ልጅ ኤልያስ (የአማርኛ ሳይንስ ኮሌጅ መሥራች
እንግዳችን ልጅ ኤልያስ በቀደመው የግዮን መጽሔት ቁጥር 225 ዕትም በነበራቸው ቆይታ በፈጠራና ሳይንስ ዕውቀቶች የላቀ ዐቅም ያለው የተማረ ትውልድ ለመፍጠር መደረግ ስለሚገቧቸው የሥርዓተ ትምህርት ለውጦች ሰፋና ዘርዘር ያሉ አስተያየቶችን መሥጠታቸው ይታወቃል፡፡
ችግሩን ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት ውስጥ፣ እሳቸውም እንደዜጋ ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹የአማርኛ ሳይንስ ኮሌጅ›› በመክፈት አጋዥ ለመኾን እንቅስቃሴ መጀመራቸውንም ገልጸው ነበር፡፡ ለመኾኑ ይኽንን ፕሮጀክታቸውን በምን መልክ ወደ መሬት ለማውረድ ዐቅደዋል? አጠቃላይ ሒደቱስ ምንን ይጠይቃል? ዐማርኛ ቋንቋ የተመረጠበት አግባብስ እንዴት ነው የሚሉትንና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ በሚከተለው መልኩ የመጨረሻውን ክፍል ቆይታ ከዝግጅት ክፍላችን ጋር አድርገዋል፡፡ መልካም ንባብ!
ግዮን፡- የእርስዎን ፕሮጀክት ለመደገፍ የሚመጡ ሰዎች በምን መልኩ ነው መረጃ የሚያገኙት?
ልጅ ኤልያስ፡- አሜሪካ ላሉ ሰዎች የቢሮ አድራሻ አለን፡፡ ድረ-ገጽ (ዌብሳይት)ም አለን፡፡ የፌስቡክ ገጻችንም ብዙ ሰዎች የሚሳተፉበትና በጣም ተደራሽ ነው፡፡ ብዙ ሰዎችም እየደወሉ ያናግሩኛል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ተነሳሽነት ያስፈልጋል፣ የእኔነት ስሜት ሊኖር ይገባል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ያለኝን አቅም አሳንሼ አላየውም፡፡ ሰዎች በማንኛውም መንገድ መድረስ የሚችሉበት ብዙ ዐይነት አማራጮች ይፈጠራሉ፡፡ ከዚህ ባለፈ አሜሪካ ውስጥ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ብቻ ሳይኾን ከእኛ ጋር መሥራት የሚፈልጉ ትላልቅ ተቋማት አሉ፡፡ እኔ እንደጀማሪ ሁሉን ነገር በአንድ ጊዜ ለመንካት አልፈልግም፡፡
ግን እየተዘረጋ ያለው አወቃቀር ይህን ይመስላል፡፡ ዋናው የእኛ ትኩረት አሁን ላይ ካሪኩለሙን ማዘጋጀቱ ላይ ነው፡፡ ምክንያቱም ትምህርቱ ራሱ ተቀባይነት ሲኖረው ነው መሥራት የሚቻለው፡፡
ግዮን፡- የአማርኛ ሳይንስ ዩኒቨርስቲ ለመክፈት ያነሳሳዎት ምንድንነው? ቁጭቱስ ከየት የመጣ ነው?
ልጅ ኤልያስ፡- ወደዚህ ሥራ እንድገባ ያደረገኝ በዋናነት ማዕድን ሚኒስቴር የተመላለስኩትና መልስ አልባው ጥያቄዬ ነው፡፡ የማዕድን ጥናት በእኛ ሀገር ኋላ የቀረ ነው፡፡ የአንድን ሀገር የማዕድን ሀብት ማጥናት በራሱ የሀገሪቱ የጀርባ አጥንት ነው፡፡
እኛ ሀገር ግን እንኳን ጠንካራ የጥናት ማዕከላት መቋቋም ይቅርና ዘርፉ ራሱ በደንብ ያልተደራጀ ነው፡፡ እኔ በግሌ ማዕድን ሚኒስቴር ስመላለስ ብዙ ነገር ነው የገባኝ፡፡
ይህን ‹‹የአማርኛ ሳይንስ ኮሌጅ›› የመክፈት ቁጭትና ተነሳሽነትም የመጣው ከዚሁ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ሳይንስ በቋንቋችን በተደራጀ መንገድ መሰጠት አለበት የሚለው ስሜት ያደረብኝም ከዚህ በመነሳት ነው፡፡ በርካታ የኢትዮጵያ ጠበብቶች በሥራቸው የሚታወቁት በኢትዮጵያ ሳይኾን በሌላው ዓለም ነው፡፡
በአንጻሩ በሀገራችን የውጭ ሀገር ተመራማሪዎች መጥተው ያገኙትን ሁሉ እንዳለ ይዘው ይሄዳሉ፡፡ በራሳቸው መንገድ ኢትዮጵያ የሥልጣኔ መነሻ መኾኗን የሚያሳዩ በርካታ መረጃዎችን በእጃቸው ያስገባሉ፡፡ መልሰው የእኛ የኾኑትን ነገሮች ይነግሩናል፡፡
የእኛን ሥልጣኔ እኛ ሳናውቀው እነሱ በሚፈልጉት መልኩ ሊያሳውቁን መሞከራቸው ለእኔ ሌላው የሳይንስ ኮሌጅ እንድከፍት ያነሳሳኝ ምክንያት ነው፡፡
በሳይንስ የበቃ ትውልድ ማፍራት ሀገርን ከባዕድ ተመራማሪና ጠበብቶች ማላቀቅ ያስችላል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ትልቁ ችግር ትምህርት ላይ መሠረት ያደረገ ልማት አለመኖሩ ነው፡፡ ለምሳሌ በሀገራችን ከተሞች በጣም ሀብታምና ስኬታማ የሚኾኑት ሰዎች ከገጠር የሚመጡ ሰዎች ናቸው፡፡
በትምህርት ላይ ተመሥርተው ኢንደስትሪ ያቋቋሙ ሰዎችን አናይም፡፡ ኢንደስትሪ ያቋቋሙ ሰዎች ኢንቨስትሮች እንጂ እውቀት መሮች አይደሉም፡፡ የኢንደስትሪዎቻችን የዕውቀት ባለቤቶች የውጭ ሰዎች ናቸው፡፡ ከቻይና፣ ከቱርክ፣ ከሕንድ አልያም ከአውሮፓ የመጡ ናቸው፡፡
አንድ ወቅት ኢትዮጵያ እያለሁ ‹‹ቢ 29›› ሳሙና የሚመረትበት ተቋም ውስጥ ለአጭር ጊዜ እሠራ ነበር፡፡
ሳሙናው ኢትዮጵያ ውስጥ ቢመረትም ጥሬ እቃው ግን ከኢንዶኖዢያ ነበር የሚመጣው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠራው ማቀነባበር ብቻ ነው፡፡ ይሄ ማለት ጥሬ ዕቃውን ሳናውቀው ነገር ግን የምርት ማዕከል ኾንን ማለት ነው፡፡ እኔ በዚያን ወቅት ‹‹ማነው ያጠናው?›› ስል ጠይቄ ነበር፡፡ ያገኘሁት መልስ ‹‹የኩባንያው ባለቤቶች›› ማለትም የውጭ ሰዎች እንዳጠኑት ነው፡፡ ምክንያቱም እኛ ልናጠናው ያልቻልነው ኢትዮጵያውያን ኢንጂነሮች ሰብስበን ማስጠናት ስላልቻልን ነው፡፡
የዚህ ዲዛይን የጥናት መንገዱ የሚገኘው ደግሞ ከትምህርት ቤት ነው፡፡ በሌላ ዓይነት መንገድ አይመጣም፡፡ በአገር ቤት እውቀቱ ሊስፋፋ የሚችለው ካሪኩለም ተቀርጾለት ትምህርት ኾኖ ሲቀርብ ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ገንዘብ የሚከማቸው በመነገድ እንጂ የፈጠራ ጥበብን ተጠቅሞ ኢንዱስትሪ በማቋቋም አይደለም፡፡
የማሽን አሠራር፣ ብረት እንዴት እንደሚቀልጥ፣ ብረት እንዴት ከተፈጥሮ ንጥረ ነገር ይወጣል የሚለው ላይ ትምህርት ካልተሰጠ በሀገራችን በዘርፉ ለውጥ የምናመጣበት መንገድ የለም፡፡ የእኛ ተቋም ወደፊት እነዚህን ጥያቄዎች ሊመልስ የሚችል ነው፡፡
በምንመሠርተው ዩኒቨሲርቲ የተማሩ ልጆች በዘርፉ ማጥናት ብቻ ሳይኾን ትላለቅ የፈጠራ ሥራዎችን ማፍለቅ ይችላሉ፡፡ ካለበዚያ እኛ የቴክኖሎጂው ባለቤት ካልኾን ለአጋሮቻችን ሁሉ ሠራተኛና አገልጋይ ብቻ ኾነን ነው የምንቀረው፡፡
ግዮን፡- እናንተ ሳይንስን በአማርኛ በኮሌጅ ደረጃ ነው ለማስተማር ያቀዳችሁት፡፡ በታችኛው የትምህርት እርከንስ መሰጠት የለበትም ይላሉ?
ልጅ ኤልያስ፡- 12ኛ ክፍል የጨረሱ ተማሪዎች የ1ኛ፣ 2ኛ፣ 3ኛ እና 4ኛ ዓመት ትምህርታቸው በየደረጃው እንደየክብደቱ የተቀመጠ ነው የሚኾነው፡፡ በተጨማሪም የኮሌጅ ኬሚካል ኢንጂነሪንግና የኮሌጅ ኬምስትሪ ነው የምናስተምረው፤ ሲቪል ኢንጂነሪንግና ኤለክትሪካል ኢንጂነሪንግም እናስተምራለን፡፡
ስለ ትምህርቱ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ከታች ጀምሮ ማስተማር አያስፈልግም ወይ ለሚለው እራሱን የቻለ ስታንዳርድ አዘጋጅተናል፡፡ እኛ ግን የምናስተምረው ኢንጂነሮችን ነው፡፡ እራሳቸው ፓተንት ሠርተው ፋብሪካ ማቋቋም የሚችሉበትን ዕውቀት ነው የምንሠጣቸው፡፡ ከአንደኛ ክፍል ጀምረን አናስተምርም፡፡
እኛ የምናስተምረው ከ12ኛ ክፍል በኋላ ነው፡፡ ቃላቱም አማርኛ በመኾኑ ለብዙ ተማሪዎች ፈተና አይኾንባቸውም፡፡ ተምረው ሲመረቁ ገንዘብ እንኳን ባይኖራቸው ከባንክና መሰል ተቋማት ጋር በመጣመር ራሱን የቻለ ተቋም መመሥረት ይችላሉ፡፡ እኛ የምናሳያቸው የሀገሪቱን ጥሬ ሀብት በምን ዓይነት መንገድ መጠቀም እንዳለባቸው የሚያስችላቸውን እውቀት ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የትኛውንም ትምህርት በእንግሊዘኛ ተምሮ ሥራ ሲቀጠር የሚሠራውና የሚግባባው በአማርኛ ነው፡፡ በእንግሊዝኛ መማር የሚያስፈልገው ሌላ ሀገር ሄዶ መሥራት ለሚፈልግ ሰው ነው፡፡ ሳይንስን በሚገባው ቋንቋ መማር ማለት በቀላሉ የተማረውን ለመሥራት ይችላል ማለት ነው፡፡
እነ ቻይና፣ ጀርመን፣ ራሸያ እና የመሳሰሉት ሀገራት ተማሪዎቻቸውን የሚያስተምሩት በእንግሊዘኛ ሳይኾን በራሳቸው ቋንቋ ነው፡፡ ቴክኖሎጂያቸውንም ማሳደግ የቻሉት በዚያ መንገድ ነው፡፡
ግዮን፡- ተቋማችሁ ሁለት ነገር ነው መሥራት የፈለገው፡፡ አንዱ ሳይንስን በአማርኛ ሲኾን ሁለተኛው ደግሞ አማርኛን በአፍሪካ ደረጃ የሚነገር ቋንቋ ማድረግ ነው?
ልጅ ኤልያስ፡- በትክክል! ማኅበረሰብ ራሱ ይህን ነገር በደንብ ማወቅ አለበት፡፡ ወደ ምንፈልገው ተግባር ለመግባት የምንችለውም በመጀመሪያ ዓላማው ሲታወቅ ነው፡፡ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት በባዕድ ቋንቋ ነው የሚማሩት፡፡ ሰው በባዕድ ቋንቋ ሲማር ምናባዊ የኾኑ ነገሮችን የመረዳት አቅሙ ዝቅተኛ ይኾናል፡፡ በርካታ አፍሪካውያን በምዕራባውያን ቋንቋ ከሚማሩ ይልቅ በእኛ ቋንቋ ቢማሩ እንደሚመርጡ በተለያየ አጋጣሚ ይገልጻሉ፡፡
በግልም ብዙ አፍሪካውያን ጓደኞች አሉን፡፡ ከእነርሱ እንደተረዳሁት የኢትዮጵያን ቋንቋ ለማወቅና የኢትዮጵያን ፊደል ለመማር በጣም ፍቃደኞች ናቸው፡፡ ይሄ ወደፊት በጣም እየተስፋፋ ሲመጣ ትምህርቱ አፍሪካ ላይ እየኾነ ይመጣል፡፡ ትልቅ ለውጥም ያመጣል፡፡ እኛ አሁን ለሕዝቡ የማስተዋወቅ ሥራ እየሠራንም ነው፡፡ ይህ ማለት መጀመሪያ ግንዛቤ እንዲፈጠር ነው፡፡
ግዮን፡- አማርኛ የአፍሪካ ሕብረት ተጨማሪ ቋንቋ እንዲኾን ጥረቶች ተጀምረዋል፡፡ እናንተስ ከሕብረቱ ጋር ለመሥራት አቅዳችኋል?
ልጅ ኤልያስ፡- በመጀመሪያ እኛ ኢትዮጵያውያን እንዴት የእንግሊዘኛ ጥገኛ እንደኾንን አላውቅም፡፡ የራሳችን በቂ ቋንቋ እያለን እስካሁን እሱን ለማሳደግ እንዴት እንዳልሠራን ይገርመኛል፡፡ በሀገራችን ትላልቅ እውቀት ያላቸው ምሁራንን ያቀፉ ዩኒቨሲርቲዎች አሉ፡፡ ተቋማቱ በሕክምና እና በሌሎች ዘርፎችም እስከ ዶክትሬት ድረስ ያስመርቃሉ፡፡ በርካታ የተማሩና የላቀ እውቀት ያላቸው ኢትዮጵያውያንም በሀገራችን የትምህርት ሥርዓት ላይ አሉ፡፡
ነገር ግን ሀገራችንን በሚጎዳ መልኩ በባዕድ ቋንቋ እንድንማር ለምን እንደወደዱ ማወቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ በእርግጥ አማርኛ ቋንቋን አሳድጎ የማስተማሪያ ቋንቋ ማድረግ እና በአፍሪካ ደረጃ ከፍ ለማድረግ አንዱ ተግዳሮት በሀገራችን ብዙ ቋንቋዎች የሚነገሩ መኾናቸው ነው፡፡ ‹‹ክልሎች በራሳቸው ቋንቋ…›› የሚለው አሠራር ሲመጣ ብዙ ነገሮች እየተከፋፈሉ መጡ፡፡ የኢትዮጵያ ዋናው ቋንቋ አማርኛ ኾኖ ሳለ እሱ ላይ እንዳይሠራ መደረጉ ትልቅ እንቅፋት ፈጥሯል፡፡
ነገር ግን ምዕራባዊ በቋንቋችን ሳይንስ እንዳናውቅ ሲሠሩ ነበር፡፡ ይህ የተጀመረው በቅኝ ግዛት ዘመን ነው፡፡ ምዕራባዊ በመጀመሪያ አፍሪካን ሲቀራመቱ እነሱ ያወቁትን የቴክኖሎጂ ልክና ጥበብ እንዳናውቅ ለማድረግ ብዙ ጥረዋል፡፡ ቅኝ ገዥዎች አውሮፕላን እንዴት እንደሚሠራ፤ መኪና እንዴት እንደሚሠራ፤ ባቡር እንዴት እንደሚሠራ፤ ሕዝቡን ለማስተማር ወደ አፍሪካ አልመጡም፡፡
የእነሱን የቴክኖሎጂ ውጤቶች የሠሩባቸው ግብዓቶች አፍሪካ ላይ እንዳሉ አውቀው እሱን ለመዝረፍ ነው የመጡት፡፡ እነርሱ ሲዘርፉ ለምን የሚል ጥያቄ እንዳይነሳባቸው ሰውን እውቀት ነፈጉት፡፡ ቋንቋን መነሻ በማድረግ ሕብረተሰቡ እንዲከፋፈል አደረጉ፡፡
እኔ ደግሞ ሀገሬን መጥቀምና ማሳደግ ስለምፈልግ ያለኝን እውቀት እሰጣለሁ፡፡ ‹‹ከዚህ አፈር ውስጥ ይሄ ብረት ይወጣል፣ ከዚህ አገር ውስጥ ይሄ ማዕድን ይወጣል፣ እንዴት ነው የሚወጣው? በምን ዓይነት መንገድ ነው የሚወጣው?›› የሚለውን ነገር እናገራለሁ፡፡ እነሱ ግን ይህን የሚናግሩት ለራሳቸው ማኅበረሰብ እንጂ ለአፍሪካውያን አይደለም፡፡ እንዲያውም አፍሪካውያን በእውቀት እንዳይመጥቁ ከፍተኛ ገንዘብ አውጥተው ሤራ ያሤራሉ፡፡
እኛን አባልተው የሀብት ምንጫችንን ለመዝረፍ በትጋት ይሠራሉ፡፡ እነርሱ አየርን መሠረት አድርገው ማዳበሪያ ይሠራሉ፡፡ አየር ከአፍሪካ የጠፋ ነገር አይደለም፡፡ ነገር ግን እውቀት ባለመኖሩ የእነርሱ ጥገኛ እንድንኾን ተደርገናል፡፡ ስለዚህ አሁን እኛ ዐይናችን የሚገለጥበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡ ቴክኖሎጂው አለን፡፡ ሰዎች ላይ ግን ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡
ሙያተኞችን በትክክለኛው መንገድ ማሠልጠን ያስፈልጋል፡፡ ይሄን ለማድረግ ደግሞ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀዳሚውን ቦታ የምትይዝ ነች፡፡ ኢትዮጵያ ተደማጭ ሀገር ነች፡፡ በደንብ ከሠራንበት እንደ ቻይና እና ጃፓን ከፍተኛ ትርፍ አግኝተን ማደግ እንችላለን፡፡
ቀዳሚ ኾነን ከወጣን ከአፍሪካ ሀገሮች ራሱ ከፍተኛ ገበያ ነው የምናገኘው፡፡ አፍሪካውያን እኛ የደረስንበት ቦታ ላይ እስኪደርሱ ድረስ ከፍተኛ ሀብት ማካበት እንችላለን፡፡ ስለዚህ ከአፍሪካ ሀገሮች ጋር አብሮ ለመሠራት መዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ዙሪያ የትኛውም የአፍሪካ ሀገር ተንኮል የለውም፡፡ ቋንቋችንን እስከተቀበሉ ድረስ ሌላውንም መቀበል ፈተና አይኾንባቸውም፡፡
‹ማስታወሻ፡- ውድ አንባቢያን ከልጅ ኤልያስ ጋር ያደረግነው ቆይታ በዚህ አልተጠናቀቀም፡፡ ቀጣዩን ክፍል በሚቀጥለው ቀናት ይዘን የምንቀርብ ይኾናል፡፡
በ“ግዮን” መጽሔት ቅዳሜ መስከረም 10 2018 ዓ.ም የወጣ
