መንግሥት ለሹመኞቹ መሳሪያ ከማስታጠቁ በፊት የሥነ-ምግባር መርሕን ያስታጥቅ!!

Date:

ዛሬ ማለዳ ላይ ወደ ሥራ ለመግባት እኔና የሥራ ባልደረቦቼ በአንድ ሚኒ ባስ ሰርቪስ ውስጥ በመሆን እየተጓዝን ነበር፤ የምንሄድበት የውስጥ ለውስጥ መንገድ በኮተቤ ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤ/ክ አድርጎ ወደ ጫካው ቤተ-መንግሥት/ወደአዲሱ መንገድ የሚያወጣን ነው፡፡ ታዲያ ይህ መንገድ እለቱ የኪዳነ ምሕረት ወርኻዊ በዓል በመሆኑ ተዘጋግቶ ነበር፡፡

በተዘጋጋው በጠባቡ የውስጥ ለውስጥ መንገድ ወደ ዋናው መንገድ ለመውጣት በርካታ መኪናዎች በሰልፍ ተደርድረዋል፤ እናም እኛ ከነበርንበት መኪና ፊት ለፊት የነበረው 4 ቁጥር መለያ የያዘው የመንግሥት መኪና ወደኋላችን ፈቀቅ እንደማለት ሲል ሹፌራችን ከኋላ መኪና አለ በሚል ጥሩንባ ያደርግለታል፤ በዚህ ቅፅበትም፤ ‹‹የሹም ዶሮ ነኝ እሽ አትበሉኝ!!›› ያለ የሚመስለው ከፊታችን በነበረው መኪና ውስጥ ያለው ሰው በመስኮት በኩል ሽጉጥን አውጥቶ እያወዛወዘ ለማስፈራራት ሞከረ፡፡

መኪና ውስጥ ያለነው እኔና የሥራ ባልደረቦቼ በሰውዬው ሁኔታ ከማስገርምም አልፎ አበሳጨን፤ ይህን ሥርዓት አልበኛ ሰውማ ልናስተምረው ይገባናል… መንግሥት ያስታጠቀው መሳሪያ ዓላማው ለምን እንደሆነ ያልገባውን ይህን ዋልጌ/መደዴ እንከታተለው በማለት ከሹፌራችን ጋር ተነጋገርን፡፡

ሹፌራችን የቀድሞ የኢትዮጵያ መከላከያ አባል የሆነ ወታደር በመሆኑ የሰውዬው ነገር በጣሙን አበሳጭቶታል፡፡ ወታደራዊ ዲስፕሊንና መርሕ ምን መሆኑን አሳምሮ የሚውቀው ሹፌራችን እንዲህ ዓይነቱን ሥርዓት አልበኝነት ፈጽሞ ሊታገሰው አልፈቀደምና ፍጥነቱን ጨምሮ መኪናውን መከታተል ጀመረ፡፡ በሰርቪስ ውስጥ ከነበርነው አንዳንዶቻችን የወታደር ልጅ ነንና ራስንና ወገንን ለመጠበቅ በሕዝባዊ ኃላፊነት የተሰጠ የጦር መሳሪያ ያለ አንዳንች ምክንያት በየሜዳው እንደማይመዘዝ አሳምረን እናውቃለን፡፡

አውላላ ሜዳ ላይ ገና በማለዳው ሽጉጡን በመምዘዝ ሊያስፈራራን የዳዳው ሰውዬ ጋር ፊትና ኋላ ሆነን በዚህ አኳኃን የተዘጋጋውን ጠባቡን መንገድ አልፈን ወደ ዋናው መንገድ እንደወጣን መኪናውን እየተከታተልን አብረነው መጓዝ ጀመርን፡፡

የሰውዬውን መኪና ታርጋውን በእጅ ስልካችን ፎቶ ካነሳነው በኋላ እግር በእግር መከታተተል ጀመርን። ይህን ያደረግነው በመንገዳችን ላይ የትራፊክ ፖሊስ አግኝተን ጉዳዩን ለማሳወቅ ነበር፡፡ እየተከታታልነው እንደሆንን የገባው ሰውዬ ፍጥነቱን ጨምሮ መንዳት ጀመረ፤ ሹፌራችንም ትራፊክ ፖሊስ ወዳለበት ስንደርስ መንገድ ዘግቶበት እንዲቆም ለማድረግ ፍጥነቱን ጨምሮ መንዳት ጀመረ፡፡

ልክ ወደ እንግሊዝ ኤምባሲ አካባቢ ስንደርስ ባለሽጉጡ አሸከርካሪ ወደ ትራፊክ ፖሊሱ ጠጋ ብሎ ሳይወርድ በመስኮት በኩል ማነጋገር ጀመረ፤ በዚሁ ፍጥነት ከኋላው የደረሰው ሹፌራችን ከሰውዬው መኪናው ከኋላው አቆመ፡፡ እናም ጉዳዩን ለማስረዳት ወደ ትራፊክ ፖሊሱ ስንጠጋ ሰውዬው በብርሃን ፍጥነት ተፈተለከ፡፡ እኛም ለትራፊክ ፖሊሱ ገና ስለሁኔታው ልናስረዳው ንግግር ከመጀመራችን፤ ‹‹ተዉ! ተዉ! የመንግሥት አካል ነው!!› ዝም ብላችሁ ሂዱ በማለት ሊያግባባን ሞከረ፡፡ 

 ‹‹የአሁኑ ይባስ!›› እንዲሉ ሕግ ለማስከበር ሕዝባዊ ኃላፊነትንና ግዴታን ተቀብሎ ፊት ለፊታችን የቆመው ትራፊክ ፖሊስ ምላሹ ከማስገረምም አልፎ አበሳጨን፤ 

የሆነስ ሆነና ለመሆኑ የመንግሥት ሹም፤ ‹‹ዘንግ በተወረወረ፤ ወፍ በበረረ ቁጥር›› እንዲሉ በትንሹም በትልቁም አውላላ ሜዳ ላይ መሳሪያውን አውጥቶ እንዲያስፈራራ የፈቀደለት አካል ይኖራል ብዬ አላስብም፤ ይህ ፈጽሞ ከኢትዮጵያዊነት ጨዋነትና ሥነ-ምግባር ያፈነገጠ ነገር ነው፡፡

አገርንና ወገንን እንዲያገለገሉበት በተሰጣቸው ሥልጣን፣ ሕዝባዊ ኃላፊነት በየሜዳው መሳሪያ እየመዘዙ የገዛ ወገናቸውን የሚያስፈራሩ፤ ለራሳቸውም ሆነ ለሌላው ሰው ክብር የሌላቸውና ኃላፊነት የጎደላቸው ሹማምንት “ሥርዓት ያዙ!!” ሊባሉ ይገባቸዋል፡፡

መንግሥትም ሹመኞቹን መሳሪያ ከማስታጠቁ በፊት- ባለ ሥልጣናቱ ለሕዝባዊ ሥነ-ምግባርና መርሕ የተገዙ፤ የአገር ፍቅር የወገን ክብር ምን እንደሆነ በቅጡ ይረዱ ዘንድ በሚገባ ሊያስተምራቸው፤ ሊያሰለጥናቸው ይገባል!!

ይህ ትዝብትና ወቀሳ- የተሰጣቸው ሥልጣን አገራቸውንና ወገናቸውን የሚያገልግሉበት እንደሆነ አምነው በፍቅር፣ በትሕትና አገራቸውንና ወገናቸውን የሚያገልግሉ፤ ለአገራቸውና ለሕዝባቸው ክብር ያላቸውን፤ ኢትዮጵያዊ ጨዋነትንና ሥነ-ምግባርን የተላበሱ ባለሥልጣናትን/ሹማምንትን ፈጽሞ የሚመለከት አይደለም፡፡

ሰላም ለኢትዮጵያ!!

በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ፤ አደረሰን

ሰማያት ተከፈቱ ፣ ምስጢርም ተገለጠ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘመዷ ቅድስት...

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...