መቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ሕሙማን ማእከል አያት መድኃኔዓለም ጠበል አካባቢ በሚገኘው ዋናው ግቢ ከ8 ሺሕ በላይ አረጋውያንን፣ አእምሮ ሕሙማንን፣ በአልጋ ላይ የቀሩና ራሳቸውን ችለው መጻዳዳት የማይችሉ ወገኖችን- በሰብአዊነት፣ በፍቅርና በኢትዮጵያዊ የመረዳዳት የቆየ ባህላችን – ቤተሰባዊ እንክብካቤ እያደረገ የሚገኝ ሀገር በቀል የበጎ አድራጎት ተቋም ነው፡፡
የማእከሉ መስራች እና ዋና ሥራ አስኪጅ ዶ/ር ብንያም በለጠ እንደተናገሩት፤ መቄዶንያ በአሁን ሰዓት በተለያዩ የሀገራችን ክልሎች ያሉት ቅርንጫፎቼ ከ50 በላይ ደርሰዋል፡፡ በማእከሉ ቤተሰባዊ እንክብካቤ እያገኙ ያሉ ወገኖች ቁጥርም ከጊዜ ወደ ጊዜ በጣሙን እየበዛ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
ለመቄዶንያ ማእከል መስፋፋትና ማደግ አሥር ሳንቲም ከሚሰጡ ወገኖቻችን ጀምሮ ባለ ሀብቶች፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ድርሻና አሻራ ጉልህ ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል ማእከሉን በተለያዩ ጊዜያት በሀብታቸው በማገልገል ላይ የሚገኙት አቶ በላይ ደበበ አንዱ ናቸው፡፡
እኚህ ባለ ሀብት የመቄዶንያ ማእክልን በበጎ ፈቃደኝነት እያገለገለች ያለችውን ልጃቸውን ወ/ት ብሩክታዊት በላይን በማእከሉ ቅትር ግቢ ውስጥ በትናንትናው እለት በደማቅ ሁኔታ ድረዋል፡፡
ብሩክታዊት በላይ በጓደኞቿ፣ በቤተሰብ፣ በወዳጅ ዘመድ ፍቅር ተከባና በመቄዶንያ አረጋውያን ምርቃት ጋብቻዋን በማእከሉ ግቢ ፈጽማለች፡፡
ጋብቻ በመንፈሳዊ አስተምህሮም ሆነ በአገራችን የኢትዮጵያ ባህል እጅግ የከበረ የቤተሰብና የአገር መሠረት የሆነ አንድነት/ቃልኪዳን ነው፤ አቶ በላይነህ፣ ልጃቸው ሙሽራዋ ብሩክታዊትና ቤተሰቦቿ ፈቅደው ሕይወት ዘመን ደስታዋን፤ ደስታቸውን በአረጋውያን ምርቃት የሰመረ ለማድረግ የልጃቸውን ሠርግ በመቄዶንያ እንዲያደርጉ ሲወስኑ ምክንያታቸው- ‹‹ፍቅር፣ ሰብአዊነት፣ ኢትዮጵያዊ የመረዳዳት ባህልና መልካምነት መሆኑን ነው፤›› የገለጹት፡፡
ይህ ቅዱስ ተግባር ሰብአዊነት፤ መልካምነት፤ በጎነት እና ፍቅር የነገሠበት ሰው የመሆን ምስጢርና የመንፈስ ልእልና መገለጫ ነው። “ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው!!” እንዲል የመቄዶንያ ማእከል መስራች ዶ/ር ብንያም በለጠ፡፡
በዲ/ን ተረፈ ወርቁ (የመቄዶንያ የአረጋውያና የአእምሮ ሕሙማን ማእከል የበጎ ፈቃደኛ አስተባባሪ/Volunteers Coordinator )
