በሥልጣን ላይ የሚገኙት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራሮች ለፓርላማ አባልነት በሚወዳደሩባቸው ስፍራዎች ገዢው ብልጽግና ፓርቲ እጩ አለማቅረቡ ታውቋል።
ግንቦት 2018 ዓ.ም. ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው ሰባተኛው አጠቃላይ ምርጫ ተቃዋሚው ፓርቲ አብን 70 ዕጩዎችን አቅርቧል። ከነዚህ ውስጥ ስድስት የሥራ አስፈጻሚ አባላቱን ጨምሮ 16 ያህሉ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይወዳደራሉ።
ብልጽግና ፓርቲ፤ 547 መቀመጫዎች ላሉት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው 466 ዕጩዎችን ብቻ ነው። ይህም ገዢው ፓርቲው በዘንድሮው ምርጫ በ81 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ላይ እንደማይወዳደር ያሳያል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
ገዢው ፓርቲ በአማራ ክልል ከማይወዳደርባቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች መካከል ለሰባቱ፤ ተቃዋሚው አብን አመራሮች እና አባላቱን ዕጩ አድርጎ ያቀረበባቸው መሆኑን ዘገባው አመላክቷል።
ከእነዚህ ምርጫ ክልሎች አንዱ፤ የአብን ሊቀመንበር እንዲሁም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ካቢኔ ውስጥ የቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ሚኒስትር የሆኑት ዶ/ር በለጠ ሞላ የሚወዳደሩበት “ራያ ቆቦ” ነው።
የአብን ምክትል ሊቀመንበር እንዲሁም የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ የሆኑት መልካሙ ፀጋዬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚወዳደሩበት “ላይ ጋይንት 1” ምርጫ ክልልም ብልጽግና ዕጩ አላቀረበም።
ብልጽግና የፓርላማ ዕጩ ያላቀረበበት ሌላኛው ምርጫ ክልል “ኩታበር” ነው። በዚህ ምርጫ ክልል፤ የአዲስ አበባ ከተማ የመንግሥት ንብረት አስተዳደር ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የአብን የሕግ ጉዳዮች ኃላፊ የሆኑት አቶ የሱፍ ኢብራሂም ይወዳደራሉ።
የአብን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንዲሁም የኢትዮጵያ ፖስታ የአቅርቦት እና ፋሲሊቲ ቺፍ ኦፊሰር የሆኑት አቶ ጋሻው መርሻ የሚወዳደሩበት “እስቴ 1” ምርጫ ጣቢያም በተመሳሳይ ብልጽግና ለተወካዮች ምክር ቤት ዕጩ አላቀረበበትም።
የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ዳምጠው ተሰማ እና ማሩ ጃኔ በዕጩነት በተመዘገቡባቸው ቦታዎችም ገዢው ፓርቲ አይወዳደርም። የቀድሞ የፓርቲው አመራር ጣሂር ኢብራሂምም አብንን ወክለው በቀረቡበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ከብልጽግና ጋር አይፎካከሩም።
በተመሳሳይ መልኩ ገዢው ፓርቲ በአዲስ አበባ ከተማ ከማይወዳደርባቸው ሦስት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ውስጥ በሁለቱ ላይ በዕጩነት የቀረቡት የተቃዋሚው ፖለቲካ ፓርቲ ኢዜማ አመራሮች ናቸው።
በቅርቡ የኢዜማ መሪ ሆነው የተመረጡት ኢዮብ መሳፍን ለተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩት በአዲስ አበባ ከተማ “ምርጫ ክልል 18” ነው። ይህ ምርጫ ክልል ብልጽግና ዕጩ ካላቀረበባቸው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች አንዱ ነው።
የኢዜማ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ ንጋቱ ወልዴ የሚወዳደሩት ደግሞ በ”ምርጫ ክልል 23″ ሲሆን በዚህም ስፍራ ብልጽግና ዕጩ አላስመዘገበም።
