
ዓይናለም ደበበ
ዛሬ ዛሬ በሀገራችን በስፋት እንደምናያቸው አስመሳይ ‘ምሁራን’ ፣ ምሁርነት ያልተገባ የግል ጥቅም ማሳደጃና በሀገር ክህደት ላይ የሚያጠነጥን የሴራ ፖለቲካ ማሳለጫ አደገኛ መሳሪያ ከመሆኑ በፊት ኢትዮጵያ በደረጀ እውቀታቸው እንደ ኮከብ የሚያበሩ አያሌ ሊቃውንትን አፍርታለች። እነዚህ ሊቃውንት ኢትዮጵያ በዓለም ሕዝብ ዘንድ እንድትከበርና እንድትወደስ ያደረጓትን ሀገር ወዳድ ጀግኖችን በማፍራትም ከፍተኛ ግልጋሎትን ሰጥተዋል። እንደዛሬው ፈጣንና ምቹ የመጓጓዣ ዘዴ በሌለበት እውቀትን ፍለጋ ‘ልወዝወዘው በግሬ’ እያሉ ካገር አገር ጋራ ሸንተረሩን፣ ወንዝና ዥረቱን እያቋረጡ፤ ለነፍሳቸው ማቆያ የሚሆን ጥሬ እየቆረጠሙ በብዙ ፈተናና ውጣ ውረድ ውስጥ ሆነው የቀሰሙትን እውቀት ያለ አንዳች ስስት ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ የሚቻላቸውን ጥረት ሁሉ ሲያደርጉ ኖረዋል። ከእነዚህ የሀገራችን ሊቃውንት መካከል “ይማሯል እንደ አካልዬ፣ ይዋጓል እንደ ገብርዬ” የተባለላቸውን የቀለም ቀንድ የሆኑትን ሊቀ ሊቃውንት አካለወልድ ሠርፀወልድን በመጠኑ እንዲህ ለማስታወስ ወደድኩኝ።
ሊቀ ሊቃውንት አካለወልድ የመንዝ ተወላጅ ከሆኑት አባታቸው ከመምህር ሠርፀወልድ እና የመርሃቤቴ ተወላጅ ከሆኑት እናታቸው ከወይዘሮ ወለተኪሮስ (በኋላ እማሆይ ተብለው ይጠራሉ።) በ1824 ዓ.ም ሰሜን ሸዋ መንዝ ውስጥ ውቢት ዓምባ አቦ ከተባለ ስፍራ ተወለዱ። አድገው ለትምህርት እንደደረሱም በዚያው በወላጆቻቸው ቤት ሆነው ትምህርታቸውን በመከታተል በአሥራ ሁለት ዓመት እድሜያቸው ላይ ንባብና ዳዊትን አጠናቀቁ። ከዚያም ወደ ዋድላና ደላንታ አቅንተው ዳጊት ማርያም በምትባል ቤተ ክርስቲያን የቅኔ መምህር ከሆኑት ከአባ ጫልቲ ዘንዳ ቅኔ ተማሩ። አካለወልድ የቅኔ ትምህርታቸውን ሰፋና ጠለቅ ባለ ሁኔታ ለመቅሰም በማሰባቸው ወደ መቄት፣ ላስታና ጎንደር በማቅናትም ትምህርታቸውን አጠናከሩ። ከዚያም ከበኣታ ለማርያም ደብር ሊቃውንት ዘንድ የደቂቀ ነብያትን ትርጓሜ በግሩም ሁኔታ አጠኑ። ትምህርት ይሰጥበታል፣ እውቀት ይገኝበታል የተባለበት ቦታ ሁሉ እየተዟዟሩ እውቀትን ለመቅሰም እጅግ የሚጥሩት አካለወልድ፣ እንደገናም ወደ ጎንደር አጣጣሚ ሚካኤልና እልፍኝ ጊዮርጊስ አቅንተው የመጻሕፍትን ትርጓሜ መማር ያዙ። እንዲህ እንዲህ እያሉም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በከፍተኛ ፍላጎትና ጉጉት እንደተሞሉ ሊቃውንት ይገኙበታል እተባለበት ደብር ሁሉ እያሰሱ የቀለም ቀንድ ሆነው ትምህርታቸውን ተከታተሉ።
አፄ ቴዎድሮስ በአካለወልድ የቀለም አያያዝ በእጅጉ ይደነቁ ነበር። በርሳቸው ዘመነ መንግሥት በነበሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና በእስልምና እምነት መሪዎች መካከል ይታይ የነበረውን ቅጥ ያጣ ፉክክር የታዘቡት ንጉሠ ነገሥቱ በሁለቱ መካከል ያለውን ክርክር ለመቋጨት በማሰብ በሁለቱም የእምነት ተከታዮች ዘንድ በሚከበረው በዘመን መለወጫ ዕለት የሁለቱንም ሀይማኖት መሪዎች ቦሩ ሜዳ ላይ በማሰባሰብ አንድ ሰንጋ አዘጋጅተው በመስጠት ተካፍለው እንዲበሉ አዘዟቸው። ሆኖም ግን የአንደኛው የእምነት አባት የባረከውን የሌላኛው የእምነት ተከታይ ላለመመገብ ሰንጋውን በመባረኩ ላይ ክርክር ገጠሙ። ታድያ በዚህ ግዜ ሊቁ አካለወልድ ከክርክሩ መሀል ገብተው ሰንጋውን የእስልምና እምነት መሪዎች እንዲባርኩት ተናገሩ። በዚህ ንግግራቸውም ካህናቱ ተጠቃን! በማለት ተቃውሟቸውን አካለወልድ ላይ በማጉረምረም ገለፁ። ሰንጋው በእስልምና እምነት አባቶች ታርዶም ንጉሡ ተካፍለው እንዲመገቡ ባዘዙት መሠረት ግማሹ ለካህናቱ ተሰጠ። ሊቁ አካለወልድም “በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሃዱ አምላክ በእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን!” ብለው ከታረደው ሰንጋ ስጋ መብላት ያዙ። ከዚያም “ክርስቲያን ያረደውን ሙስሊም አይብላ፣ ሙስሊም ያረደውን ክርስቲያኑ አይቅመስ የሚል ትእዛዝ በመጽሐፍ ቅዱስ ወይም በቅዱስ ቁርዓን ተፅፎ እንደሆነ ንገሩኝ።” ብለው የሁለቱንም ሃይማኖት መሪዎች ቢጠይቁ፣ አባቶቹ እርስ በእርስ ተፋጠው ከመተያየት ውጪ ለተጠየቁት ጥያቄ መልስ መስጠት ባለመቻላቸው ዐፄ ቴዎድሮስ በአካለወልድ የአስተሳሰብ አድማስ እጅግ ተደንቀውና ተደስተው ይህን አሉ። “ስሚኝ አንቺ ቆማጣ ቆመጥማጣ፣ በየፊናሽ ተምሬያለሁ እያልሽ በወገኔ ላይ ትደነፊያለሽ፣ እውቀት ማለት ግን እንደ አካልዬ ያለ ነው። ይማሯል እንደ አካልዬ፣ ይዋጓል እንደ ገብርዬ” ሲሉም እጅግ ከሚወዱት የጦር አዛዣቸው ከፊታውራሪ ገብርዬ ጋራ በማነፃፀር አካለወልድን አሞካሿቸው።
ግብፃዊው ጳጳስ አቡነ ሰላማ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ሆነው፣ ለኢትዮጵያ አንድነት ቀን ከሌት የሚተጉትን የአፄ ቴዎድሮስን ራዕይ ለማጨናገፍ በሚያሴሩበት ግዜ፣ ሊቀ ሊቃውንት መምህር አካለወልድ ንጉሡ በሊቀ ጳጳሱ ተንኮል ተበሳጭተው በብስጭት ሕዝባቸውን እንዳይጎዱ ጥበብ በተመላበት ሁኔታ ለንጉሡ ምክር ይለግሷቸው ነበር። እንዲሁም በዐፄ ዮሐንስና በዐፄ ምኒልክ መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ቅራኔ ለማርገብ ዐፄ ምኒልክን ተከትለው ቦሩ ሜዳ ካቀኑት ታላላቅ ሊቃውንት መካከል አካለወልድ አንዱና ዋንኛው ነበሩ።
ለሊቀ ሊቃውንት አካለወልድ ስራ እጅጉን አክብሮት የነበራቸው ነገሥታቱ አንዳንዴም ግዛት እየጨመሩላቸው ድጋፋቸውን አሳይተዋቸዋል። እርሳቸው ግን በግል የቁሳዊ ጥቅም ከመምበሽበሽ፣ በሥጋዊ ድሎትና ምቾት ከመምነሽነሽ ለመንፈሳቸው እርካታ ወጥተው ወርደው ሀገራቸውን ማገልገልን የሚመርጡ ሰው ነበሩ። ተማሪዎቻቸውንና ሕዝቡን በሃይማኖትም ሆነ በሌላ ጉዳይ አንዱን ካንዱ ሳይለዩ ልብስ ለቸገረው ልብስ፣ እህል ለቸገረው እህል እየሰጡ ማገዝ ይቀናቸው ነበር። አካለወልድ ለተቸገረ ደራሽ፣ ለተራበ አጉራሽ ደግ ሰው በመኾናቸው የክርስትናም ሆነ የእስልምና እምነት ተከታይ የሆነው ምእመን እጅግ ይወዳቸው ነበር። እንዲያውም አንድ ወቅት ላይ በኢየሩሳሌም ሲያደርጉ የነበረውን ጉብኝት አጠናቀው አገራቸው ተመልሰው ደሴ ከተማ በገቡ ግዜ ሕዝቡ በሙሉ ተሰባስቦ “በክፉ ቀን ከጎተራ እህል እያወጡ እስላም ክርስቲያን ሳይሉ ለሁሉም ያከፋፈሉት ሰው እንኳን ደህና መጡ” እያሉ ተቀብለዋቸዋል። የእስልምና ሀይማኖት መሪዎች “ይህ ሰው የአላህ ሰው ነው። ማተብ ይኑረው አይኑረው ብቻ እሱን የሚጠላ ሐራም ነው” በማለት ለርሳቸው ያላቸውን ፍቅር ገልፀዋል።
ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ አልጋ ወራሽ በነበሩበት ግዜ የመጻሕፍተ መነኮሳት ንባብ ትርጓሜ በመጽሐፍ መልክ እንዲዘጋጅ አስበው ሊቀ ሊቃውንት አካለወልድን ቢጠይቁ አካለወልድም ትእዛዙን ተቀብለው በዚሁ የረቂቅ ሥራ ላይ እንዳሉ ያደረባቸው ሕመም ተባብሶ በተወለዱ በሰማንያ ስምንት ዓመታቸው ሕዳር 9 ቀን 1912 ዓ.ም አረፉ። ሲያገለግሉ በኖሩበት ቦሩ ሜዳ ሥላሴ ቤተ ክርስቲያንም ስርዓተ ቀብራቸው ተፈፀመ።
“አፈር መልሱ እንጂ ድንጋይ ለምናችሁ፣
የቀለም ቀንድ ነው ትሰብሩታላችሁ።
መምህር አካለወልድ ቄሱ የት ደረሱ፣
ጎንደር ወረዱ ወይ ሥልጣን ሊመልሱ።
እስቲ ሰፌድ ስጡኝ አፈሩን ላንፍሰው፣
ያንን ሁሉ ቀለም ወዴት አፈሰሰው” በማለትም ተገጠመላቸው።
ሊቀ ሊቃውንት መምህር አካለወልድ በሕይወት ዘመናቸው ያካበቱትን እውቀት ተጠቅመው የፃፉትን እንዲሁም ከተለያየ ቦታ ያሰባሰቡትን መዛግብት በቦሩ ሜዳ ሥላሴ ደብር ለማቆየት ችለዋል። ሀገራቸውን በመምህርነት፣ በቤተ ክህነትና በሕዝብ አስተዳደር እንዲሁም በሀገር ሽምግልናና በአማካሪነት በትጋት አገልግለዋል። ከአፄ ቴዎድሮስ እስከ ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ አያሌ ሊቃውንትንና ነገሥታትን በማስተማር፤ በሀገር ፍቅር፣ በሥነምግባርና በግብረገብነት እውቀት የበቁ እልፍ አዕላፍ ዜጎችን በማፍራት ኢትዮጵያ በልጆቿ የታፈረችና የተከበረች ሀገር ሆና በነፃነት እንድትኖር ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
በቸር ያቆየን!