በአሜሪካዋ ቴክሳስ ግዛት ባሳለፍነው አርብ በተከሰተው ከባድ የጎርፍ አደጋ የማቾች ቁጥር ከ 100 በላይ መድረሱ ተገልጿል ።
በማዕከላዊ ቴክሳስ በተከሰተው ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ሰዎች ደብዛቸው ጠፍቷል።
የማቾች ፍለጋ እና ነብስ የማዳን ስራዎች ጭቃ በተከመረባቸው የወንዝ ዳርቻዎች ላይ ተጠናክሮ ቢቀጥልም አደጋው ከተከሰተ ከአራት ቀናት በኋላ በሕይወት የተረፉ ሰዎችን የማግኘት ተስፋ እየደበዘዘ መሆኑ እየተገለጸ ይገኛል።
ማዕከላዊ ቴክሳስን የመታው ድንገተኛ ጎርፍ በኬር ካውንቲ ከፍተኛ ጉዳት ያስከተለ ሲሆን፣ ቢያንስ 84 ሰዎች መሞታቸው ተረጋግጧል። ከእነዚህ ውስጥ 56ቱ ጎልማሶች ሲሆኑ 28ቱ ደግሞ ህጻናት ናቸው።
የካውንቲ የሸሪፍ ጽህፈት ቤት እንደገለጸው፣ በኬር ካውንቲ ከሞቱት ሰዎች መካከል 22 ጎልማሶች እና 10 ህጻናት እስካሁን ማንነታቸው አልታወቀም።
በቀጣዮቹ ቀናት በግዛቱ ተጨማሪ ከባድ ዝናብ እንደሚጠበቅ የተተነበየ ሲሆን ከ 5ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የአካባቢው ዜጎችም ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዋይት ሀውስ በብሔራዊ የአየር ሁኔታ አገልግሎት (NWS) ላይ የበጀት ቅነሳ የአደጋውን ምላሽ ሊገታ ይችላል የሚለውን አስተያየት ውድቅ አደርጓል።
ዘገባው የቢቢሲ ነው
