“ሻምፒየንስ” ን አየሁት!

Date:

በከተማችን ስም ካላቸው የትምህርት ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው ሻምፒየንስ አካዳሚ በእህት ኩባንያው SOZO Psychological Services አማካኝነት በአካቶ ትምህርት ፕሮግራሙ የሚያሰለጥናቸውን ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆች ልዩ የክረምት መርሃግብር ስልጠና ለማየት ዛሬ ረፋድ ላይ ጀሞ አካባቢ ወደሚገኘው ካምፓሱ ብቅ ብዬ ነበር።

ትሁቷን የትምህርት ቤቱ መስራችና ባለቤት ወይዘሮ መዓዛ መንክርን አገኘኋት። መዓዛ ከሻምፒየንስ በተጓዳኝ በአእምሮ ጤና እና የኦቲዝም ሕክምና (Therapy) አገልግሎት ግንባር ቀደም ተቋም የሆነው የ SOZO Psychological Services መስራች ናት።

ከኔ ጋር ዩኒቨርሲቲ አንድ ካምፓስ ነው የተማርነው። በ2013 ዓ.ም. ያሳተመችውን “ሁሉም በአንድ: ተግባር-ተኮር የሕክምና መጽሐፍ” ካነበብኩት ቆይቻለሁ።

ይህ መጽሃፍ በተለይ በኦቲዝም ጥላ ሥር የሚኖሩ ልጆች ያሏቸው ወላጆች ከምርመራ እስከ ሕክምና የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች ከነመፍትሄዎቹ የሚያጋራ ነው። “የዩኒቨርሲቲ ባቼ” መሆኗን ሳላውቅ በፊት “ይህች ሴት ይህንን ድንቅ መጽሃፍ የመጻፍ አቅም ካላት በዘርፉ ብዙዎችን ማብቃት ትችላለች” ብዬ ነበር ያደነቅኳት።

ከብዙ አመታት በኋላ ባሳለፍነው ቅዳሜ “የማይናገረው ልዑል መጽሃፍ”ን ስናስመርቅ ሃይሌ ግራንድ ሆቴል መጥታ ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል አገኘኋት። የምትመራውን ተቋም ማየት እንደምፈልግ ነግሬያት በፍጹም የራስ መተማመን መንፈስ “በደስታ!” ነበር ያለችኝ።ለዚያ ነው ዛሬ የሄድኩት።

እንደምታውቁት ኦቲዝም በሃገራችን እየሰፋ የመጣ ማህበራዊ ችግር ሆኗል።አሁን ያለውን የኦቲዝም መስፋፋት መጠን (Prevalence rate) በተመለከተ ምንም ሃገርበቀል ጥናት አልተካሄደም።

ይህ የመረጃ እጥረት ደግሞ መንግስት ኦቲዝም እያስከተለ ያለውን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና በቅጡ እንዳያውቅና ጣልቃ እንዳይገባ አድርጎታል።

በዚህ የተነሳም ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም አይነት በመንግስት የሚደገፍም ይሁን በመንግስት ባለቤትነት የሚካሄድ ኦቲዝም ተኮር ፕሮጀክት የለም ።በውጤቱም፣ ኦቲዝም ያለባቸው ልጆች በቂ የመዋያ፣ የመማሪያ እና የህክምና ስፍራ አልተዘጋጀላቸውም።

ከችግሩ መስፋፋት አንጻር ኦቲዝም ላይ የሚሰሩ ጥቂት ግብረሰናይ ድርጅቶች ቢኖሩም የሚሰጡት አገልግሎት የደረሳቸው ህጻናት እጅግ በጣም ውስን ናቸው (ከአንድ ሺህ አይበልጡም)

በዚህ የተነሳም ብዙ ልጆች ደረጃውን ላልጠበቀና በባለሙያ ለማይመራ የኦቲዝም ቴራፒ አገልግሎት ተጋልጠዋል። በተለይ የአካቶ ትምህርት የሚሰጡ መደበኛ ትምህርት ቤቶች አሁን ካለው ፍላጎት አንጻር በአቅምም፣ በቊጥርም እጅግ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ናቸው።

በዚህ ሳቢያ ብዙዎች ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆች በአገልግሎት ማጣት ሳቢያ በየቤቱ እየባከኑ፣ ለወላጅ ከትከሻ የማይወርድ ሸክም እየሆኑም ነው። ይህም በነጠላው ለቤተሰብ በድምሩ ለሃገር ትልቅ ችግር ደቅኗል።

የመዓዛ መንክር “ሻምፒየንስ አካዳሚ” ከተቋቋመ ረጅም አመት ያስቆጠረ፣ በአካቶ ትምህርት ዘርፍም ከፍ ያለ አስተዋጽዖ እያደረገ የሚገኝ ዝና ያለው ትምህርት ቤት ነው።

ከጅምሩም መዓዛ ራሷ በልዩ ፍላጎት ዘርፍ ቀደምት ባለሙያ እንደመሆኗ ያቋቋመችው ትምህር ቤት ነውና ተቋሙ የብቁ ባለሙያ ቤት ሆኖ ነው ያገኘሁት።

እንደደረስኩ የክረምት መርሃ ግብር ላይ ያሉትን ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆች በየክፍላቸው ተዘዋውሬ አየኋቸው።ልጆቹ ከክፍል ውጪ የሚያደርጉትን ትምህርታዊ ስልጠናና አክቲቪቲም ጎበኘሁ።

የትምህርት አሰጣጡን፣ የመማሪያ ስፍራውን ንጽህና፣ ለመማር ማስተማር ሂደቱ የሚጠቀሙባቸውን ግብዓቶችና አጠቃላይ የግቢውን ለዚህ ዓላማ አመቺነት ጊዜ ወስጄ ታዘብኩ ።

እሱ ላይ ስለጋንን ዕውነት መናገር አለብኝ። ባየሁት ሁሉ በጣም ተደንቄ ፣ በጣም ረክቼና በጣም ደስ ብሎኝ ነው ከዚያ ግቢ የወጣሁት።

ከ3 ዓመት እስከ 10 ዓመት ድረስ ያሉት ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆች የአካዳሚ ደረጃቸውን ፣ የህይወት ክህሎታቸውንና፣ የተግባቦት መጠናቸውን ስታዘብ ብዙዎቹ እንደውም ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ እስከማይመስሉኝ ድረስ በብዙ የተለወጡ ሆነው ነው ያገኘኋቸው። (ኦቲዝም በሽታ ባለመሆኑ “የዳኑ” የሚል ቃል መጠቀም ተገቢ ስላልሆነ ነው)

ልጆቻቸውን ሊወስዱ መጥተው በአጋጣሚ ያገኘኋቸውን ወላጆችም አነጋግሬያቸው ነበር። እነዚህ ወላጆች ልጆቻቸው ቀድሞ ከነበራቸውና አሁን ካሉበት ደረጃ ጋር እያነጻጸሩ ለውጣቸውን ሲነግሩኝ እርካታ እና ደስታ እያየሁባቸው ነበር። ለሁሉም ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆች የሚያሳድጉ ወላጆች ይህንን ደስተኛ፣ ተስፋ የሞላውና ብሩህ ፊት እየተመኘሁ ነው የሰማኋቸው።

ከሁሉም የደነቀኝ አካዳሚው ልጆቹን የሚያሰለጥንበትና የሚያስተምርበት መንገድ ነው። DSM 5 የሚባለው በዓለምቀአፍ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ማኑዋል በሚያዘው መሰረት እንደልጆቹ የኦቲዝም ደረጃ የተጠና እና በቀላል ሁኔታ መተግበር የሚችል ቴራፒ ሲሰጥ አይቻለሁ።

ቴራፒስቶቹ ቴራፒ ከሚሰጡባቸው ተቆጥረው ከማይዘለቁ ማቴሪያሎች ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ የሚሆኑት በቤት ውስጥ ከሚገኙ የማይጠቅሙ የሚመስሉ ነገሮች በልዩ ፈጠራና በውብ ሁኔታ የተዘጋጁ መሆናቸው ደግሞ ይበልጥ አስደንቆኛል።

ብዙ ወላጆች ለከፍተኛ ወጪ የሚዳረጉባቸው ከውጭ የሚገቡ የቴራፒ ማቴሪያሎች እንዲህ በቀላል በቤት ውስጥ እንደሚዘጋጁ አላውቅም ነበር።

በግሌ ከኦቲዝም ጋር የሚኖሩ ልጆች የሚረዱበት በርካታ የኦቲዝም ማዕከላትን አይቻለሁ። እሱ ይቆየንና ሻምፒየንስን ማነጻጸር ካለብኝ ግን ካየኋቸው አካቶ ትምህርት የሚሰጡ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ጋር መሆን አለበት።

እስካሁን ባለኝ መረጃ በሻምፒየንስ አካዳሚ ደረጃ ልጆችን በእድሜ፣ በችሎታ፣ በባህሪና በክህሎት ከፋፍሎ ፣ ለእያንዳንዱ በአሴስመንት ላይ ተመርኩዞ የተዘጋጀ የግል የትምህርት እቅድ (IEP) በመጠቀም የሚያሰለጠንና ለመደበኛ ትምህርት የሚያዘጋጅ ተቋም አልገጠመኝም።ግቢውም ለዚህ ተብሎ የተዘጋጀ እስኪመስል ድረስ ውብ እና ለልጆቹ ደህንነትም ፍጹም ምቹ ሆኖ ነው ያገኘሁት ።

ያናገርኳቸው የአካዳሚው ቴራፒስቶችም የሚሰሩትን የሚያውቁ፣ በስልጠና የበቁና የእያንዳንዱን ተማሪ ለውጥ ሂደት (Change trajectory) በሚገባ መግለጽ የሚችሉ፣ ለውጡንም በዋና ዋና ውጤት መለኪያዎች ( KPI) መሰረት የሚሰሩና የሚገመገሙ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ።

ገንዘቡና ትርፍ እንጂ የልጆቹና የወላጅ ችግር የማያሳስበው፣ ልጆቹን በአንድ ክፍል አጭቆ ያለመርጃ መሳሪያ አውሎ የሚመልስ ‘በስመ አካቶ’ የተቋቋመ ትምህርት ቤት በበዛበት ከተማ እንደሻምፒየንስ አካዳሚ ያለ ቢዝነስን በሃላፊነት መንፈስ የሚሰራ የትምህርት ተቋም ማግኘት በራሱ ተስፋ የሚሰጥና የሚያበረታታ ነው።

ልጆቹ ላይ ከመስራት ባሻገር በየሳምንቱ ቅዳሜ ለወላጆች ስልጠና እንደምትሰጥ የነገረችኝን መዓዛን ጉብኝቴን ጨርሼ ልወጣ ስል ያልኳት ነገር አንድ ነው ።

“በርቺ! ስራ በባለሙያ ሲሰራ እንዴት እንደሆነ ማስተማሪያ ነሽ፣ ለዚህ ዘርፍ በስነምግባር መመራት ያንቺ መኖር በጣም ያስፈልጋል፣ ሌሎች ካምፓሶችንም በመክፈት አገልግሎትሽን በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የወላጆችን እንባ ማበስ ሃላፊነትሽ ነው”

አዎ! የችግሩን ጥልቀት የምናውቅ ሁሉ መዓዛ መንክርን “በርቺ!!” ልንላት ግድ ነው!

ከመላኩ ብርሃኑ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የኢራን ጠቅላይ መሪ ለአባታቸው ግድያ “የበቀል እርምጃ” እንደሚወሰድ ተናገሩ

የኢራን ጠቅላይ መሪ ሞጅታባ ኻሜኒ በጽሑፍ ባስተላለፉት መልዕክት አባታቸው...

የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን የመጨረሻ ልምምዱን ሰርቷል

ቡድኑ ነገ የአለም ዋንጫ ማጣሪያ የመጨረሻ ዙር የመልስ ጨዋታውን...

ኢራን ከአሜሪካ ጋር ለመደራደር አለመጠየቋን አስታወቀች

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኢስማኤል ባጋይ፤ አገራቸው...

ሱዳን ዉስጥ ለሦስት ዓመታት የተካሄደው ጦርነትን ሰለ ማቆም

የሱዳን ብሔራዊ ጦር ለሦስት ዓመታት የተካሔደውን ጦርነት ለማቆም አሜሪካ...