Home ኪነ ጥበብ “ማንኛውም ሰው ለተፈጠረበት ዓላማ ሊኖር ይገባል”አርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ

“ማንኛውም ሰው ለተፈጠረበት ዓላማ ሊኖር ይገባል”አርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ

“ማንኛውም ሰው ለተፈጠረበት ዓላማ ሊኖር ይገባል”አርቲስት ታሪኩ ብርሃኑ

ውድ አንባቢያን፣ በቅርቡ ወጣቱን የትወና እና የጥበብ ሰው ታሪኩ ብርሃኑ (ባባ)ን በሞት አጥተነዋል፡፡ ሁለገቡ አርቲስት ታሪኩ (ባባ) ባለፉት ዐሥራ አምስት ዓመታት በድንቅ የትወና ብቃቱ የሚሊዮኖችን አድናቆት ያገኘ የጥበብ ባለሙያ ቢኾንም፣ ስለ ሥራውና ስለራሱ በብዙኃን መገናኛዎች ላይ ወጥቶ የመናገር እምብዛም ፍላጎት የሌለው ሰው ነበር፡፡ ኾኖም በዝግጅት ክፍላችን ተሰናድታ ለንባብ ትበቃ በነበረችው የቀድሞዋ ዕንቁ መጽሔት ቁጥር 49፣ ነሐሴ 2003 ዓ.ም “ከስክሪን መስኮት” ከተሰኘው ዓምዳችን ጋር አድርጎት የነበረውን አጭር ቆይታ ለማስታወሻ ይኾን ዘንድ እንደሚከተለው ልናስነብባችሁ ወደድን፡፡ ነፍስ ይማር!

ወደ ትወናው ሙያ እንዴት ልትገባ ቻልክ?

ታሪኩ፡- ወደዚህ ሙያ የገባሁት በአጋጣሚ አይደለም፡፡ ማንኛውም ሰው ራሱን ፈልጎ እስኪያገኝ፣ ተሰጥኦውን እስኪያውቅ ድረስ የተለያዩ ነገሮችን ይሞክራል፡፡ አንድ ቀን ተሠጥኦውን ያውቃል፡፡ በዚያ መንገድ በተገቢው አካሄድ ከተጓዘ ወደሚፈልገው ስፍራ ይደርሳል፡፡ በዚህ መልኩ ነው እኔም ወደ ትወናው ዓለም የገባሁት፡፡

የፊልም ትወናን በትምህርት ነው ያገኘኸው ወይስ በተሰጥኦ?

ታሪኩ፡- የመጀመሪያው ነገር የራስን ተሰጥኦ ማግኘት ነው፡፡ ያንን ካወቅክ በኋላ ትጥራለህ፡፡ በአካባቢዬ ከሚገኙ ጓደኞቼ ጋር በድራማ ጉዳይ እንንቀሳቀስ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ግን የብዙዎች አባት የሆነው “ፋዘር” ጋር ተማርኩ፡፡ እዚያው ያገኘኋቸው የ“ስላንቺ” እና የ“ላውንደሪ ቦይ” ደራሲና ዳይሬክተሮች ፀጋዬ ዮሐንስ እና ልዑል ሠለሞን ያላቸውን እውቀት በሙሉ ያለ ስስት አካፍለውን የ“ላውንደሪ ቦይ” መሪ ተዋናይ አድርገው መረጡኝ፡፡ በዚህም ያለኝን ነገር እያዳበርኩ ከተፈጥሮ ጋር ተደምሮ ተዋናይ ልሆን ችያለሁ፡፡

በአሁኑ ወቅትስ ልትሰራው የተዘጋጀህበት ፊልም አለ?

ታሪኩ፡- በቅርቡ የሚወጣ መደበኛ ርዕስ ያልተሠጠው አንድ ሥራ አለ፤ በተጨማሪም በአማን አስፋው እና በመስፍን አያሌው ተደርሶ በተዘጋጀው “ከጀርባ” የተባለ ፊልም ላይም እየሠራሁ ነው፡፡

“300 ሺህፊልም ምን አይነት ገጸባህሪይ ይዘህ ነበር የተጫወትከው?

ታሪኩ፡- ሠዎች እያነበበ የሚፈላሠፍ ሰው እያዩ ያድጉና ሕይወታቸው እንደዚያ እንዲሆን ይፈልጋሉ፤ እነዚህ ሰዎች ግን የራሳቸው የሆነ ሌላ ስብዕና ያላቸው ናቸው፡፡ መጽሐፉን ያነቡታል፤ የራሳቸውን ሕይወት እየኖሩ ተመስጠው ያዩት ሠው ተግባር ግን ጫና ያሳድርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም የሚያነቡት ለመፈላሰፍ ብለው ስለሆነ ተፅዕኖ ካሳደረባቸው ሰው ኑሮ ጋር የራሳቸው ሕይወት ይቀላቀልባቸዋል፡፡ በ“300 ሺህ” ላይ ያለው ገፀ-ባህሪይ ያዕቆብም እንደዚህ አይነት ሰዎችን ወክሎ ፊልሙ ውስጥ የተወነ ወጣት ነው፡፡

በፊልሙ ውስጥ ራስህን እንዴት አገኘኸው?

ታሪኩ፡- እንደ መጀመሪያ ፊልም “ላውንደሪ ቦይ” ላይ ያለው ልጅ በጣም ሞቃት ስሜት ያለው ነው፡፡ “300 ሺህ” ላይ ያለው ደግሞ የእሱ ተቃራኒ ነው፤ ትንሽ ያስቸግር ነበር፤ ግን በተወሰነ መልኩ ጥሩ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

ፊልሙ ላይ በዋና ገጸባህሪይነት የሠራችሁት ጓደኛማቾች ጥሩ መተሳሰብ ታሳያላችሁ፤ በገሃዱ ዓለም ከጓደኞችህ ጋር ያለህ ግንኙነት ምን ይመስላል?

ታሪኩ፡- በደንብ ከተግባባህ እና ከተከባበርክ በገሃዱ ዓለምም ጥሩ ጓደኝነት መሥርቶ መኖር ይቻላል፡፡ እኔ በአሁኑ ጊዜ የምኖረው ከጓደኞቼ ጋር ነው፡፡ ተቀራራቢ እድሜ እና ተመሳሳይ ሙያ ላይ ያለን ስለሆንን ተሳስበን እና ተጋግዘን በፍቅር ነው የምንኖረው፡፡

ከተመልካች እየደረሠህ ያለው አስተያየት ምን ይመስላል?

ታሪኩ፡- ጥሩ አስተያየት እየደረሰኝ ነው፡፡

300 ሺህ ፊልም ቀረፃ ወቅት ከዳይሬክተሮች ጋር የነበረህ ግንኙነት ምን ይመስል ነበር?

ታሪኩ፡- ዳይሬክተሩ ሙሴ በጣም አሪፍ ሰው ነው፤ ሃሳብ እየተቀበለ በመነጋገር የሚያምን ዳይሬክተር ነው፡፡ አርት ዳይሬክተሩ ተመስገንም ጥሩ ሰው ስለነበረ በእኔ በኩል ከሁሉም ዳይሬክተሮች ጋር በጥሩ መግባባት ነበር የሠራነው፡፡

የፊልሙ ቀረፃ ተጠናቆ ለዕይታ ከበቃ በኋላ ይሄንን ብጨምርበት ወይም ይህንን ብቀንሰው ብለህ ያሰብከው አለ?

ታሪኩ፡- አንድ ሥራ ሠርተህ እስክትጨርስ ድረስ ባሉት ጊዜያት ውስጥ በቆይታም ሆነ በተለያዩ ነገሮች ከመጀመሪያው የተሻለ ነገር ይኖርሃል፡፡ ስለዚህ የሚቆጭ ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ በወቅቱ የነበረኝ አቅም ጥሩ ስለነበር ን ብዙ የተቆጨሁበት ነገር የለም፡፡

ለዚህ ፊልም በመሪ ተዋናይነት ያጨህ ማነው? ስክሪፕቱ ሲሰጥህ ያቀረብከው ሃሳብስ ምንድነው?

ታሪኩ፡- መሪ ተዋናይ እንድሆን የመረጡኝ ዳይሬክተሩ እና አርት ዳይሬክተሩ ናቸው፡፡ ስክሪፕቱ ሲሰጠኝም መግባባታችን በውይይት ላይ የተመሠረተ ስለነበር ብዙ ተነጋግረናል፡፡ ስክሪፕቱን በመነጋገር የሠራነው ለክሬዲት ሳይሆን ጥሩ እንዲሆን ነበር፤ በመጨረሻም ስክሪን ፕሌይ ብለው ስሜን አካተውታል፡፡

በሃገራችን ብዛት ያላቸው ፊልሞች ወደ ተመልካች እየቀረቡ ነው፤ ፊልሞች እንደመብዛታቸው እድገትና ለውጥ አሳይቷል?

ታሪኩ፡- የፊልም መብዛት ተቃዋሚ አይደለሁም፤ በተቻለ አቅም ግን ተመልካቹን የሚያሸሽ ባይሆን ደስ ይለኛል፡፡ መብዛቱ ግን ሰዉ የተመቸውን እንዲመርጥ ስለሚያስችለው በዚህ ረገድ ለውጥ መጥቷል ማለት ይቻላል፡፡

በምን ዓይነት ገፀ ባህርይ መተወን ይመችሃል?

ታሪኩ፡- በጣም የሚፈትኑ፣ ጊዜ የሚያስፈልጋቸው፣ ከለመድናቸው ሰዎች የተለየ ገፀ ባህርይ ያላቸውን ብሰራ ደስ ይለኛል፡፡

ምን አይነት ፊልም ማየት ያስደስትሃል?

ታሪኩ፡- የድራማ ባህርይ ያላቸው ፊልሞች፡፡

ከፊልም ትወና ሌላ ሥራህ ምንድነው?

ታሪኩ፡- ከፊልም ሙያ ውጪ ሌላ ሥራ የለኝም፡፡ ከትወና በተጨማሪ ፊልም እየፃፍኩ ነው፤ ፊልም ለማዘጋጀትም አስባለሁ፡፡

ልትታገለው ቃል የገባህበት ትግልህንም በልብህ ይዘህ እየተንቀሳቀስክበት ያለው ዕቅድህ ምንድነው?

ታሪኩ፡- “ቃላችን ለትግላችን፤ ትግላችንም ለልባችን” 300 ሺህ ፊልም ላይ ያለነው ጓደኛማቾች እንመራበት የነበረው መርህ ነው፡፡ ይህን መርህ ሁሉም ሰው ቢኖርበት ጥሩ ይመስለኛል፡፡ “ሙያ በልብ ነው” ዓይነት መልዕክት ነው ያለው፡፡ የሰው ፍላጎት መጨረሻና ገደብ የለውምና እኔም በዚህ መርህ መሠረት እየኖርኩ ነው ያለሁት፡፡

በፊልሙ ቀረፃ ወቅት ያጋጠሙህ አዝናኝ ወይም አሳዛኝ ክስተቶች ነበሩ?

ታሪኩ፡- የስቲም ባዝ ቀረፃ እየሠራን ራቁታችንን በፎጣ ሆነን ለማወላለቅ ስንሞክር አልተሳካልንም፡፡ በኋላ ዮሐንስ አንሸራቶት ወድቆ ክፉኛ ተጎድቶ ስለነበር ራቁቱን መሆኑን ረስቶት ሕመሙን ሲያስታምም እኛ በጣም እንስቅበት ነበር፡፡

ገንዘብ ያጣ ሰው ሲያገኝ ያለፈውን ችግሩን ዞሮ ለማስታወስ የማይቸግረው ለምን ይመስልሃል?

ታሪኩ፡- ብዙ ጊዜ ገንዘቡን የሚያገኝበት መንገድ ይወስነዋል፡፡ በአጋጣሚ ያገኘው ወይም ምንም ያልለፋበት ከሆነ ያጣበት ወቅት ጨርሶ አይታወሰውም፡፡ ጥሮ፣ ግሮ፣ ለፍቶ ያገኘው ከሆነ ግን በአንድ ወቅት ማጣቱን እያሰበ በጥንቃቄ ይኖራል፡፡

“300 ሺህፊልም ማስተላለፍ የፈለጋችሁት መልዕክት ምንድነው?

ታሪኩ፡- ፊልሙ የተማሪዎች ፊልም ነው፤ ይበልጥ እነርሱን ይመለከታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ ማንኛውም ሰው ለተፈጠረበት ዓላማ ሊኖር ይገባል፤ በፊልሙ እንዲተላለፍ የተፈለገው መልዕክት ለዓላማ መኖር እንደሚገባ ነው፡፡

ከአንጋፋ የፊልም ባለሙያዎች ምን የተማርከው ነገር አለ?

ታሪኩ፡- በፊልም ሙያ ውስጥ ከፍተኛ ትዕግስት እንደሚያስፈልግ እንዲሁም ለፈለግሁት ነገር እስከ… የማይባል መስጠትን ተምሬያለሁ፡፡