቢት 20 2017 ዓ.ም
